በአለም ከአንድ ሺህ ሰዎች 3 በመቶ ከእግር መቆልመም ችግር ጋር እንደሚወለዱ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ ሲሆን በሀገራችን በአመት 5ሺ ህፃናት ከእግር ቆልማማነት ችግር ጋር የሚወለዱ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል እስከ 1ሺህ 800 ሕፃናት ተገቢውን ሕክምና ያገኙት ሕክምናው በሚሰጥባቸው በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ 35 የመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት የዞረ እግር በወሊድ ወቅት የሚከሰት የህፃኑን እግር ወደ ውስጥ ወይም ወደ ታች እንዲዞር የሚያደርገው መንስኤው የማይታወቅ የህመም አይነት ነው። ይህ በታዳጊ አገሮች ሲወለዱ የሚከሰት ሲሆን፤ በጣም በሠለጠኑት አገሮች ግን ሕፃኑ ማሕፀን ውስጥ እያለ በመሣሪያ ሊለዩት ይችላሉ፡፡ ይህም ቢሆን ተገቢውን ሕክምና የሚያገኘውና የሚስተካከለው ከተወለደ በኋላ ነው፡፡ የእግር መዞር ህፃናት በውልደት ጊዜ በእግራቸው ላይ የሚያጋጥም ወደ ውስጥና ወደ ታች የመዞር ክስተት መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ:: የዞረ እግር ችግር ያጋጠመው ሕፃን እግር በቀላሉ የማይንቀሳቀስ ሲሆን ወደ ታችና ወደ ውስጥ ይጠማዘዛል (ይዞራል)፡፡
በወቅቱ ካልታከመ ደግሞ ለአካል ጉዳተኝነት ይዳርጋል፡፡ ችግሩ በእርግጠኝነት የታወቀ መንስዔ ባይኖረውም በፈጣሪ ቁጣ (እርግማን)፣ በኃጢአት ምክንያት እንደማይከሰት ግን ይታወቃል፡፡ ከእግር መቆልመም ችግር ጋር የሚወለዱ ህጻናት ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ችግሮች ይዳረጋሉ። በተለይ በሃገራችን የእግር መቆልመም ችግርን በዘር ወይም በእርግማን የሚመጣ አድርጎ የመውሰድ ነገር ስለነበር ችግሩን ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል።
ከእግር መቆልመም ችግር ጋር የሚወለዱ ህጻናት በወቅቱ ህክምና ካገኙ 99 በመቶ መዳን ይችላሉ። የፖንሴቴቲ የሕክምና ዘዴ በጣም ተመራጭ ሲሆን፤ ሁለት ደረጃዎችም እንዳሉት ባለሙያዎች ይናገራሉ። የመጀመርያ ደረጃ የማስተካከያ (የጄሶ ሕክምና)ና የጅማት መብጣት ቴናቶሚ ሲሆን፣ የጄሶ ሕክምና የዞረው እግር በቀስታ ወደ ቦታው እንዲመለስ ያርገዋል። ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ የማስጠበቂያ (የጫማ ድጋፍ) ሲሆን፤ በዚህኛው ደረጃ ደግሞ የተስተካከለው እግር ከእግር ጣቶቹ አንስቶ እስከ የላይኛው እግሩ ታፋ ድረስ በጄሶ ይጠቀለላል፡፡
የሕፃናትን የዞረ እግር ለማስተካከል ከስድስት እስከ ስምንት ጊዜ በጄሶ መታሰር ሊያስፈልጋቸው ይችላል፤ የታሰረውን ጄሶ በአዲስ ለመተካት ሕፃኑን በየሳምንቱ ወደ ሕክምና ተቋም መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ የእግር ቆልማማነት ችግር ተጠቂ የሆኑ ህጻናት ይህን በመሰለ የህክምና አገልግሎት በመስጠት በቀላሉ ማዳን ቢቻልም፤ ህክምና ማግኘት ባለመቻላቸው ከችግሩ ጋር አድገው ይሞታሉ። በተለይ ደግሞ በሃገራችን የህክምናው አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ከፍተኛ ችግር በመኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ለአካል ጉዳተኝነት የሚዳረጉ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ።
በሀገራችን ህክምናው ከተጀመረ 16 አመት ያስቆጠረ ቢሆንም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ተደራሽ አለመደረጉን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ የህክምናውን ተደራሽነት ለማስፋት የሁሉንም ትብብር በተለይ ባለሙያውን በማስተባበር ህክምናውን ማዳረስ ይገባል። በዚህ ረገድ ጤና ሚኒስቴር የህክምና ውስንነቱን መሰረት በማድረግ ተደራሽነቱን የማስፋት ስራዎች እየሰራ ይገኛል። የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገው የሆስፒታሎች ሪፎርም ፕሮግራም በተለይ በሪሀቢሊቴሽን ፕሮግራም 10 ሆስፒታሎችን በመምረጥ፣ በማደስና በፊዚዎቴራፒ መሳሪያዎች በማደራጀት እየሰራ ይገኛል። በ28 የመንግስት ሆስፒታሎች ህክምናው እንዲሰጥ ማስቻሉን፤ እንዲሁም ኪውር ኢትዮጵያ ከተባለ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር የእግር መቆልመም ችግር የህክምና አገልግሎቱ በክለብ ፉት ማእከሎች እየተሰጠ መሆኑን ተከትሎ ችግሩን ለማቃለል እንደተቻለ መረጃው ያስረዳል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014