ሳዋ ሳዋ ሳዋሌ….አንድ ሰሞን ይህን ዘፈን ያልሰማ እና ወዝወዝ ያላለበት ሰው አይገኝም:: በተለይ አዲስ አበባ ሙዚቃው በወጣ ሰሞን በዚህ አፍሪካዊ ምት ያለው ሙዚቃ ስትደንስ ከርማለች:: በአጭሩ ሙዚቃው በወጣበት ሰሞን የኢትዮጵያን የሙዘቃ ሰንጠረዥ ራስጌ ተቆጣጥሮ ለሳምንታት የሙዚቃ አድማጩ ቁጥር 1 ተመራጭ ነበር:: የሙዚቃው ባለቤት ደግሞ በመድረክ ስሙ ዚጊ ዛጋ በመታወቂያ ስሙ ደግሞ ዚጊ ታፈሰ ነው:: የዛሬው የዝነኞች የእረፍት ውሎ ቆይታችን ከእርሱ ጋር ይሆናል፡፡
የተወለደው መሀል አዲስ አበባ ጨርቆስ አካባቢ ነው:: ወቅቱም በ1982 ዓ.ም:: እናቱ ወ/ሮ አሰለፈች መኮንን እና አባቱ አቶ ታፈሰ ከወለዷቸው 6 ልጆች 5ኛ ነበር:: በወቅቱ 4ኛ ክፍለ ጦር ማእከሉ እዚያ የነበረ ሲሆን ቤተሰቡ የወታደር ቤተሰብ በመሆኑ እሱም የተወለደው እዚያው ነበር:: አባቱ እሱ ገና የ5 አመት ልጅ እያለ በመሞታቸው እድገቱ ከአያቱ ጋር ሆነ:: እድሜው ከፍ ብሎ ለትምህርት ሲደርስም ጠመንጃ ያዥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ ፊደልን ቆጠረ:: ሁለተኛ ደረጃውን ደግሞ ሽመልስ ሀብቴ ተማረ፡፡
አባቱ ትራምፔት በመጫወት ቤተሰቡን ከሙዚቃ ጋር ያስተዋወቁ ሲሆን እናትን ሳይጨምር መላው ቤተሰቡም ለሙዚቃ ፍቅር ያለው ነበር:: በዚህም ቤተሰባዊ ሙዘቃ ዝንባሌ የተነሳ ትምህርት ቤት ውስጥ ዚጊ በሙዚቃው በኩል በክበባት ንቁ ተሳታፊ ነበር:: ሰፈር ውስጥ ለሙዚቃ የሚሆን አጋጣሚ በተፈጠረ ቁጥርም በታላላቆቹ ትእዛዝ ሙዚቃውን እና ዳንሱን ያቀርብ ነበር:: ከትምህርት ቤት የሚኒ ሚዲያ ክበብ በተጨማሪም በቀበሌ ኪነት በቤተሰብ መምሪያ የሙዚቃ ቡደን ተሰጥኦውን ማዳበርም ቀጠለ፡፡
የመጀመሪያ መድረኩ እዚያው ጨርቆስ አካባቢ የሚገኘው ታምሩ ቤት የሚባል ክበብ ነበር:: ይህ ቤት አንድ አስቂኝ ገጠመኝ አለው፡፡”አንድ ቀን እየዘፈንኩ አንድ ሰው ወደ መድረክ መጥቶ በርታ ብሎ በእጄ የሆነ ነገር አስጨበጠኝ:: እኔም ያው ብር ነው ብዬ ኪሴ ውስጥ ከተትኩት:: ከዚያ ከመድረክ ስወርድ ወደ ጓሮ ሄጄ አውጥቼ ሳየው ሰኔ ጎልጎታ ነው:: (ሳቅ) ከዚያ ሌላ ቀን ሳገኘው ያው ብር እንደምትጠብቅ አውቃለሁ ግን ብር ስለጨረስኩ ነው ያለኝን የሸለምኩህ አለኝ:: ስቄ ችግር የለውም አልኩት” ይላል፡፡
ከዚያ መድረክ በኋላ ዚጊ በርካታ መድረኮችን በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሰራ ሲሆን በተለይ ግን በጣም የሚደሰተው እና ኩራት የሚሰማው በታሪካዊው ቡፌ ደላጋር በመስራቱ ነው:: እንደ አለማየሁ እሸቴ ፤ መሀሙድ አህመድ እና ቴዲ አፍሮን የመሳሰሉ ታላላቅ አርቲስቶች በሰሩበት በዚያ መድረክ በመስራቱ ደስታ እንደሚሰማው ይናገራል:: ከመድረክ ስራ በኋላ ወደ ስቱዲዮ ጎራ ሲል የሰራው የመጀመሪያ ነጠላ ዜማው በ1999 ዓ.ም ገደማ የሰራው እና ከአድማጭ ጋር ያስተዋወቀው ቀኑዬ የተሰኘ ሙዚቃ ነው::
ከቀኑዬ የጀመረው ነጠላ ዜማ 15 ገደማ ነጠላ ዜማዎችን ሰርቷል:: ከነዚህም መሀከል ተወዳጁ ሳዋ ሳዋሌ ፤ ሌላኛው ብዙ ተደማጭነት ያገኘለት ሙዚቃው ጅሎ ፤ ቢ ሲማ ሀያ ፤ ሎኦና እና ባለፈው ሳምንት ያወጣው እሷ ላይ ፈዞ ይገኙበታል:: አንዳንዶቹ ነጠላ ዜማዎች ለብቻው የሰራው ሲሆን አንዳንዶቹን ደግሞ እንደ ቴዲ ዮ እና አበበ ከፈኒ ካሉ ድምጻውያን ጋር በጋራ በመሆን የሰራው ነው፡፡
የዚጊ የመጀመሪያ አልበም ነቃ በል ባርዬ የሚባል ሲሆን ወቅቱም 1999 ገደማ ነው:: ከዚያ በኋላ ኮርማ የተሰኘ አልበምም አውጥቷል፡፡”ኮርማ ማለት በኦሮምኛ ጀግና ማለት ነው:: ጃንሆይ ለአበበ ቢቂላ ከድል ሲመለስ የሰጡት ስም ነው፡፡”በማለት የአልበሙን ስያሜ ያብራራል:: በቀጣይ አመት አጋማሽ ላይ አዲስ አልበም ለማውጣት ዝግጅት እያደረገ እንደሆነም
ይገልጻል፡፡”አልበም መከበሪያ ነው:: የአንድ ድምጻዊ ብቃትም የሚታየው በአልበም ነው” ይላል:: በነጠላ ዜማ በኩልም በቀጣይ አመት ለህዝብ የሚደርሱ ከዝነኛው ድምጻዊ ጌቴ አንለይ እንዲሁም ከተወዳጇ አርቲስት ማሪቱ ለገሰ ጋር በመሆን የተሰሩ ሙዚቃዎች እንዳሉት ነግሮናል:: ለራሱ ከሚሰራው ባለፈ የጃኖ ባንድ አባል ለነበረችው ሄዋን ገ/ወልድ ፤ በቅርቡ ከአብዱ ኪያር ጋር ወዬ ወዬ የሚል ነጠላ ዜማ ላወጣችው ሜላት ቀለመወርቅ ፤ ከየኛ ሚዘቃ ቡድን አባላት መሀከል አንዷ ለነበረችው ለምለም ሀይለሚካኤል እና ሌሎችም ዜማ መስጠቱን ነግሮናል::
በግላዊ ህይወቱ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት እንደሆነ የሚናገረው ዚጊ ኤልዳና እና ፌዝ የተባሉ ሁለት ልጆች አሉኝም ይላል:: በሳምንት ውስጥ በርከት ያለውን ቀን በስቱዲዮ እና በምሽት ክበቦች ባለው ስራ የሚያሳልፈው ዚጊ ለማህበራዊ ኑሮም እንዲሁ አይሰንፍም:: በተለይ ከኦቲዝም ጋር በተያያዘ ንቁ ተሳታፊ ነው:: ለዚጊ ሙዚቃ ከሙያም በላይ ሲሆን ምናልባትም ሙዚቃ ባይኖር ህይወቱ እንዲህ የተቃና ሊሆን እንደማይችል ያምናል:: ”የህዝብ ፍቅር አፍርቻለሁ ከዚያም ባለፈ አሁን የምኖረውን ቆንጆ ህይወት ያገኘሁት በሙዚቃ ነው” ይላል:: በሙዚቃ አውሮፓን ፤ አውስትራሊያን እና መካከለኛው ምስራቅን እንዳካለለም ይገልጻል፡፡
ሙዚቃን በተመለከተ ቀጣይ አላማው ከኢትዮጵያ ውጭም ተደማጭ የሆኑ ሙዚቃዎችን መስራት ሲሆን ለዚህም ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ይገልጻል:: ”የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የሚገናኝበት ድልድይ የለውም:: ያን ድልድይ እኛ መስራት አለብን:: ”የሚለው ዚጊ በቀጣይ በራሳችን ቋንቋ ለሌሎችም ቋንቋችንን ለማይሰሙ ህዝቦች የሚመጥን ስራ ለመስራት እየሞከረ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
የእረፍት ቀንህን እንዴት ነው የምታሳልፈው አልነው:: ”ብዙውን ጊዜ የእረፍት ቀኔን የማሳልፈው ቤቴ ነው:: ከዚያ ውጪም የምዝናናው ከጓደኞቼ ጋር ነው:: ግን ለመዝናናት ብዬ ክለብ ምናምን አልሄድም:: እሱ ብዙም አይመቸኝም” ይላል:: አክሎም ”ቤት በምሆንበት ሰአት ፊልም ማየት እወዳለሁ:: ከስፖርት ለቦክስ ፍቀር አለኝ:: ድሮ በልጅነቴ ወንድሜ ቦክስ ያለበት ቦታ ይዞኝ ይሄድ ስለነበር ለቦክስ ስሜት አለኝ:: ምናልባትም ሙዚቀኛ ባልሆን ቦክሰኛ ልሆን እችል ነበር” ይላል:: ዋነኛ መዝናኛው ግን ስቱዲዮ ውስጥ ሆኖ አዲስ ሙዚቃ ለመፍጠር የሚያደርገው ትግል እንደሆነ ይናገራል፡፡
ለዚጊ ዋነኛው ቀጣይ አላማው ከኢትዮጵያ አልፈው የሚደመጡ ሙዚቃዎችን መስራት ነው:: ኮርማ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ የኢትዮጵያን የዜማ ቅኝት ከማሊ ቅኝት ጋር በማዋሀድ ሙዚቃ መስራቱን የሚገልጸው ዚጊ በቀጣይ ከወራት በኋላ በሚወጣው አልበሙ ላይ ይህን ሙከራውን አጠናክሮ ለመቀጠል ማቀዱን ገልጾልናል:: ለመላው አድናቂዎቹ እና የጋዜጣችን አንባቢዎችም አዲሱ አመት የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጧል፡፡
(አቤል ገ/ኪዳን)