ለስፖርት እድገትና መስፋፋት መሰረታዊ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ዋነኛው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርትም ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጠባቸው ስራዎች መካከል አንዱ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ትልልቅና ዘመናዊ ስታዲየሞችን በመገንባት ላይ የሚገኙ ቢሆንም ከጥራትና በጊዜ ግንባታቸው ከመጠናቀቅ ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎች ይነሱባቸዋል፡፡ ስቴድየሞቹ ከጥራትና ደረጃ ጋር የተያያዘ ትልቅ ጥያቄ የሚነሳባቸው ሲሆን፤ በዚሁ ምክንያትም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ከማስተናገድ እስከመከልከል ደርሰዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስፈርት መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፍ ጨዋታ የማስተናገድ አቅም ያለው ስታዲየም አለመኖሩን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የቻን አዘጋጅነቷን ስትቀማ ከአንድ ስታዲየም በቀር ሌሎቹ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳያስተናግዱ ታግደዋል፡ ፡
ከዚህ በኋላም የስታዲየሞቹ ግንባታ እንዲሁም ጊዜያዊ ፈቃድ የተሰጠው ስታዲየም መስፈርቱን የሚያሟሉበት ሁኔታ ካልተፈጠረ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች በጎረቤት ሃገራት መካሄዳቸው የግድ እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መፍትሄ እንዲፈለግ ካልሆነ ግን ክልከላውን መጋፈጥ የግድ መሆኑን ለኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ባዘጋጀው ያለፈው ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የበጀት ዓመቱ ዕቅድ ላይ ውይይት ባደረገበት መድረክ ስታዲየሞች በመስፈርታቸው መሰረት እንዲጠናቀቁ መንግስት ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፤ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች የሚካሄዱበት የባህርዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እያደረገ ያለው በገደብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገደብ የተሰጠውን ዕድል ለማጣት የሚያስችል ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል አመላካች ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በጊዜያዊነት ስታዲየሙ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግድ ቢደረግም መስፈርቶችን በሂደት ማሟላት የሚጠበቅበት ቢሆንም ለውጦችና መሻሻሎች እየታዩ አይደለም፡፡ በየጊዜው በፎቶ እና በተንቀሳቃሽ ምስል ተደግፎ የሚቀርበው ሪፖርት ተመሳሳይ በመሆናቸው ቀጣይ ጨዋታዎችን ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሚሆን ካፍ ለፌዴሬሽኑ ማመላከቱንም አቶ ባህሩ ጠቅሰዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከማዳጋስካር ጋር ጨዋታ ካደረገ በኋላ ፌዴሬሽኑ የ4ሺ ዶላር ቅጣት እንደተላለፈበትም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ በሚኖሩ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ይህ ቅጣት የሚቀጥል በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡
በስፖርት ምክር ቤቱም ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ስታዲየሞች እየተገነቡ እንዲሁም የዲዛይን ርክክብም እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህ መልካም ሆኖ ሳለ ግን ምን ያህል ደረጃቸውን ጠብቀው ነው የሚገነቡት የሚለው ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ዋናው ነገር የስታዲየሙግንብ ሳይሆን ሜዳው፣ የተጫዋቾች መልበሻ ክፍልና ሌሎች መሰረታዊ መሰረተ ልማቶች ናቸው፡፡ ለስታዲየሙ ሌሎች ጉዳዮች የሚወጣው ገንዘብ ወደ ሜዳው መዞር ካልቻለ ደረጃውን የጠበቀናና መስፈርቱን ያላሟላ ስታዲየም ይሆናል፡፡
የካፍ ምልከታ ስታዲየሞች ከሚይዙት የተመልካች ቁጥር ይልቅ ጥራት ላይ በመሆኑ በሚገነቡ ስታዲየሞች ዲዛይን ላይ መንግስት ትኩረት በማድረግና ግብረኃይል በማዋቀር አቅጣጫ ማስቀመጥ ቢቻልና ክትትልም ቢደረግበት መልካም ይሆናል፡፡ ካልሆነ ግን አሁን ባለው ተመሳሳ ሁኔታ መቀጠል የግድ ይሆናል ሲሉም ኃላፊው አሳስበዋል፡፡ በካፍ ደረጃውን አላሟሉም የተባሉ ትልልቅ ስታዲየሞች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ጥልቅ ጥናት እንደተደረገበትና ዕቅዶችም የተመላከቱበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና ፋሲሊቲ ዳይሬክተር ኢንጂነር አስመራው ግዛው ናቸው፡ ፡
ጥናቱንም ለኢፌዴሪ ስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢ ለሆኑት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ቀርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዲያስተናግድ የተፈቀደለት የባህርዳር ስታዲየምም የካፍን መስፈርት ባሟላ መልኩ ለማጠናቀቅ እንዲቻል የመንግስት ውሳኔውን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የደረጃ ምደባ ላይ ከዚህ ቀደም የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ መመሪያ እንዲዘጋጅበትና ክልሎችም ግብዓት እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ሲጸድቅ ራሱን የቻለ የህግ ማዕቀፍ ይኖረዋል በማዘውተሪያ ስፍራዎች አስተዳደር ላይም አዋጅ አለ፤ ይህንንም መሰረት በማድረግ ማስፋፋት፣ መጠበቅ እና ማልማት ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም በክልል ስታዲየሞች ላይ በተደረገው ምልከታ የተመላከቱ ግብረ መልሶችም በአጭር ጊዜ ተዘጋጅቶ እንዲደርሳቸው የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የማዘውተሪያዎች ተደራሽነትን እንዲሁም የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላትን በሚመለከትም ኮሚሽኑ ከክልሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014