በበዓላት ወቅት አመጋገብን ማስተካከል እንደሚገባ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ሰዎች ብዙ ጊዜ በበዓል ወቅት ቅባት የበዛበት ምግብ ሲመገቡ ለህመም ያጋልጣቸዋል። ቅባት የበዛበት ምግብ ለሠውነት ባለመስማማቱ በዓልን በህክምና የሚያሳልፉም አይጠፉም። በመሆኑም ብዙ ሰዎች በበዓላት ቀን ቀለል ባሉ ምግቦች የመፈሰክ ልምድ ማዳበር ያስፈልጋል። ቅባት የበዛበት ምግብ እና አልኮል መጠቀም የጤና ሁኔታን ያናጋል። የጨጓራችን መጎዳት ለሌላ ተጨማሪ ህመም ሊጋልጥ ስለሚችልም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።
ለበዓል ቅባት የበዛበት ምግብ ማዘጋጀት የተለመደ ቢሆንም መጥኖ መሥራት ተገቢ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ። አንዳንድ ጊዜ በበዓል ጊዜ ተልባ እና ሱፍ ይዘጋጃል። ጤናችን ለመጠበቅ ሠውነታችንን ቀስ በቀስ አለማምደን መመገብ ጥሩ ነው።
የሥነ ምግብ እና አመጋገብ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት የአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የበዓል አመጋገብ ተመሳሳይ ነው። የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ማለትም ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ቅቤ እና መሰል ምግቦች መመገብ የተለመደ ነው። ይህ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ከቅባት ርቆ የቆየው ጨጓራችን በአንድ ጊዜ ለመቀበል ይቸገርና ለህመም እንጋለጣለን። በመሆኑም በበዓል ወቅት አመጋገባችን ጤናማ መሆን አለበት። ምክንያቱም በበዓል ወቅት የምንመገባቸው የእንስሳት ተዋጽኦዎች በተፈጥሮአቸው ከፍተኛ ቅባት አላቸው፤ በተጨማሪ ወጥ ለማጣፈጥ የምንጨምረው ዘይት ቅባት (የፕሮቲን) መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን ያባብሰዋል።
ጨጓራ ከለመደው ሥርዓት የወጣ አመጋገብ ማለትም ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ ስንጀምር ሆድ መንፋት፣ ማቃጠል፣ ቁርጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እናመሰል ህመሞች መሰማት ይጀምራሉ።
ሰውነታችን ወደ ውስጥ የገባውን ቅባት በሚፈልገው መጠን ከተጠቀመ በኋላ ቀሪው በስብ መልክ ለተጓዳኝ በሽታ ያጋልጣል። እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ በበዓላት ወቅት ዝቅተኛ የቅባት መጠን ያላቸውን እንደ አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም ጭማቂ የመሳሰሉ ምግቦችን መመገብ ተገቢ ነው፤ ይህም ሰውነታችን ቀስ በቀስ ቅባቱን እንዲለማመደው ያደርጋል።
በተጨማሪ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከሁሉም የምግብ ክፍሎች ማለትም ከጥራጥሬ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ከእንስሳት ተዋጽኦ የተሰባጠረ ጤናማ አመጋገም ተግባራዊ ማድረግም ያስፈልጋል።
በባሕላዊ መንገድ የሚዘጋጁ እንደተልባና ሱፍ ምግቦችን ቀድሞ በመመገብ ከአፍ ጀምሮ እስከ ጨጓራ ያለውን የሥርዓተ ልመት አካሎች ወደ መደበኛው ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ተገቢ መሆኑን በባለሙያዎቹ ያስረዳሉ። የምግብ መጠንን በመቀነስና የአልኮል መጠጦችን ባለመጠቀም በበዓል ወቅት የሚከሰቱ ህመሞችን ማስወገድ እንደሚቻልም ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014