በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሸዋ ሮቢት ተሀድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት በልዩ ልዩ መሠረታዊ የቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ታራሚዎች አስመረቀ።
ተቋሙ ለስድስት ወራት ከይፋት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጂ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸው የሕግ ታራሚ ተማሪዎች ነው ያስመረቀው።
ከመስከረም 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰጥ የቆየውን ስልጠና ካጠናቀቁ 370 ሰልጣኞች መካከል የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወስደው ያለፉ 235 የሕግ ታራሚ ተማሪዎች የምሥክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡
የሸዋ ሮቢት ተሀድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት ዋና አስተዳዳሪ ኮማንደር እንዳሻው ማሙዬ “የመንግሥትን የለውጥ ጉዞ ማዕከል በማድረግ ማረሚያ ቤቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ የሕግ ታራሚዎችን ተቀብሎ በተለያዩ ሙያዎች ላይ አሰልጥኖ በማስመረቅ ፍርዳቸውን ጨርሰው ሲወጡ እራሳቸውን ፣ ቤተሰባቸውን ብሎም ሀገራቸውን የሚጠቅሙበትን ዕድል ማመቻቸትና በክህሎት በቅተው እንዲወጡ ማድረግ ነው›› ብለዋል፡፡
ማረሚያ ቤቱ በልብስ ስፌት ሙያ፣ በእንጨት ሥራ፣ በብረታ ብረት ሥራ፣ በሽመና ሙያ፣ በኤሌትሪክ ሥራ፣ በቧንቧ ጥገና፣ በውበት ሳሎን፣ በህንፃ ግንባታ እና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሙያ ነው ታራሚዎች የተመረቁት፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች በተግባር የስልጠና ጊዜያቸው ላይ በዕደ ጥበብ ሙያዎች የሰሯቸውን ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርና ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋም ተጋብዘው ለሔዱ እንግዶች አስጎብኝተዋል፡፡
ምንጭ፡- የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ