ኢትዮጵያ ከዘመናዊ ስፖርቶች ጋር ከምዕተ ዓመት ያላነሰ ትውውቅ እንዳላት የተለያዩ የታሪክ ማህደሮች ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በብዙዎቹ ዘመናዊ ስፖርቶች አሁን የደረሰችበት ደረጃ አንገትን ቀና አድርጎ በኩራት የሚያስኬድ አይደለም። በአገራችን በርካቶቹ ዘመናዊ ስፖርቶች ረዘም ያለ ዓመት ያስቆጠሩ ቢሆንም ዓለማችን በስፖርቱ ከደረሰችበት ልዕለ ሃያል ደረጃ ለመድረስ ገና ብዙ መንገድ ይቀራቸዋል። እነዚህ ስፖርቶች በማህበርና በፌዴሬሽን ደረጃ ተዋቅረው ዘመናትን ቢሻገሩም በተለያዩ ምክንያቶች እድገታቸው ቁልቁል እንጂ ሽቅብ ሲጓዝ አይታይም። ከሃያ በላይ ዘመናዊ ስፖርት ፌዴሬሽንና ማህበራት የየራሳቸውን እንቅስቃሴ እያከናወኑ የሚገኝ ሲሆን በውጤትም ይሁን ወደ ህብረተሰቡ ዘልቀው በመስፋፋት ረገድ በጣት የሚቆጠሩት እንኳን ስኬታማ ናቸው ለማለት አያስደፍርም። አንገታችንን ቀና አድርገን በዓለም አቀፍ መድረክ እንድንሄድ የሚያደርገን ብቸኛው የአትሌቲክስ ስፖርትም ቢሆን ከነ ብዙ ችግሮቹ ውጤታማ ነው የሚባለው በግለሰቦች (አትሌቶች) የግል ጥረት ላይ ተንጠልጥሎ እንጂ እንደ አገር የተጠናከረ ስኬታማ ስራ ተሰርቶ ነው ለማለት አያስደፍርም።
የአገራችን ስፖርቶች በተለይም ካለፉት ሰላሳ ዓመታት ወዲህ ተጠናክረው ከመቀጠል ይልቅ ሲዳከሙና አንዳንዶቹም ከነጭራሹ የመጥፋት አደጋ ሲጋረጥባቸው እያስተዋልን ነው። በደርግ ዘመነ መንግስት የተለያዩ ስፖርቶች የተሻለ እንቅስቃሴ ይደረግባቸው እንደነበረና አገራችንም ከአትሌቲክስ ባሻገር በሌሎች ስፖርቶች እንደ አፍሪካም ቢሆን የተሻለ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደነበረች በጊዜው የነበሩ ስፖርተኞችና ባለሙያዎች አሁን ላይ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ለዚህም ጠንካራ የነበሩና ሰፊ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው ስፖርቶችን በክለብ ደረጃ የሚይዙ አራት ወይንም አምስት የስፖርት አይነቶችን ጨምረው በመያዝ ተደጋግፈው እንዲጓዙ የሚደረግበትን አሰራር ይጠቅሳሉ። ከዚህ ባሻገር በወታደሩ ክፍል ሰፊ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸውና አገርን በታላላቅ ደረጃ የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚደረገውም እንቅስቃሴ ከሰፊ ማህበረሰብ አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ ከሰላሳ ዓመታት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ስፖርት የተሻለ እንደነበር ይነገራል።
ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ በአገራችን በርካታ ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በጥሩም በመጥፎም ጎን እንደተፈጠሩ አይካድም። ወደ ስፖርቱ ስንመጣ ግን በስፖርቱ ዘርፍ በመልካም የሚነሱ ነገሮች ቢኖሩም መጥፎ ጎኖች ሚዛን የሚደፉ መሆናቸውን አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተን መናገር ይቻላል። ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ገደማ መንግስት ለስፖርቱ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቷል ማለት አይቻልም። ይህም በተለያዩ ምክንያቶች ሊገለፅ የሚችል ሲሆን ዋነኛው ስፖርትን ካለመረዳትና ትክክለኛውን አቅጣጫ ካለማወቅ ተደርጎ ሊነሳ ይችላል። ኢህአዴግ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ለስፖርቱ ትልቅ ትኩረት እንደሰጠ ተደርጎ በማሳያነት የሚጠቀሰው ከስፖርት መሰረተ ልማቶች ጋር በተያያዘ ነው። በእርግጥ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በየክልሉ በርካታ ዘመናዊ ስቴድየሞች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡም ነው። ይህ ብቻ ግን የአንድን ስፖርት ለማሳደግ በቂ አይደለም፣ የአንድ አገር ስፖርት እድገት መለኪያ ሊሆንም አይችልም። ስቴድየሞችን መገንባት መልካም ነገር ቢሆንም ስፖርቱ ህዝባዊነት እንዲኖረው ወርዶ ከመስራትና ከማስፋፋት አኳያ ሲቃኝ ከጋሪው ፈረሱ የቀደመ ይመስላል። በየመንደሩ የነበሩ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለህንፃ ግንባታ በማዋል ግዙፍና ዘመናዊ ስቴድየም መገንባት ብቻውን የአንድን አገር ስፖርት ሊያሳድግ እንደማይችል መገንዘብ ይቻላል። ይህ የሚያመለክተው መንግስት ስፖርትን ከመሰረተ ልማት ግንባታዎች ባሻገር ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ መመልከት እንዳለበት ነው።
በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ስፖርት ከቀደምት ጊዜያት በበለጠ በብዙ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትንና እውቅናን አትርፏል። የስፖርት ውድድር አይነቶችም በቁጥር እየጨመሩ እና በየትኛውም የእድሜ ክልል ላይ ያለን ሰው ሁሉ ትኩረት እየሳቡ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ትልቅ ዓለም አቀፋዊ የስፖርት ሁነቶች (mega sport events) ናቸው። ከነዚህ አይነት ውድድሮች ለምሳሌ የኦሊምፒክ ፣ የዓለም እግር ኳስ ጨዋታ ፣ የጋራ ሃብት ጨዋታዎች ይገኙበታል። የነዚህን አይነት ውድድሮች ለማዘጋጀትና ለማስተናገድ ብዙ ሃገሮች ወይም ከተሞች ፍላጎታቸው የላቀ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ትልቅ የስፖርት ሁነቶች ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረጅም ጊዜ ለማህበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ እድገት ጥቅም ስለሚያስገኙ እንዲሁም የገፅታ ግንባታ ላይ ጉልህ ሚናን ስለሚጫወቱ ነው።
ይሁን እንጅ እንዲህ ያሉ ትላልቅ የስፖርት ሁነቶችን ማዘጋጀት እጅግ በጣም ፈታኝ ሲሆን ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለደህንነት ስራዎች ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ ነው። ነገር ግን ለአዘጋጁ ከተማ ወይም አገር ትልቅ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ልማት አወንታዊ ተፅእኖ አለው። ከነዚህም ጠቀሜታዎቹ ውስጥ የምጣኔ ሃብት እድገት ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፣ ጤናማና ታታሪ ትውልድን ማፍራት ፣ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት መጨመር ፣ የስራ እድልን መፍጠርና የከተሞች መስፋፋት በዋናነት ሲጠቀሱ ስፖርት ለሰላም ያለው ፋይዳም በጉልህ የሚጠቀስ እውነታ ነው።
በዚህ ወቅት ቱሪዝም በዓለም አንዱና ትልቁ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ የምጣኔ ሃብት ሴክተር ሲሆን አጠቃላይ የዓለምን 10% GDP እና 1/10 የዓለምን ሰራተኛ የመቅጠር እምቅ ሃይል አለው። ለዚህ የስታቲስቲክስ አስተዋፅኦ ካደረጉት መካከል ደግሞ አንዱ የስፖርት ቱሪዝም ነው። ምክንያቱም ስፖርት የዓለማችን ትልቁ ማህበራዊ ክስተት ነውና። ሆኖም በስፖርት እና በቱሪዝም መካከል ያለው ግንኙነት ተመጋጋቢ በመሆኑ ፈጣን እምርታዊ ለውጥን አሳይቷል። የነዚህ ሁለት ኢንዱስትሪዎች ጥምረትም ዛሬ ላይ የስፖርት ቱሪዝምን ፈጥሯል።
የስፖርት ቱሪዝም ባለፉት አስርት ዓመታት እጅግ በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው። በዚህም ምክንያት ብዙ መንግስታት እንዲህ ያለውን ሁነት የማዘጋጀት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው። ይህ የስፖርት ቱሪዝም እድገት በፊት ከነበረው ባህላዊ ጨዋታዎች ተለውጦ ልምድን እና ክህሎትን መሰረት ያደረገ የመዝናኛ ማዕከል ሆኗል።
የስፖርት ቱሪዝም በዓለም ዙርያ ለብዙ ሰዎች ትልቅ የማህበራዊ እና የምጣኔ ሐብት የገቢ ምንጭ ሲሆን ተቀባይነቱም ልክ እንደ ኦሊምፒክ ጨዋታ ፣ የዓለም እግር ኳስ ጨዋታ ሁሉ የዓለማችን ግዙፍ ሁነት መሆን ችሏል። ፍላጎቱ የስፖርት ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በስፖርትና በምጣኔ ሃብት መካከል ያለው ቁርኝት ተመጋጋቢ በመሆኑ ወጣቶችን ለማነፅና ሰላማዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር የመንግስት አካላትም ትኩረት ሊሳብ ይገባዋል።
የስፖርት ቱሪዝም የሐገር ውስጥ እና የውጭ ሐገር ተሳታፊዎችንም ሆነ ተመልካቾችን የመሳብ አቅም አለው። በዚህም ምክንያት ለምጣኔ ሃብት እና ለከተማ እድገት ትልቅ አፅተዋፅኦ አለው። ለምሳሌ ገቢን ይጨምራል ፣ የዋጋ ግሽበትን ያረግባል ፣ ትኩረት ያላገኙ ከተሞች ትኩረት እንዲደረግባቸው ያስችላል። ይህም የተረጋጋና ሰላማዊ ማህበረሰብን ለመፍጠር ያለው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ስፖርት ማህበራዊ ለውጥን ለማምጣት አይነተኛ መሳሪያ ነው። ስፖርት የአካል እንቅስቃሴ እና የጤና ፣ የማህበረሰብ ፣ የምጣኔ ሃብት እድገት መሠረት ነው። እንዲሁም ስፖርት ለሰላም እና ለእድገት እንደ መሳሪያነት ያገለግላል። ይህ ማለት ስፖርት የግልም ሆነ ማህበራዊ ግባችን ላይ ለመድረስ አስፈላጊ ነው።
የስፖርት ቱሪዝም በአዘጋጁ ከተማ ማህበረሰብ ላይም ሆነ በእንግዶቻችን ላይ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በዘለለ የራሱ የሆነ ማህበራዊ ተፅእኖዎች ያሉት ሲሆን የማህበረሰባችንን አካላዊ እና አዕምሯዊ ጤና እንዲጎለብት ያስችለናል። የህክምና ወጫችን እንዲቀንስ ይረዳናል። ከዚህ ባሻገር የስፖርት ቱሪዝም የህዝብ ለህዝብ ትስስራችን እንዲጠነክር፣ ወንጀል እንዲቀንስ፣ ፀረ ማህበራዊ ባህርያት እንዲወገዱ ያስችላል።
የማህበረሰብ ክፍል መሰሉ ጋር ይህን ማህበራዊ ትስስር በአካላዊ እንቅስቃሴም ይሁን በደጋፊነት መንፈስ ማጎልበት ይችላል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የማህበረሰባችን የነቃ ተሳትፎ ፣ የማህበረሰቡ ጤና እና ምርታማነት ይሻሻላል ፣ በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ መፍጠር ያስችላል። ስታዲየማችን ከስፖርት እንቅስቃሴው እና ከደጋፊነት ስሜት ጋር ተያይዞ የአካባቢውን ማህበረሰብ የሚያስተሳስር እና አንድነትን የመፍጠር ሚና ይኖረዋል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በማህበረሰባችን የሚስተዋሉ የወንጀል ድርጊቶች እና ፀረ ማህበራዊ ድርጊትና ባህሪን ማስወገድ የሚያስችል ሲሆን ሰው በሰላም ተቻችሎ የመኖርን እና በጋራ ሰርቶ የማደግን አቅጣጫ ያገኛል። እንዲሁም ስፖርት የሃገራችን ህዝቦች የአንድነት መገለጫ እንዲሆን ያስችለናል። መንግስት እነዚህ ነገሮች ሳይገቡት ቀርተዋል ማለት ባይቻልም ለዘርፉ ዝቅተኛ ትኩረት ወይንም የተዛባ አመለካከት መኖሩ አይካድም።
አገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካው ዘርፍ የተለያዩ ለውጦችን እያስተናገደች ትገኛለች። በዚህ ለውጥ ውስጥ በርካታ ሴክተሮች ወደ ተሻለ መንገድ የሚያመሩበት እድል መኖሩን መገንዘብ ይቻላል። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በብዙ ሴክተሮች ላይ ለውጥ ለማምጣት በርካታ ማብራሪያዎችን በመስጠት ህዝብ ብዙ ተስፋ እንዲሰንቅ አድርገዋል። ጊዜው ገና ቢሆንም ከስፖርቱ ጋር በተያያዘ ግን ይህ ነው የሚባል ነጥብ ሲያነሱ አልተስተዋለም። ወደ ፊት ግን የአገራችን ስፖርት ዋነኛ ማነቆ ከሆነው አደረጃጀት አንስቶ ሌሎች ችግሮችን የሚቀርፍ መፍትሄ ይዘው እንደሚመጡ ተስፋ ማድረጉ አይከፋም። በተጠናቀቀው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የተፈጠረው ውዝግብና የተመዘገበው ውጤትም ዛሬ በጀመርነው የ2014 አዲስ ዓመት ስፖርት እንደ ሌሎቹ ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶት ከውድድርነት ባሻገር በአዲስ አስተሳሰብ ሊቃኝ የሚገባበት ትክክለኛ ወቅት መሆኑን አመላካች ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም