ወይዘሮ አበበች ቶላ በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ ሰባት ነዋሪ ናቸው:: የበጎ ፈቃድ ስራ የጀመሩት በስታድየም አካባቢ የሚገኙ ህፃናት ልጆችን በመርዳት ነበር:: ልጆቹ መኪና ሲቆም በመለመን ነበር ኑሯቸውን የሚገፉት:: የልጆቹ ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ስለነበር እሳቸው ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር በመሆን በወር አንድ ቀን‹‹ ምሳዬን እኔም ለወገኔ›› በሚል የበጎ ስራ ለማከናወን ተሰባሰቡ:: እሳቸውና አብረዋቸው ያሉ ሰዎች በወር አንድ ቀን ለምሳቸው የሚያወጡትን ገንዘብ ማጠራቀም ጀመሩ:: በዚህ ሁኔታ የመጀመሪያውን የበጎነት ተግባር መጀመራቸውን ይናገራሉ:: በወር አንድ ጊዜ አንድ ሰው የምሳውን እስከ ሶስት መቶ ብር ድረስ የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህ ገንዘብ ከ15 እስከ 20 ሰዎች የሚታደግ ነበር::
ወይዘሮ አበበች በሰበሰቡት ገንዘብ በወር አንድ ጊዜ በስታዲየም የሚገኙ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ህፃናትን መመገብ ጀመሩ:: በጎዳና ላይ ህፃናት፣ አዋቂዎችና ወጣቶች ይገኛሉ:: ወይዘሮ አበበች በመመገብ ስራቸው ላይ በሶስቱም ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ይገልፃሉ:: እሳቸው የመመገብ ስራውን በሚያከናውኑበት ወቅት በጎዳና ላይ የሚያገኟቸውን ህፃናት፣ ወጣቶችና አዋቂዎችንም በእግረ መንገድ ይመግባሉ:: በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናት እጅግ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ኑሯቸውን ሲገፉ ማየት ልብ የሚነካ በመሆኑ ወይዘሮ አበበች የበጎነት ተግባራቸው ወደዛ እንዲያዘነብል ምክንያት እንደሆናቸው ያስረዳሉ:: ህፃናቱ በጎዳና ላይ ማስቲሽ በመሳብ የሆነ ቦታ ወድቀው ይገኛሉ:: ልጆቹ በወላጅ ክትትል ስር መሆን ሲገባቸው መኪና በሚቆምበት ወቅት ሲለምኑ ይታያል:: ሰዉም የመኪና መስታወት በመዝጋት ያልፋቸዋል:: ይህ ሁኔታ እሳቸውን ለልጆቹ የተሻለ ነገር እንዲያደርጉ እንዳነሳሳቸው ይጠቅሳሉ::
በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናት፣ ወጣቶችንና አዋቂዎችን ለመመገብ የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት በተለያዩ መድረኮች ላይ በሚሳተፉበት ወቅት ከሰዎች ጋር በማውራትና ሁኔታውን በመንገር ድጋፍ እንደሚያገኙ ይጠቁማሉ:: አንዳንድ ግለሰቦች ደግሞ በራሳቸው ወጪ የአንድ ቀን የምገባ ወጪ እንደሚሸፍኑ ይናገራሉ:: ከዚህም ባለፈ የአርባ መታሰቢያ፣ የድግስ ፕሮግራም ሲኖር እሳቸው ለሚመግቧቸው ልጆች የሚሆን እገዛ ያገኛሉ:: ይህን ስራ ከጀመሩ አምስት አመት የሆናቸው ሲሆን ለምገባው ገንዘብ መሰብሰበ ፈታኝ ሁኔታዎችን ማለፍ እንደሚጠይቅ ይናገራሉ:: ቀደም ብለው ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች እራሳቸው አስበው ቃል የገቡትን ካልሰጡ ሌሎች ሰዎችን እንደሚጠይቁ ይጠቅሳሉ:: በየጊዜው እየደወሉ ሰዉ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቅ አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ አበበች፤ በዚህም የተረጂዎችን ቁጥር ለመቀነስ ተገደዋል::
ወይዘሮ አበበች በግላቸው ተነሳሽ የሚሰሩት የበጎ ስራ በግለሰብ ደረጃ ተቀባይነት እንደሌለው ይናገራሉ:: አንዳንድ ሰው ሀሳቡን በመደገፍ የሚያበረታታ ቢሆንም የተወሰኑ ሰዎች ‹‹ለምን ከነዚህ ጋር ትለፊያለሽ፣ ነገ ተምልሰው እዚሁ ለሚሆኑት›› የሚል አስተያየት ይሰጣሉ:: በመንግስት ደረጃ በሚኖሩበት ወረዳ ላይ እገዛ ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ:: ነገር ግን ስራውን ከወረዳም ጋር ተባብሮ ለመስራት እጅግ ከባድ እንደሚሆን ያመለክታሉ:: ሁሉንም ሰው አሳምኖ ወደ ስራ መግባት እራሱን የቻለ ከባድ ነገር ሆኖባቸዋል፡: በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆችን ህብረተሰቡ ገና እንዳልተረዳቸው የሚጠቅሱት ወይዘሮ አበበች፤ በመንግስት ደረጃ የሚኖሩበት ወረዳ ስራውን እንዲሰሩ ቢያበረታታቸውም ሁኔታው ከባድ እንደሆነ ይጠቁማሉ:: ሁሉም በወረዳ ደረጃ በመከፋፈል ስራውን መስራት ካልተቻለ በስተቀር ስራው አስቸጋሪ ነው:: እሳቸው የሚሰሩትን ስራ የሚኖሩበት ወረዳ ተረድቶ ተቀባይነት ያገኘላቸው ሲሆን ለሌሎች ወረዳዎችን ምሳሌ ሆነው መቅረብ እንደሚችሉ ተገልፆላቸዋል::
ወይዘሮ አበበች በጎዳና ላይ የሚገኙ ልጆችን ከማብላት በዘለለ ወደ ቤተሰቦቻቸው የመሸኘት ስራም ያከናውኑ ነበር:: በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በየቀኑ ምሳ የማብላት ስራ ያከናውኑ የነበረ ሲሆን ለዚህ ምክንያቱ በወቅቱ ምግብ ቤቶች ስራ የቀነሱበት ወቅት በመሆኑና ልጆቹ የሚመገቡት አለማግኘታቸው ነበር:: የኮቪድ ወረርሽኝ በቀነሰበት ወቅት በጎዳና የሚገኙ ልጆችን ወደ ቤተሰቦቻቸው የመሸኘት ስራ አከናውነዋል:: ሃያ በጎዳና የሚኖሩ ልጆችን ወደ አገራቸው የሸኙ ሲሆን ሁለት ሲመለሱ የተቀሩት 18 ልጆች ቤተሰቦቻቸው ጋር እየኖሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል:: ልጆቹም ትምህርት ጀምረውና ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ:: ስራው በዚህ መልክ መቀጠል ከተቻለ ብዙ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ያስረዳሉ፡፡
በአቅም እጥረት ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ የነበረባቸው ልጆች ሊመለሱ አለመቻላቸውን የሚጠቅሱት ወይዘሮ አበበች፤ የትራንስፖርትን ጨምሮ የልብስና ሌሎች ወጪዎች ስለሚያስፈልጉ አቅም ቢኖር ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚሸኙ ልጆች በእጃቸው እንዳሉ ይጠቁማሉ:: ይህን ስራ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት የነበረባቸው የመንግስት አካላት ቢሆኑም ሁሉም ህብረተሰብ እገዛ ሊያደርግ ይገባል ባይ ናቸው::
ባለሀብቱም ሆነ ህብረተሰቡ በየአካባቢው ተደራጅቶ ሊንቀሳቀስ ይገባል:: በአዲስ አበባ ውስጥ እርዳታ ፈላጊ ህፃናት በብዛት ይገኛሉ:: እነዚህ በየጎዳናው መብራትና በመንገድ አካፋይ የሚገኙት ቤተሰብ ያላቸው ናቸው:: በልጆቹ ወላጆች ላይ መስራት ከተቻለ ሁኔታው ሊቀንስ እንደሚችል ይጠቅሳሉ:: ወላጆች ላይ መስራት ካልተቻለ በጎዳና የሚኖሩ ልጆች ቁጥር በቀጣይ ሊጨምር ይችላል:: ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ የሚገኙ በጎዳና የሚኖሩ ልጆች ሁኔታም በመንግስት ደረጃ ቢሰራበት በጎዳና ላይ የሚኖሩት ልጆች እየቀነሱ ይመጣሉ የሚል እምነት አላቸው::
ነሀሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ በጎዳና ይገኙ ከነበሩ ወጣቶች ጋር ውይይት የተደረገበት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር:: ወጣቶቹ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት የምግብ ማብላት ስራ ይከናወንላቸው የነበሩ ናቸው:: መንግስት ወደ ስራ እንዲገቡ ባደረገው ጥሪ ወደ ወረዳ በመውሰድ ስራ እንዲያገኙ ተደረጉ:: ወጣቶቹ በካርቶን ስራ ተደራጅተው በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ናቸው:: እነዚህ ወጣቶች እኛም ለአገራችን መቆም እንፈልጋለን በማለት የደም ልገሳ መርሀ ግብር እንዲዘጋጅ መደረጉን ወይዘሮ አበበች ያመለክታሉ:: ስራውም በጥሩ መልኩ ተካሂዷል::
የደም ልገሳ በተከናወነበት ወቅት ደም ባንክ ከፍተኛ ትብብር አድርጎላቸዋል:: በተለይ ልጆቹ ከጎዳና ላይ ተነስተው እራሳቸውን የቻሉ በመሆናቸው የተወሰነ ጥርጣሬ ነበር:: እሳቸው ግን በልጆቹ ሙሉ እምነት ስላላቸው ደም ልገሳው እንዲከናወን አድርገዋል::
ከሚኖሩበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት አስተዳደር ጋር በመተባበር ለማንኛውም ስራ ደብዳቤ እየተፃፈላቸው ይንቀሳቀሳሉ:: ከቀይ መስቀል በጎዳና ለሚገኙ ልጆች አልባሳት ለማግኘት ወረዳው ደብዳቤ ጽፎላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ:: በተገኘውም ድጋፍ ልጆቹን የማልበስ ስራ ተሰርቷል:: የብርድ ልብስም ድጋፍ እንደተደረገላቸው ያስታውሳሉ:: ከዚህ በመቀጠል በሚኖሩበት ወረዳ የእሳት አደጋ ለገጠማቸው ቤተሰቦች ቀይ መስቀል የአልባሳት ድጋፍ በእሳቸው በኩል አድርጓል:: ሌላው ደግሞ በጎዳና የሚኖር ልጅ ታሞ የካቲት 12 ሆስፒታል ሙሉ ህክምና በነጻ እንዲሆን እንደተባበራቸው ይገልጻሉ:: ልጁ ከነበረበት ህመም እንዲያገግም ተደርጎ ማዘር ትሬዛ ማቆያ ውስጥ ተኝቶ እየታከመ ነው:: የልጁን ህክምና በብዛት ውዳሴ ዲያጎኒስቲክ ሆስፒታል ትብብር አድርጓል::
ከአንድ አመት በፊት የጎዳና ልጆችን ወደ ቤተሰቦቻቸው ከሸኙ በሶስተኛው ቀን ከለሊቱ ስምንት ሰዓት የእጅ ስልካቸው ላይ ተደወለ:: ስልካቸው ላይ የደወሉላቸው በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ነበሩ:: ልጆቹ የደወሉበትም ምክንያት በተኙበት የመኪና አደጋ ደርሶ የአንድ ልጅ ህይወት ማለፉን የሰሙበት ወቅት ስራውን ከጀመሩ ያዘኑበት ቀን መሆኑን ይናገራሉ:: በቀጣይ ወይዘሮ አበበች የበጎ አድራጎት ማህበር ለመመስረት እቅድ ያላቸው ሲሆን በሚኖሩበት ወረዳ ውስጥ በጎዳና ላይ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በየቤቱ የሚገኙ ችግረኞችን ለመደገፍ ሀሳብ አላቸው:: በተጨማሪም አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍና ቤት ለቤት ክትትል ለማድረግ አላማ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ነው::
‹‹በመጨረሻ ማለት የምፈልገውና አያይዤ የማስተላልፈው ሐሳብ ምንድን ነው፤ የሰው ልጅ እያንዳንዱ የተፈጠረለትና የሚኖርለት ዓላማ አለው። በየአንዳንዱ ሰው ሐሳብ፣ ልብና አእምሮ ውስጥ ሕልም አለ። እነዚህ ጎዳና ላይ እየኖሩ የምናያቸው በተለይ ወጣቶችና ልጆችም ሕልም አላቸው። ሰው ምቹ አልጋ እያለው ጠጠር ላይ እንደማይተኛ ሁሉ፣ ማንም ሰው ፈልጎ ጎዳና አይወጣም። ከዛ ይልቅ በእነዛ ልጆች ውስጥ የፈረሰ ቤተሰብ፣ ያልበረታና የተዘነጋ ማኅበረሰብ፣ ቸል ያለ የአስተዳደር ስርዓት እንመለከታለን። አገር የሚሠራው ደግሞ በእነዚህ ሁሉ ድምር ነው።›› ይላሉ።
ወይዘሮ አበበች ያለፈውን መጠገን ባይቻል እንኳን መጪው በሁሉም እጅ ነው ያለው ብለው ያምናሉ። ‹‹መተጋገዙ ይጠናከር፣ በተለይ በጎዳና የሚኖሩ ልጆችን ካሉበት ለማውጣት በሚደረጉ ጥረቶች እንሳተፍ። ነቅተንም ልጆቻችንን እንከታተል፤ እንጠብቅ። እነዚህ ልጆች ዋጋ አላቸው፤ የሚሰጡትም አላቸው። ቅድም እንዳነሳሁት፤ በቀደም ማለትም ነሐሴ 29 በነበረው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይ ደም ለግሰዋል። ደም ትልቅ ስጦታ ነው። እነዚህ ልጆች ትልቁን ስጦታ ነው የሰጡት። ብዙ የተደረገላቸው ሆነው ግን አይደለም። የመቄዶንያው ቢንያም እንደሚለው ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ስለሆነ ነው። እናም ለእነዚህ ልጆች እድል እንስጣቸው ማለት እወዳለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል።
እንደሚታወቀው ደግሞ አሁን አገሪቱ ከባድ ችግር ውስጥ ያለችበት ጊዜ ነው። ሁሉም እሳቱን ለማጥፋት የውሃ ባሊ መሸከም ባይችል ወይም መሸከም ላይኖርበት ይችላል። አገሪቱ ይህን አልፋ እንደምትቀጥል በተስፋ በመጠበቅ ሁሉም የድርሻውን እየሠራ መቆየት እንዳለበት ይናገራሉ። ‹‹አይ፣ በቃ ጨልሟል ተብሎ የያዙትን ሻማ ማጥፋት ትክክል አይደለም፤ ያንን ብርሃን ማስተላለፍና ፀሐይ እስክትወጣ መጠበቅ አለብን›› ይላሉ። ለአገር ተሰራ ማለት የምንችለው ለሰው/ለተቸገረ ወገን ስንደርስና ስንተጋገዝ ነው። ኢትዮጵያ በተቀበለችው አዲሱ ዓመት ማንኛውም ሰው በጎዳና ላይ የሚገኙ ልጆችን ከመሸሽና ከማባረር በመቆጠብ የአቅሙን እንዲያደርግ ጥሪ ያቀርባሉ:: ማንኛውም ሰው ፈቅዶ ጎዳና ላይ አይወጣም የሚሉት ወይዘሮ አበበች፤ ማንም ሰው ወደዚህ ህይወት ሊገባ ይችላል:: ስለዚህ ማንኛውም ሰው ካለው ላይ በማካፈል በጎዳና ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሊታደግ እንደሚገባ ያሳስባሉ::
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም