ለኪነ ጥበብ በልክ የተሰፋች ናት ይሏታል። ደራሲም ናት። ምንም እንኳን የግጥም መድብሏ የታተመው እሷ ካረፈች በኋላ ቢሆንም ግሩም የግጥም አዘጋጅ እንደነበረችም ይነገርላታል። ደግሞም በመረዋ ድምጿ በርካታ መጽሀፍትን በትረካ ሕይወት ዘርታባቸዋለች። የቅርብ ወዳጆቿና ጓደኞቿ በቁልምጫ ባዩ ይሏታል። ቲያትረኛ፣ ገጣሚ፣ ተዋናይ፣ አዘጋጅና ተራኪ አርቲስት ባዩሽ አለማየሁ።
አርቲስት ባዩሽ አለማየሁ ጥበብን የተቀበለችው ከአባቷ ይመስላል። ወላጅ አባቷ እውቁ የትርጉም ባለሙያ መስፍን አለማየሁ ነው። ተርጓሚ፣ ደራሲና ኃያሲም ነው። በተለይ የሼክስፒርን ድርሰቶችና የሩሲያ ድርሰቶችን በግሩም ሁኔታ በመተርጎም ይታወቃል። ካፖርቱና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች፣ የመጨረሻዋ ቅጠልና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች፣ ባህሩና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች በመጽሀፍ ካሳተማቸው ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የአባቷ አባት አቶ አለማየሁ ጠይቃቸው ቤታቸው በልጆች ድምቀት ቢሞላም የአይን ማረፊያ የምትሆን ሴት ልጅ በማጣታቸው ሁሌ ሴት ልጅ ይመኙ ነበር። ግራ ቢገባቸው በየቤተክርስቲያኑ ሌሎች በሥለት ልጅ ተሰጠን ሲሉ ቢሰሙ ባለቤታቸውን እስቲ ሴት ልጅ እንዲሰጠን ተሳይ እስከ ማለት የደረሰ የሴት ልጅ ፍቅር ነበረባቸው። ይህን የባለቤታቸውን የሴት ልጅ ፍቅር የሚያውቁት ሴት አያቷ ወይዘሮ ፈሰስወርቅ ኃይሌ ባለቤታቸው ካረፉ በኋላ የተገኘች የልጅ ልጃቸውን “ምነው አለማየሁ ቢያይሽ ኖሮ” ሲሉ ባዩሽ አለማየሁ የሚል ሥም አወጡላት።
በ1969 በአዲስ አበባ ፒያሳ የተወለደችው ባዩሽ፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በመድኃኒአለም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች። ቤተሰቦቿ መክሊቷን ለመረዳት ጊዜ እንዳልፈጀባት እማኞች ናቸው። ከልጅነቷ ጀምሮ ታነባለች፤ እጇን ከወረቀት አገናኝታ ለመጻፍ እድሚዋ ከፍ እስኪል አልጠበቀችም። ትያትር ቤት ከመቀጠሯ አስቀድሞም በአማተርነቷ በርካታ የጥበብ ሥራዎችን ሠርታለች። “ሰቀቀን”፣ “የፍቅር ዜማ”፣ “እቡይ ደቀመዝሙር”፣ “የክፉ ቀን ደራሽ”፣ “የሁለት ቤት ድግስ”፣”የፌዝ ዶክተር”፣ “ማን ይንገራት?” የተሰኙ ትያትሮችን ከእውቅ ተዋናዮች ጋር የመተወን አጋጣሚን ያገኘቸው ገና በለጋ እድሜዋ ነበር።
በአማተርነቷ ዘመን ከትያትር ትወናዋ ባሻገር የሬድዮ ድራማዎችንም ትሰራ ነበር። በመላኩ አሻግሬ ከሚመራው ቴዎድሮስ የትያትር ቡድን ጋር “አንድ ጡት” እና “ማሪኝ” የተሰኙ ተውኔቶችን በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል በመዘዋወር አሳይታለች።
1990 ዓ.ም “አድጌበታለሁ የደስታ ጊዜያቶችን እንዲሁም ሐዘኔን አልፌበታለሁ” የምትለውና ረዥም ጊዜ የሠራችበትን የሀገር ፍቅር ትያትር ቤት የተቀላቀለችበት ዓመት ነበር። በሀገር ፍቅር ቆይታዋም “የጣር ሳቅ”፣ “ጥንድ መንገደኞች”፣ “ጣውንቶቹ”፣ “የቀትር ጥላ”፣ “ሰማያዊ አይን”፣ “ረመጥ”፣ “ትዳር ሲታጠን”፣ “የብዕር ሥም”፣ “የጉድ ቀን”፣ “አሉ” እና ሌሎችም ትያትሮች ላይ በመሪ ተዋናይነት ተውናለች። ትያትር በመጻፍ ለትያትር በልኩ የተሰፋች መሆኗን አስመስክራለች።
በአንድ ወቅት “ሰማያዊ አይን”ና “ረመጥ” የተሰኙ ሁለት ትያትሮችን የዋና ገጸባህሪን ተላብሳ ያለምንም እረፍት በተከታታይ ተጫውታለች። የሼክስፒር ድርሰት የሆነውንና በአባቷ የተተረጎመው “የቬኑሱ ነጋዴ” ትያትር ላይ የሴትንም የወንድንም ገጸ-ባህሪ ተላብሳ ተውናለች። በትያትሩ ላይ መጀመሪያ ከምትጫወታት የሴት ገጸ-ባህሪ ወደ ወንድ ጠበቃነት ስትቀየር በአለባበስና በገጽ ቅብ ብቻ ሳይሆን ከድምጿ አንስቶ በሁለንተናዋ ታዳሚ ወንድ መሆኗን አሳምና አስደምማለች።
የሙያ ባልደረቦቿ ባዩሽ ከራሷ በላይ ለኪነጥበብ ከበቂ በላይ የተገዛች መሆኗን ይመሰክራሉ። ለዚህ በርካታ ማሳያዎች ቢኖሩም አንዱ ማሳያ የተከሰተው ሀገር ፍቅርን ተቀላቅላ ብዙም ሳትቆይ ነበር። የኪነጥበብ ሰው በዓልን ከሕዝብ ጋር ማሳለፍ እንግዳው አይደለምና እሷም በፋሲካ ዋዜማ ምሳዋን በልታ በወቅቱ ትተውንበት የነበረው “የጣር ሳቅ” ትያትር ላይ ለመተወን ጉዞ ወደ ትያትር ቤቱ። የትያትር ቤቱ በር ከርቀት ይታያል፤ በርካታ ሰዎች ከትያትር ቤቱ አቅጣጫ ወደእሷ በሩጫ ሲመጡ ብታይም መንገድ ላይ የሚሸጡትን ሰዎች ደንብ አስከባሪዎች እያባረሯቸው ነው ብላ ስላሰበች ሰዉ ወደሚሸሽበት አቅጣጫ ጉዞዋን ቀጠለች። በዚህ መሃል ፊት ለፊት ሰው ሁሉ ፈርቶ ሲሸሸው ከነበረው የደነበረ በሬ ጋር ስትፋጠጥና በሬው በቀንዱ ወደ መሬት ሲቀላቅላት እኩል ሆነ።
መጎዳቷን ያዩና በተዋናይነቷ የሚያውቋት ሰዎች አንስተው ወደ ትያትር ቤት ወሰዷት። የወቅቱ የትያትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ “ወደሆስፒታል ሄደሽ ታከሚ ትያትሩን ሊያይ የመጣን ታዳሚ ይቅርታ ጠይቀን ለሳምንት እንቀጥራለን” የሚል ሀሳብ ቢያመጣም ባዩሽ ግን ልትስማማ አልቻለችም። ይልቁንስ ከህክምና መልስ ትያትሩን እንደምትሰራ ተናገረች። ይቅርብሽ ብትባልም ሞያውን አክብሮ ቀኑን ሰውቶ ረዥም ሰልፍ ይዞ የጠበቀን የትያትር ተመልካች አክብራ ከህመሟ ጋር ታግላ ለመስራት ወሰነች። ራስ ደስታ ሆስፒታል ተወስዳ ቁስሏ ታሽጎ ቁስሏን በሻሽ ሸፍና ተወነች።
አብረዋት የሠሩ ተዋናዮችና አዘጋጆች ገና የትያትር ልምምድ ሲጀመር ከሌሎቹ ቀድማ ገጸ-ባህሪዋን በመረዳት ይጠቅሷታል። እራሷ ከምትደርሳቸው ተውኔቶች ባሻገር የሌሎች ድርሰቶችንም ያልመሰላት ነገር ሲገጥማት እንዲህ ቢሆንስ በሚል ደራሲውን በማስፈቀድ ድርሰትን በማቃናት ትታወቃለች። አርቲስት ኪሮስ ኃይለሥላሴ የተውኔት ዝግጅት ላይ ቃለተውኔትን በማረም ጎበዝ እንደነበረች ያስታውሳል። ታዲያ ያኔ በማናለብኝነት እና እኔ አውቃለሁ ተሳስታችኋል ሳይሆን “ይህ እንዲህ ቢሆንስ” ማለት የሷ መለያ ነው። ለተወሰነ ጊዜ ከሀገር በመውጣቷና ወደ ጀርመን በማምራቷ ከትያትር አፍቃሪያን እሷም ከምትወደው መድረክ ተራርቃ ቆይታ ነበር። ሆኖም ከሀገሯም ከምትወደው የትያትር መድረክም ተለይታ መቆየት አልቻለችምና ወደ ሀገሯ ተመለሰች።ወደ ሀገሯ ተመልሳ ሰማያዊ ዓይን፣ ሰዓት እላፊ፣ ነቃሽ፣ አሉ በተሰኙ ትያትሮች በመተወን ወደ መድረክ ተመልሳለች።
ከጀርመን መልስ እሷ የተወነችባቸው ሰማያዊ አይን፣ ነቃሽና ሰዓት እላፊን ያዘጋጀው ተፈራ ወርቁ በዚህ የዝግጅት ጊዜ ባዩሽ ምን ያህል አዘጋጅን የምታግዝ መሆኗን ማየቱን ጠቅሷል። የማይመስላት ነገር ሲኖር ሰው ፊት የማትናገር የሞያ ሥነ-ምግባር ያላት መሆኗን ከፋና ቲቪ ጋር በነበረው ቆይታ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ባዩሽ ዋነኛ መታወቂያዋ የመድረክ ትያትር ቢሆንም በቴሌቭዥንና በሬድዮ ድራማም፣ በፊልምም ሆነ በማስታወቂያዎች በመተወን ብቃቷን አሳይታለች። “ንስር”፣ “ፍለጋ”፣ “ስደት” የተሰኙት ፊልሞች ላይ ብቃቷን ያስመሰከረች ሲሆን፤ በተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ “አልተገናኝቶም”፣ “የማለዳ ጤዛ”፣ “አሳንሰር”፣ “አቋራጩ”፣ “አስታራቂ”፣ “ሻሞ”፣ “ሔዋን”፣ “እጣ”፣ “አዲስ ድባብ” ተጠቃሽ ናቸው። በሬድዮ ድራማ “መንታ መንገድ”፣ “የተከፋፈሉ ልቦች”፣ “የተዳፈነ ልብ”፣ “ጽናት”፣ “መስዋዕት”፣ “የሙት ልጅ”፣ “ወፌ ቆመች” ባዩሽ በድንቅ ብቃት የተወነችባቸው የሬድዮ ድራማ ርዕሶች ናቸው።
ባዩሽ ከመድረክ ጀርባ ስትታይ አጠር ብላ መድረክ የምትሞላ አትመስልም። ይህ ግምት ግን መድረኩ ላይ ስትወጣ እውነታው ሌላ ሆኖ ቁጭ ይላል። እሷ መድረክ ላይ ስትወጣ አጭር ቁመቷ ረዝሞ ቀጠን ያለው አካሏ ወፍሮ መድረኩን ትሞላዋለች። የሚያውቋት ከራሷ በላይ ሥራዋን የምታከብር ይሏታል። ይሄም በሥራዎቿ እንደሚታይ ምስክር ናቸው። ገጸባህሪን ቀድሞ በመረዳት የሚደርስባት የለም፤ ለትያትር ልምምድ ሲጀመር እሷ ገጸባህሪዋን ተረድታ በሚገርም ብቃት ለመተወን አፍታም አይፈጅባት። ታዲያ ይሄንን የተረዱ አብረዋት የሚተውኑ ከአዘጋጁም አልፈው አብረን እንለማመድ ብለው የሙጥኝ ይሏት ነበር።
የሷ ትወና ሙሉ ነውና አብሯት የሚተውነው ተዋናይ አብረዋት እንዲሞሉ ታደርጋለች። እሷ ስትተውን የተጻፈ ስክሪብት የምትሰራ ሳይሆን የዕለት ከዕለት ሕይወቷን የምትኖር እንዲመስል አድርጋ ከራሷ ጋር ታዋህደዋለች። አብረዋት የሰሩ ተዋንያንም ሆኑ አዘጋጆች የራሷን ሥራ ቤቷ ጨርሳ እንደምትመጣ ይመሰክራሉ። ከራሷም ተርፋ ሌሌች ተዋናያን እንድታለማምዳቸው ስለሚመርጧት የአዘጋጅን ሥራ በማቅለል ትታወቃለች።
አብሯት አምስት ትያትር የሰራውና የሀገር ፍቅር ሥራ አስኪያጅ የነበረው አብዱልከሪም ጀማል “እሷ ነዳጅ ነበረች፣ ጉልበት ናት፤ እሷ መድረክ ላይ ካለች እራሷን ብቻ ሳይሆን አጠገቧ ያሉትንም አብረዋት የሚሰሩትንም ሰዎች እንደ ኢነርጂ የምታነሳና ከፍ የምታደርግ የመድረክ ፈርጥ ነበረች!” ሲል ረዥም ጊዜ ባገለገለችበት ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት የእሷን ዕረፍት አስመልክቶ በተዘጋጀ የሽኝት መሰናድኦ ላይ ሀሳቡን ገልጿል።
ባዩሽ ተዋናይ፣ ደራሲ፣ አዘጋጅና ተራኪነትን አዳብሮ የቸራት ሁለገብ የጥበብ ሰው ነበረች። ከመድረክ ውጭ ሲያዩአት አጠር ደግሞም ቀጠንም ያለች ትመስላለች። የምትጫወተውን ገጸ ባህሪ ትልቅነት ለተረዳ ተመልካች እንዲያውም ያልተገባ ተዋናይ የተመረጠ ሁሉ ሊመስለው ይችላል። ግን ወደ መድረክ ስትወጣ ይሄ ሁሉ ይቀየራል። መድረኩን በግዝፈት ትሞላዋለች። “ገጽ ሁለት”፣ “ፎርፌ” እና “ረመጥ” የእርሷ ብዕር ውጤቶች ናቸው። በተለይ “ረመጥ” በ2008 ዓ.ም በተዘጋጀው የትያትር ፌስቲቫል ያሸለማትና በትወና ብቋቷም ሆነ በድርሰቷ በብዙዎች ዘንድ የምትታወስበት ሥራዋ ነው። ከጥበብ ሥራዋም በተጓዳኝ በነርሲንግ ትምህርት ተመርቃለች። በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት የሚዘጋጁ ትያትሮችን የህክምና ጉዳዮችን በውስጣቸው ከነበረ ደራሲዎችም ሆነ አዘጋጆች ባዩሽን ማማከር ምርጫቸው ነበር።
በሀገር ፍቅር የምትወደው ትያትር ልምምድ ላይ ነበረች። በመሃል ትንሽ አመመኝ በማለቷ የሥራ ባልደረቦቿ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ሸገር ክሊኒክ ወሰዷት። ለመታየት በሄደችበት ክሊኒክ አልጋ ትያዝ ተባለ። በክሊኒክ የተጀመረው ህክምና ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ተሸጋገረ። ቤተሰቦቿም ሆነ የሞያ አጋሮቿ ሕመሟ ለሞት ያደርሳል ብለው አላሰቡምና በበርካታ አድናቂዎቿ ዘንድ የመታመሟ ዜና ሳይደርስ ታህሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞተ ተለየች። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትያትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ለመውሰድ ለምርቃቷ ሽር ጉድ በምትልበት በ2013 ዓ.ም ሞት ቀደማት። የቀብር ስነ ስርዓቷም በቅድስት ስላሴ መንበረ ፀባኦት ካቴድራል ተፈፅሟል። አርቲስት ባዩሽ አለማየሁ በቲያትር ጥበብ ያላትን ልምድ ለማካፈልና ጥበቡን ከፍ ለማድረግ በምትችልብት እድሜዋ ብታልፍም የጥበብ ስራዎቿ ግን ዛሬም ህያው ናቸው።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም