በሀገራችን የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከተጀመሩ ከ70 ዓመታት በላይ ቢቆጠርም ምርምሮቹ ለማህበረሰቡ ችግር መፍቻ ይውሉ እንዳልነበር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። የምርምር ስራዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ፤ ችግር ፈቺነታቸው ጥያቄ ላይ የሚወድቅ በመሆኑ ነው የሚሉ አስተያየቶች ጎልተው ይደመጣሉ። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን ለምርምር ዘርፍ የሚሰጡት ትኩረት አነስተኛ ከመሆኑ ጋር የሚያያዙ አሰተያየቶችም አሉ። በተለይ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶች ለጥናትና ምርምር ዘርፍ የሚሰጡት ዋጋ በሚፈለገው ደረጃ እንዳልሆነ ተደጋግሞ ይነሳል።
በሃገራችን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጥናትና ምርምር ዘርፍ የሰጡትን ትኩረት፣ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ የአንጋፋው ቅድስተ ማርያም ተሞክሮን መሰረት በማድረግ ለመመልከት ወደድን። በቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና አለም ዓቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዚዳን ዶ/ር ምስጋናው ሰለሞን፤ በሃገር አቀፍ ደረጃ ካለው እንቅስቃሴ በመነሳት እንደሚከተለው ያብራራሉ።
ትኩረትን ለምርምር ዘርፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ከመማር ማስተማሩ በተጓዳኝ የተጣለበት ኃላፊነት ጥናትና ምርምር መሆኑ ይታወቃል። በሃገራችን ከቅርብ አመት ወዲህ በጎ ጅምሮች እየተመለከትን እንገኛለን። በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የታየው መነቃቃት በግሉ ዘርፍ በተወሰነ ደረጃም እየታየ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ሰለሞን፤ የግል ከፍተኛ ተቋማት በመማር ማስተማሩ ብቻ ተወስነው የሚቀጥሉበት ጊዜ አለመሆኑንም ይገልጻሉ። በሃገራችን ከቅርብ አመታት ወዲህ በመንግስት ብቻም ሳይሆን በግሉ ዘርፍ ከመማር ማስተማሩ ባሻገር ምርምሩን የበለጠ እያጠነከሩ የመሄድ እድሎች፣ ዝንባሌዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሃገሪቱ የሚገኙ አብዛኛዎቹ የግል ከፍተኛ ተቋማት የማስተርስ ፕሮግራም ላይ ማተኮራቸውን ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ “ማስተርስ ፕሮግራም ላይ ካተኮሩ ደግሞ ለምርምር ትኩረት እንዲሰጡ የውዴታ ግዴታ ይሆንባቸዋል። ስለዚህበተለይ ደግሞ የማስተርስ ፕሮግራምን የጀመሩ ተቋማት ጥናትና ምርምር ማድረግ የግድ ይላል። ቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ወደ ማስተርስ ፕሮግራም ትኩረቱን ለማድረግ ሲነሳ የጥናትና ምርምር ዘርፍን በማጠናከር ላይ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ ጀምሮ ለዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው “ሲሉም በሃገር አቀፍ ካለው ተሞክሮ በመነሳት የዩኒቨርሲቲያቸውን እንቅስቃሴ ያስመለከቱት።
የ22 ዓመታት ጉዞ !
የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከመማር ማስተማሩ በተጓዳኝ የተጣለበት ኃላፊነት ጥናትና ምርምር ማድረግ መሆኑን ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ለዘርፍ ልዩ ትኩረት ከሰጡ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል በግንባር የሚጠቀስ መሆኑን ይናገራሉ። ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ባለፍት 22 ዓመታት እጅግ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን ሲያደርግ ነበር።
በተጨማሪም ሴሚናሮችን በማስኬድ እና ለባለድርሻ አካላት በወቅቱ እንዲደርሱ በማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ያብራራሉ። በዚህ ረገድ ደግሞ ዩኒቨርሲቲው በሃገራችን ለሚገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርዐያ ተደርጎ ሊታይ የሚገቡ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ መሆኑን ይናገራሉ።
አራቱ ጉባኤዎች!
ዶ/ር ሰለሞን የተቋሙን እንቅስቃሴ በተጨባጭ ለማስረዳት አራቱ የጥናትና ምርምር ጉባኤዎችን ያነሳሉ። “ዩኒቨርሲቲው በየአመቱ አራት ትላልቅ ጉባኤዎችን ያዘጋጃል። የመጀመሪያው የአለም ዓቀፍ የአፍሪካ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምር ሲሆን፤ ጉባኤው ባለፍት 18 አመታት ያለማቋረጥ ሲካሄድ ቆይቷል። ዘንድሮ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ ማካሄድ ተችሏል። ሁለተኛው ዘርፈ ብዙ የምርምር ሴሚናር የሚባለው ሲሆን፤ ይሕ ጉባኤ ባለፍት 13 አመታት ሲካሄድ የቆየ ነው”።
ዩኒቨርሲቲው ከሚያዘጋጃቸው ጉባኤዎች አንዱ ከሆነው ዘርፈ ብዙ የምርምር ሴሚናር እንደ ሃገር ውጤት ያስገኘ መሆኑን ዶ/ር ሰለሞን አመላክተው ሲያብራሩ፤ ጉባኤው ዋነኛ ትኩረቱ የምርምር አካላትን ወይም መምህራን ብቻ አይደለም። በተለያዩ የስራ መስኮች የሚገኙ ልዩ ልዩባለሙያዎች በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ የሚመለከቷቸውን ችግሮች በምርምር አስደግፈው ውጤቱን በጋራ እንዲወያዩበት ማድረግ ላይ ነው። ይሕ ደግሞ በሃገሪቱ የስራ እንቅስቃሴ ላይ የሚታዩ ችግሮችን፣ በጎ መልኮችን በማመላከት ረገድ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ሦስተኛው የጥናትና ምርምር ጉባኤ አይነት በርቀት ትምህርት ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደ ሌሎቹ ጉባኤዎች ሁሉ በየአመቱ የሚደረግ መሆኑን ይናገራሉ። ዘንድሮም የአለም ዓቀፍ የአፍሪካ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምር ጉባኤ ጋር አብሮ መካሄዱን ያስታውሳሉ። ተቋሙ ከሚያዘጋጃቸው የጥናትና ምርምር ጉባኤዎች መካከል የመጨረሻውና አራተኛው ‘የተማሪዎች ምርምር ጉባኤ’ ይባላል ያሉት ዶ/ር ሰለሞን፤ መድረኩ ለተማሪዎች ብቻ ክፍት የሚደረግ እና፤ አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚመሩት፣ የሚያስተባብሩት፣ የሚያንቀሳቅሱት ራሳቸው ተማሪዎች ናቸው።
መድረኩ እንዲዘጋጅ የተደረገበት ምክንያት ሲያብራሩ፤ ተማሪዎቹ ከመመረቃቸው በፊት የተለያዩ 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚፈልጋቸውን ክህሎቶች እንዲላበሱ በማሰብ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም ተማሪዎቹ የራሳቸውን የጥናትና ምርምር አቅም እንዲፈጥሩ፣ የሰዐት ወይም የጊዜ አጠቃቀም፣ የተግባቦት፣ የመምራት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያስችላቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን ያስጨበጣቸውን ክህሎት በተግባር እንዲመለከቱ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል ያሉት ዶ/ር ሰለሞን፤ ጉባኤው ከ14 አመት በፊት እንደ ተቋም ተጀምሮ፤ በሂደት ጠቀሜታውን በመረዳት እና ለሃገር የሚኖረውን ፋይዳ በመገንዘብ ሃገራዊ ሊደረግ መቻሉን ይገልጻሉ። ዘንድሮም ለ15ኛ ጊዜ መስከረም ላይ የሚካሄድ መሆኑን በመግለጽ፤ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉም እንደሆነም ነው ያመላከቱት።
ከሃገር እስከ አህጉር
ዶ/ር ሰለሞን ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዘርፈ መሰረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የሃገርን የልማት አቅጣጫን መሰረት አድርጎ መሆኑን ይናገራሉ። ቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ የራሱን ስምንት የምርምር አቅጣጫዎች በመቅረጽ መሆኑንይናገራሉ። የተቋሙ እቅዶች የተቀረጹት ደግሞ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተያዙ ዘላቂ የልማት ግቦች መሰረት በማድረግ እንደሆነም ይገልጻሉ። ስለዚህ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራን እንዲሁም፤ በተቋሙ በኩል በሃገር አቀፍ ድርጅቶች ሆኑ አለም ዓቀፍ ተቋማት የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮች ይህን መሰረት አድርገው እንደሆነም ያስረዳሉ። በመሆኑም ሃገሪቱ የምትፈልገውን ልማት የኢኮኖሚ፣ የፍትህ፣ የፖለቲካውን እድገት ማቀላጠፍ እና ማከናወን እንድትችል ትልቅ እገዛ ይኖራቸዋል ሲሉ ያመላክታሉ።
በሌላ በኩል ተቋሙ በምርምር ዘርፍ እየሰራ ያለው ስራ ከሃገር አልፎ በአህጉሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ተጽእኖ መፍጠር እንደሚችል ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሲያብራሩ፤ ዩኒቨርሲቲው በየአመቱ ኢንተርናሽናል የጥናትና ምርምር ጉባኤዎችን የሚያዘጋጅ መሆኑን ይገልጻሉ። በዚህ መድረክ ተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱባቸውን ርዕስ እንሰጣለን፤ ቀጣይ ደግሞ የሚመጡ የምርምር ውጤቶችን ደግሞ አስፈላጊነታቸውን፣ ጥራታቸውን፣ አግባብነታቸውን በመመዘን ጉባኤው ላይ እንዲቀርቡ የሚደረግ መሆኑን ያብራራሉ።
“የጉባኤው ማጠንጠኛ ዐብይ ጉዳይ የሚወሰነው በሃገር አቀፍ ደረጃ ከታቀዱት ግቦች ውስጥ ዋና የሚባለውን በመለየት መሆኑን ይገልጻሉ። ስለዚህ በጉባኤው ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ የሚቀረጸው የሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በመንተራስ ይሆናል። ሃገር አቀፍን የልማት አቅጣጫ፣ የኢኮኖሚ አቅጣጫ አጠቃላይ መነሻ ይደረጋል። ይሕም ‘ሃገራዊ የልማት አቅጣጫ ወዴት መሄድ አለበት’ የሚለውን የሚያመላክት ምርምር ማካሄድ ያስችላል” በሚል ያስረዳሉ።
ዶ/ር ሰለሞን ክለውም፤ የአለም ዓቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤን ዐብይ ጉዳይ የሚመረጠው በዩኒቨርሲቲው ብቻ ሳይሆን፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አብሮን ይሰራል፣ አፍሪካ ህብረትና የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ማህበርም ተሳትፎ የሚያደርጉ መሆናቸውን ይናገራሉ። እነዚህን ሁሉ በአንድ ላይ እንዲመጡ የተደረገው ‘የአፍሪካን ልማት በአፍሪካዊያን አብሮ በመስራት የሚመጣ ነው’ ከሚል እሳቤ እንደሆነ ይገልጻሉ። አፍሪካዊያን በአንድ ላይ ተባብረው የሚያመነጩት ሃሳብ ለኢትዮጵያም ብሎም ለአፍሪካ ልማት የተሻለ ውጤት የሚያመጣ ይሆናል ሲሉም ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014