ወጣቶች ናቸው። ትውውቃቸው በትምህርት ቤት ጓደኝነትና በስራ ነው። ከአንዳቸው በስተቀር ሌሎቹ ተቀጥረው ሰርተው አያውቁም። የጋራ ቢዝነስ የጀመሩትም የራሳቸውን ኢንተርኔት ቤት በመክፈት ነበር። ይህ ቢዝነስ ሳያዋጣቸው ቢቀር ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ለኢንተርኔት ስራ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ኮምፒዩተሮችን በመያዝ ወደ ህትመትና ዲዛይን ስራ በድፍረት ገቡ።
ወደዚህ የህትመትና ዲዛይን ስራ ከገቡም በኋላ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልሆኑላቸውም። በቀላሉም ከዚህ ቢዝነስ ገቢ ማግኘት አልቻሉም። እያደር ግን ነገሮችን በማስተካከላቸው፣ ጓደኝነታቸውንም በማጠናከራቸውና አዳዲስ የቢዝነስ መንገዶችን በመከተላቸው በሁለት እግራቸው መቆም ችለዋል።
‹‹አብሮስ›› በሚል ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ያቋቋሙት የህትመትና ዲዛይን ስራ ድርጅታቸው በጥቂት ዓመታት ውስጥ በተለይ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የተማሪዎችን የልዩ ፕሮግራም ቲሸርቶችና ሹራቦች ላይ በማተም እውቅናን ማግኘት ችሏል። በሂደትም ሌሎች የወረቀት ላይ ህትመቶችንና በተለያዩ እቃዎች ላይ ህትመቶችን በስፋት በማከናወን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስታወቂያው ዘርፍ ውጤት ማምጣት ችሏል።
ከድርጅቱ ባለድርሻዎች ውጪ ተጨማሪ ሰዎችን በማሳተፍም ስራውን በስፋት እያከናወነ ይገኛል። በጥምረት ቢዝነስን ማከናወን ለሚፈልጉ ወጣቶችም በምሳሌነት የሚጠቀስ ድርጅት ለመሆን በቅቷል።
አቶ ዮሃንስ ታዱ የአብሮስ ህትመትና ዲዛይን ድርጅት ባለድርሻ ነው። ከዚህ በፊት እርሱና ጓደኞቹ በኢንተርኔት ቢዝነስ ስራ ውስጥ እንደነበሩ ያስታውሳል። ይሁን እንጂ የኢንተርኔት ስራው አዋጭ ሆኖ ባለማግኘታቸው ሂጅራ ሳፊ እና ሄዋን ማሞ ከተባሉ ጓደኞቹ ጋር በመሆን ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ወደ ህትመትና ዲዛይን ስራ እንደገቡ ይናገራል።
ከአንዷ በስተቀር እርሱና ሌላኛው የቢዝነስ አጋሩ ከአሁን ቀደም ተቀጥረው እንዳልሰሩ፤ በመካከላቸው ጠንካራ ጓደኝነት በመኖሩና በሁሉም በኩል ተቀጥሮ የመስራት ፍላጎት ባለመኖሩ ወደዚህ የቢዝነስ ዘርፍ ለመግባት እንደተገፋፉም ይጠቅሳል።
ቀደም ሲል ለኢንትርኔት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ኮምፒዩተሮችን በማምጣት ለህትመትና ዲዛይን ሥራ እንዳዋሏቸው የሚናገረው አቶ ዮሃንስ፤ እርሱና ጓደኞቹ ወደዚህ የህትመትና ዲዛይን ስራ የገቡት ያን ያህል ጥልቅ እውቀት ኖሯቸው ሳይሆን ገና ‹‹ሀ›› ብለው እንደአዲስ መሆኑን ይናገራል። በሂደት ግን ራሳቸውን እያስተማሩ፤ ስራውንም እያወቁትና በደምብ እየተረዱት እንደመጡ ይገልፃል።
የእነርሱ መነሻ ካፒታል ቀደም ሲል ለኢንተርኔትና ኔትዎርኪንግ ስራ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ኮምፒዩተሮች እንጂ ጥሬ ገንዘብ እንዳልሆነም ገልፆ፤ ስራውን ሲጀምሩ ዋነኛው አላማቸው በቶሎ ገንዘብ ማግኘት ሳይሆን ስራውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደነበር ይጠቁማል። መጀመሪያ አካባቢም ትናንሽ የወረቀት ህትመት ስራዎችንና የልብስ ላይ ህትመቶችን ማከናወን እንደጀመሩና በሂደት ሌሎች የኢንተርኔት ቤት ዕቃዎችን በመጠቀምና የተሻሉ ማሽኖችን በመግዛት ሌሎች የህትመትና የዲዛይን ሥራዎችን ማከናወን እንደቻሉ ያስረዳል።
በተለይ ደግሞ ድርጅታቸው አብሮስ ህትመትና ዲዛይን ስራ በጀመረበት በመጀመሪያው ዓመት በይበልጥ የሚታወቀው ብዛት ያላቸውን የተማሪዎች የልዩ ፕሮግራም ቲሸርትና ሹራብ ላይ ህትመቶችን በማከናወን እንደነበርም ያስታውሳል። ይህም ድርጅቱን ይበልጥ እንዳስተዋወቀው ይጠቁማል።
እርሱና አንዷ የቢዝነስ አጋሩ የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪዎች፤ ሌላኛዋ ደግሞ የአርክቴክችር ባለሙያ እንደሆኑና ይህንኑ ሙያቸውን በመጠቀም የህትመትና ዲዛይን ቢዝነስ ስራቸውን ከትንንሽ የወረቀት፣ ቲሸርትና ሹራቦች ላይ ህትመት ቀስ በቀስ ወደ ትልቅ ደረጃ እያሳደጉ እንደመጡም አቶ ዮሃንስ ይናገራል። እርሱም ሆነ ጓደኞቹ በዚህ የህትመትና ዲዛይን ስራ ያላቸውን እውቀት እኩል አፍሰው እንደሚሰሩም ይጠቁማል።
አቶ ዮሃንስ እንደሚለው ቀደም ሲል አብዛኛዎቹን የህትመት ስራዎችን በውጪ ሲያሰራ የነበረው አብሮስ ህትመትና ዲዛይን በአሁኑ ግዜ አብዛኛዎቹን የህትመትና ዲዛይን ስራዎች በራሱ ያከናውናል። ማንኛውም ልብስ ላይ የሚታተሙ የህትመት ስራዎችን በተለያዩ መንገዶች ይሰራል። የወረቀት ህትመትን በሚመለከትም መፅሄቶችን፣ ብሮሸሮችን፣ በራሪ ወረቀቶችን፣ የሰርግ፣ የቢዝነስና የልደት ካርዶችንና ሌሎችንም ህትመቶች ያከናውናል።
የህትመት ስራ በርካታ ዘርፎችን የሚያቅፍ ቢሆንም አብሮስ በልብስ ህትመቱ በይበልጥ ይታወቃል። አብዛኞቹ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም በዚሁ የቲሸርትና የሹራብ ላይ ህትመት ሥራዎቹ ያውቁታል። በቲሸርት፣ በሹራብ፣ ጃኬትና ቦዲዎች ላይ በአጠቃላይ በልብስ ላይ የሚታተሙ ህትመቶችን በሙሉ በጥራት ይሰራል። የህትመት ገበያውን ለማግኘትም ቴሌግራም፣ ኢንስታግራምና ፌስቡክ የመሰሉ ማህበራዊ ድረ ገፆችን ይጠቀማል።
የኢንተርኔት ቤት ኮምፒዩተሮችንና ሌሎች አነስተኛ ዕቃዎችን በመያዝ ስራውን የጀመረው አብሮስ፤ በአሁኑ ግዜ አጠቃላይ ካፒታሉ አንድ ሚሊዮን ብር ተጠግቷል። ከሶስቱ የድርጅቱ ባለድርሻዎች በተጨማሪ አራት ሰዎችንም በማሳተፍ ስራዎቹን አስፍቶ እያከናወነ ይገኛል። ለህትመት ስራው አጋዥ የሆኑ ማሽኖችንም አሟልቶ ስራውን ይሰራል።
እንደ አቶ ዮሃንስ ገለፃ በቀጣይ አብሮስ ህትመትና ዲዛይን ድርጅት በህትመትና ዲዛይን ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የማስታወቂያ ዘርፎች ውስጥም በስፋት ገብቶ የመስራት እቅድ አለው። በተለይ ደግሞ በባነር ህትመት ስራዎች ላይ የመግባት ውጥን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ለዚህ ስራ አገዥ የሆኑ ማሽኖችን በማሟላት የህትመት ስራውን የማሳደግ ፍላጎት አለው።
ከዚህ ባለፈ ለልብስ ህትመት የሚያስፈልጉ ማሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የልብስ ህትመት ስራውን ይበልጥ የማሳደግ አላማም ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በሌሎች የህትመት ዘርፎች ውስጥ ለመግባትም ጥረት እያደረገ ነው።
‹‹አብሮስ ህትመትና ዲዛይን ሥራ ድርጅት በሶስት ዓመት እድሜው አብዛኛውን የህትመት ስራ ገበያ የሚያከናውነው ማህበራዊ ድረ ገፆችን በመጠቀም ነው›› የሚለው አቶ ዮሃንስ ከዚህ አኳያ ደምበኛ እንደልብ በአካል አይቶት ለማሰራት እንደማይችል ይጠቁማል። ይህም ድርጅቱ ደምበኞችን በቀላሉ ማግኘት እንዳያስችለው አድርጎታል ይላል። በዚህ መነሻነትም ድርጅቱ ለብዙሃን ደምበኞች ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ይጠቁማል።
የማስታወቂያና የህትመት ሥራ ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢሆንም የግብአት እጥረት ግን የዘርፉ ዋና ተግዳሮት ነው። የእነርሱም ድርጅት በተለይ በልብሶች ላይ ለሚደረጉ ህትመቶች በተደጋጋሚ የጥሬ እቃ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ይጠቁማል። በተለይ በዚህ ጊዜ ችግሩ የጎላ መሆኑን ይጠቅሳል።
ጥሬ እቃዎቹ ቢገኙም እንኳን በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት እንደማይቻልም ይገልፃል። ከዚህ አንፃር ጥሬ እቃዎቹ እንደልብ እንዲገኙና በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እንዲቀርቡ ከማድረግ አኳያ የመንግስት ቁጥጥር ወሳኝ መሆኑን ያመለክታል።
ገና ከመነሻው ለፍተን ስለመጣንና ከምንም ስለጀመርን ‹‹make it happen›› የሚለውን መፈክር አንግበናል የሚለው አቶ ዮሃንስ ጠንክረን በመስራታችን በአሁኑ ግዜ ደምበኞች ወደኛ እየመጡ ነው ይላል።
በዚህ የህትመትና ዲዛይን ቢዝነስ ስራ በጋራ ሆነን በመስራት ውጤታማ መሆናቸውንም አቶ ዮሃንስ ተናግሮ፤ የእነርሱ ትልቁ ስኬት ከዚህ በፊት ሲሰሩት ከነበረው የኢንተርኔት ቢዝነስ ወደ ህትመትና ዲዛይን ስራ በአጭር ግዜ ውስጥ መዘዋወራቸው መሆኑን ይጠቁማል።
በዚህ ስራ የተሻለ ገቢ ከማግኘት በዘለለ ተጨማሪ ተቀማጭ ካፒታል ያላቸው መሆኑና ከእነርሱ በዘለለ በስሯቸው ሌሎች ጓደኞቻቸውንም በማሳተፍ ስራውን ማከናወናቸው የውጤቱ ትልቁ ማሳያ መሆኑንም ይናገራል። ይህ ሲባል ግን ገና የስኬት ጫፍ ላይ እንዳልደረሱና ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያስረዳል።
በተመሳሳይ ሌሎች ወጣቶችም በጋራ ሆነው የራሳቸውን ቢዝነስ በመጀመርና በመስራት ውጤት ማስመዝገብ ከፈለጉ በቅድሚያ ሰርቶ በመለወጥ ማመን እንዳለባቸው ይጠቁማል። እነርሱ እዚህ ለደረሱበት ውጤት ትልቁን ድርሻ የተወጣው ከደባል ሱስ ነፃ በመሆናቸው ሌሎች ወጣቶችም ወደዚህ ሱስ ሳይገቡ ገብተውም ከሆነ በቶሎ ተላቀው ስራቸውን ሱስ ማድረግ እንደሚገባቸውም ጓደኞቹን በመወከል ምክሩን ይለግሳል።
በኢትዮጵያ በቀላሉ ሰርቶ ማግኘት ባይቻልም አልባሌ ቦታ ከመዋል ስራን በራስ ሰርቶ የሚገኝ አንድ ብር ብልጫ እንዳለውም ይጠቁማል። የራሳቸውን ቢዝነስ ለመጀመር ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችም በቅድሚያ ድፍረቱ ሊኖራቸው የሚገባ ቢሆንም ሲደፍሩ ግን በጥናትና በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት አቶ ዮሃንስ ይመክራል።
በጋራ ሆኖ ቢዝነስን በመጀመርና በማንቀሳቀስ ከውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል የአብሮስ ህትመትና ዲዛይን ስራ ድርጅት ባለድርሻዎች ጥሩ ምሳሌዎች በመሆናቸው በተመሳሳይ ሌሎችም ወጣቶች ከእነርሱ ተምረው በጋራ ሆነው በመስራት ውጤት ማምጣት ይችላሉ። የእለቱ መልእክታችን ነው። ሰላም!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013