“ተስፋ” ምሰሶዎቹ ሶስት ፊደላት ይሁን እንጂ ግዝፈትና ጥልቀቱ የትየለሌ ነው። በተለይ “የሰው ልጅ በተስፋ ነው የሚኖረው” የሚለውን ስናስብ፣ ጉዳዩ የራስም ነውና “እንዴ …” ማለታችን የግድ ነው። ከ”ጊዜ” ጥናትም አኳያ በሶስት ከፍለን ስናየው አንዱ የወደፊቱ ሲሆን፤ ይህም ያው ተስፋ እንጂ እርግጠኝነትን አያመለክትም። በመሆኑም ተስፋ የሁላችንም ስንቅ፤ የመኖር ምክንያት፣ የመቀጠል ምኞት — ወዘተረርፈ ነው ማለት ነው።
ሰው የተስፋ “እስረኛ” መሆኑን ነው ከላይ የተመለከትነው። ሰው “ነገ ይሄንን አደርጋለሁ” ሲል ያው ተስፋ እንጂ ምንም የተጨበጠ ነገር በእጁ ይዞ አይደለም። እዚህ “ሰው” ያልነው በተለይ “የሚያስብ” ከመሆኑ አኳያ እንጂ ሁሉም (በደመ ነፍስም ቢሆን) ያውና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ናቸው።
ይህ መንደርደሪያችን በዛሬው ጽሑፋችን ስለ ተስፋ እንደምናወራ ከወዲሁ ያሳውቃልና ስለ “ተስፋ” ነው የምናወራው።
አንድ በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት የቀረበ ትያትር “ተስፋ እርቆ የተሰቀለ ዳቦ ነው” የሚል ሃሳብ እንዳስተጋባ አስታውሳለሁ። ያ ትያትር ነው፤ የራሱ የሆነም ምክንያትና ዓላማ አለው። የጥበበኛው የመጠበብ መብት እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። እኛ ግን እምንነጋገረው መንጋቱ ስለማይቀረው ለሊት፤ ከመሆን ስለማይስተጓጎለው እውነት ነው። ይህን ስንል ደግሞ ከነብይነት የመጣ ሳይሆን ከታሪክና ከሁሉም በላይ ከእምነት የመነጨ ነው።
ከታሪክ እንደምንረዳው ለጊዜው ቢያብጥም ሲሟሽሽ የሚታየው፣ የተነሳ ቢመስልም እንዘጭ እምቦጭ የሚለው ግፈኛ እንጂ ተበዳይ አይደለም። ታሪክ እንደሚነግረን ከሆነ እውነት ምን ጊዜም እውነት ነች እንጂ በጊዜ ብዛትም ሆነ በአደንቋሪ ጩኸት ተስተጋቦት ሀሰት ልትሆን አትችልም፤ ሆናም አታውቅም። ይህ ደግሞ ከማንምና ከየትም በላይ በኢትዮጵያና ኢዮጵያውያን ዘንድ ተደጋግሞ ቷይቷል። ይህ ከታሪክ አኳያ ነው። ከእምነት አኳያ ከዚህ ጸሐፊ በላይ ሁሉም ያውቀዋልና ወደ ዝርዝሩ ባለመግባት አልፈዋለሁ ።
እኛ ኢትዮጵያውያን መታመስ ብርቃችን አይደለም። የፈለገው፣ የነሸጠው ሁሉ እየመጣ ወይም ከውስጥ እየወጣ ሲያምሰን፤ ጠንከር ሲልም ሲገድልና ሲያጋድለን ነው የኖረው። የሁሉም መጨረሻ ግን ውድቀት፤ አይሆኑ ሆኖ መቅረት ነው። ለምን ? የሚሰሩትን እያደረጉ፣ ተስፋን ተስፋ አድርጎ ወደ ላይ በማንጋጠጥ መጪው ጊዜ የተሻለ፣ ብሩህ የሆነ እንዲሆን መመኘት ለኢትዮጵያውያን የእለት ተእለት ተግባር በመሆኑ ነው። ይህንን ደግሞ እራሷ ኢትዮጵያን “የተስፋዬቱ ምድር” በማለት የሚጠሯት ያረጋገጡት ነውና እኛም ከዚህ፣ በታላቁ መጽሐፍ ከተረጋገጠው በላይ መረጃና ማስረጃ ልናቀርብ እንችልም።
እርግጥ ነው ከራሞታችን አስደሳች አይደለም። እንደውም አሰቃቂና ሰቅጣጭ ነው። ሰው የረገፈበት፣ ከሰውም አልፎ እንስሳትና አራዊት ሳይቀሩ የተቀጡበት፣ የተቀጠፉበት ጊዜ ነው ያሳለፍነው። የሚያሳዝነው ይህ ሁሉ የሆነው በራሳችን ከውስጣችን በወጡ እኩያን መሆኑ ነው። “ላም እሳት ወለደች ….” እንደ ተባለው ማለት ነው።
እርግጥ ነው ንፁሀን ያለ ሀጢያታቸው በኢሰብአዊና ሰቅጣጭ ተግባራት ህይወታቸውን አጥተዋል። ህፃናት፣ እናቶች፣ ሴቶች፣ አቅመ ደካሞች …. ላይ የደረሰው አደጋ እንዲህ በቀላሉ በጋዜጣ ላይ ጽሑፍ የሚገለፅ አይደለም። “አገር ካላፈረስኩ …” እያለ የሚፎክረው ቡድን የሰራውንም ስራ እንዲሁ በቃላት ጠቀስ ጠቀስ አድርገን የምንገልፀው አይደለም።
በተለይ ግፉ በዝቶ እየፈሰሰ ያለን ቡድን እንዲህ በቀላሉ እገልፀዋለሁ ብሎ ማሰብ እራሱ ስህተት ይሆናልና የሚሻለው እሱን ከእነተግባሩ ለታሪክ አሳልፎ በመስጠት የነገውን ማሰብ፤ አዲሱን ዓመት ተስፋ በማድረግ የተሻለን መመኘት ነው።
አንዳንድ ሰዎች ተስፋ ማድረግን እራስን ከስራ ውጪ አድርጎ ቁጭ በማለት ህብስተ መናን ከሰማይ የመጠበቅ ተግባር አድርገው ሲመለከቱት በግልፅ ይታያል። ይህ፣ ሁሉም እንደሚያውቀው ፍፁም ስህተት ነው። ተስፋን በዚህ መልኩ መረዳት እራሱ ተስፋ የመቁረጥ ምልክት እንጂ የተስፋ ማድረግ ማሳያ ሊሆን አይችልም።
አሁንም ተስፋ እናድርግ ስንል፣ መጪው ጊዜ ብሩህ ነው ስንል፣ አትዮጵያን “የተስፋዬቱ ምድር” ስንል ማድረግ ያለብንን እያደረግን፤ መስራት ያለብንን እየሰራን እንጂ እራሳችንን የተስፋ እግር ብረት ውስጥ አድርገን አይደለም። “ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል ድረስ እንወርዳለን”ላለ ቡድን “ኢትዮጵያን ለማዳን ሲኦል የተመኘውን ቡድን እዛው እናደርሰዋለን “ በማለት ምላሽ የሰጠውና እየሰጠ ያለው የአንድነት ኃይል በአንድ እጁ የአሸናፊነት ተስፋንና ስነልቦናን፣ በጠላት ላይ የበላይነትን የመያዝ ሞራልን …፤ በሌላኛው እጁ ደግሞ አነጣጥሮ መግደያ መሳሪያውን ይዞ እንጂ ድልን፣ ነፃነትን፣ ፍትህን … ቁጭ ብሎ ከላይ እንደ ህብስተ መና በመጠበቅ አይደለም። እኛም እንደዛው ነው፤ መጪው አዲስ አመት የሰላም፣ የተስፋ፣ የብልፅግና …. ነው ስንል ማድረግ ያለብንን ሁሉ በማድረግ እንጂ ህብስተ መናን ከላይ በመጠበቅ አይደለም።
እንደ አንድ ትልቅና የረጅም ዘመን ታሪክ አገር ባለቤትነቷ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ነገር ሊያጋጥማት አይገባም የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ይታወቃል፤ የሚሉትንም እየሰማን ነው። ትክክልና ለአገር ካለ ቀናኢነት ነው። ይሁን እንጂ ትልቅ፣ ገናናና የረጅም ታሪክ አገር ባለቤት መሆን በየትውልዱ “አገር ካላፈረስን፣ ካልሸጥናት …” የሚሉ ወገኖች አይፈጠሩም ማለት አይደለም፤ ይፈጠራሉ።
በተለይ “ዘመናዊ” የሚባለው ዓለም ዘመኑ በሄደ ቁጥር ለሆዳቸው የሚያድሩ ግለሰቦች እየበዙ እንደሚሄዱ ይጠበቃል። “አይ ዶንት ኬር” ትውልድም ሊመጣ ይችላል የሚሉም አሉ። በተፃራሪው የዛች አገር ገናናት፣ ታላቅነትና የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤትነት የሚጠቅመው (ወይም መለካት ያለበት) ከገባችበት ችግር ለመውጣት የምታደርገው ጥረትና አሸንፋ የመውጣቷም አቅም ነውና በዚህ በኩል ኢትዮጵያችን አትታማምና አንዱም ተስፋችን ይህ ሊሆን ይገባል። መፈክሩ “አንጠራጠርም!!!” እንዳለው ሁሉ እኛም አንጠራጠርም። (አለመጠራጠር እራሱ በጠንካራ ስነልቦና ላይ የተገነባ ተስፋ መሆኑን ልብ ይሏል።)
ለማጠቃለል፣ ለእኛ ያለፈው ዓመት ጥሩ ነበር ማለት አይቻልም፤ ፈትኖናል፣ ታግሎናል፣ ሊጥለን እስኪደርስ ድረስ አንገዳግዶናል (እነ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ ጃፓን ወዘተ በተለያዩ ዘመናት ገጥሟቸው እንደነበረው ሁሉ) ….፤ ይሁን እንጂ የብዙዎቻችን ተስፋ እንደነበረው ሁሉ አብዛኛውን ፈተና በድል ተወጥተነዋል፤ አልፈነው እዚህ የአዲሱ ዓመት መባቻ ላይ ደርሰናል። በመሆኑም “የተስፋዬቱ ምድር” ተብሏልና አዲሱ ዓመት ተስፋችን ከተስፋ እግር ብረት የሚወጣበትና በሰነቅነው ተስፋ አማካኝነት የተስፋይቱን ምድር የምናይበት ይሁን። አሜን!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014