ቅዱስ መጽሐፍ ‘ሊነጋ ሲል ይጨልማል’ እንዲል በበርካታ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች የተሞላው 2013 ዓ.ም የጊዜ ሁደቱን ጠብቆ ተሸኝቷል። የኮቪድ ተሻጋሪ ተግዳሮት፣ የህዳሴ ግድባችን ላይ ያለአግባብ ለመፍጠር የተሞከረው ጫና፣ የዓለም ፖሊስ ነን ባይ አገራት በአገራችን ጉዳይ ገብተው ለመፈትፈት ያደረጉት ትርጉም አልባ ሙከራና ሱዳን የአገራችንን ግዛት በመጣስ የፈጸመችው ወረራ በ2013 አገራችን ኢትዮጵያን ከፈተኗትና ተግዳሮት ከሆኑባት ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። ከሁሉ ከሁሉ በላቀ እጅግ የሚያሳዝነውና ለሀገራችን ህልውና ትልቅ ፈተና የነበረው ግን ጨካኙ ፣ የእናት ጡት ነካሹ፤ ዘራፊውና አራጁ ህውሓት በአገራችን ላይ የደቀነው አደጋ እንደነበር ከማናችንም ሊሰወር አይችልም።
ይህ አረመኔ ቡድን በወርሃ ጥቅምት 2013 ዓ.ም ህዝቡን ደጀን አድርጎ አገሪቱን ከጠላት ይጠብቅ በነበረው በጀግናው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ማንም ባልጠበቀው መልኩ ከጀርባ አጥቅቶ የባንዳነት ተግባር ፈጽሟል። በዚህ አሸባሪ ኃይል የጥፋት ሥራ በርካቶች ህይወታቸውን እንዲያጡ፣ አካላቸው እንዲጎድል ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ የአገር ሀብት እንዲወድምና የሀገራችን ህልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሆኗል። ይህ የጥፋት ኃይል በፈጸመው የመሠረተ ልማት ውድመትና የህዝብ ማፈናቀል አገራችን በሌለ አቅሟ በመቶ ቢሊዮኖች ብር ወጪ እንድታደርግ አስገድዷል።
ይህ ጨፍጫፊ ቡድን በሀገር መከላከያ ላይ ባደረሰው ጥቃት ብቻ ሳይታጠር ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በማይካድራ፣ ጋሊኮማ፣ አጋምሳ፣ ሁመራና ጭና ወዘተ የብዙዎችን ህይወት በአሳዛኝ ሁኔታ ነጥቋል። የዚሁ የሽብር ኃይል መንታ የሆነውና ዕድሜ ዘመኑ ሁሉ ከጥፋት ውጪ ፋይዳ ያለው ተግባር ከውኖ የማያውቀው ሸኔም ንጹሃንን በመጨፍጨፍ ዓመቱ ለኢትዮጵያ የጨለመ እንዲሆን ለማድረግ ብዙ ጥሯል።
እነዚህ እኩይ አሸባሪዎች በፈጸሙት ግፍና ጥቃት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲፈናቀሉ፣ የግብርናና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲደናቀፉ በማድረግ ሀገራዊ ህልውናችን ለአደጋ እንዲጋለጥ ተሞክሯል። ኢትዮጵያን የማፍረስ ድብቅ አጀንዳ ላላቸው የውጭ አካላት አጀንዳ ፈጻሚ በመሆን እነዚህ የሽብር ድርጅቶች ባይሳካላቸውም ሀገርን ለማፍረስ ያለዕረፍት ጥረዋል።
የሱዳን መንግስት ሀገራችን የገጠማትን ወቅታዊ ችግር እንደምቹ ዕድል በመጠቀም የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ግዛት መዳፈሩም በ2013 ዓ.ም ሀገራችንን ካጋጠሟት ተግዳሮቶች መካከል የሚጠቀስ ነው። የሱዳን መንግስት ከዚህም ባለፈ ሳምሪ በሚል ስያሜ የሚጠራውና ንጹሃንን በመጨፍጨፍ በሱዳን ለመሸገው አሸባሪ ሃይል ሽፋን በመሆንም የሶስተኛ ወገን ተላላኪነቱን በተግባር ያሳየበት ሁኔታም ነበር።
ሀገራችንንና ህዝባችን ከሌላቸው ጥሪት መድበው ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ብርሃን የሚሆነውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ወደ ፍጻሜ እያቀረቡ ባለበት ወቅት እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባይዋ ግብጽና ተላላኪዋ ሱዳን የግድቡን ሂደት ለማደናቀፍ የሄዱበት መንገድም በ2013 ዓ/ም ከገጠሙን ፈተናዎች የሚመደብ ነው።
“ምንም ዓይነት ተግዳሮትና ፈተናዎች ቢገጥሙንም ጥሰን ማለፋችንና የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆኑ አይቀሬ ነው” ሲሉ ዶ/ር ዓብይ አህመድ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ተደራርበው የመጡ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ኢትዮጵያን ከብልጽግና ጉዞዋ ለአፍታ ሊያቆሟት ግን አልቻሉም። ይልቁኑ በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎችና አበሳዎች መካከል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አስደማሚ ድሎችንና ውጤቶችን አስመዝግበዋል።
በ2013 ዓ.ም ከተገኙ ድሎች መካከል ዋነኛው “ጦርነት ለእኛ ዕቃ ዕቃ ጨዋታችን ነው” በሚል ትምክህት የተወጠረውና አገር አፍራሹ አሸባሪው ህውሓት በመከላከያ ሃይላችን ኃይል ሃያል ክንድ ተደቁሶ በነፋስ ላይ እንደተበተነ ዱቄት መብነኑ ነበር። ጀግናው የኢፌዴሪ መከላከያ ኃይል አገር ለማፍረስ የተነሳውን ይህን አሸባሪ ቡድን ደግሞ ደጋግሞ በመደቆስ ከመንግስታዊ ሽፍታነት ወደ በረሃ ተሹለክላኪነት ቀይሮታል!
አንድ በመቶ አንኳን ካላመነጨችው የዓባይ ውሃ ብቻዬን ልጠቀም ባይዋ ግብጽና ግራ ቀኝ ማስተዋል የተሳነው የሱዳን መንግስትም በሀሰተኛ ክስ ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን ለማደናቀፍ ያደረጉት ከንቱ ልፋትም በዓለም መድረክ እውነትንና ፍትህን በያዘችው ኢትዮጵያ በአሸናፊነት መጠናቀቁ በ2013 ዓ/ም የኢትዮጵያውያንን ልብ ሞቅ ካደረጉ አስደሳች ድሎች አንዱ ነው። በዓለም ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ቢደረግም ሂደቱ የኢትዮጵያን ታላቅነትና አርቆ አስተዋይነት በሚዘክር መልኩ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተደምድሟል።
ከ2013 ድሎች ትልቁና ለመጪዋ ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል ብሩህ ተስፋን የፈነጠቀው ሌላኛው ድል ደግሞ መላ ኢትዮጵያውያን በህብረትና በከፍተኛ ጽናት ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ያጠናቀቁበት ሁነት ነው። በዚህ ምርጫ የኢትዮጵያን መልካም የማይወዱ ብዙ ቢያሟርቱምና ይሄንኑ ሰበብ አድርገው አገራችንን ለማተራመስ ቢያቅዱም በሉዓላዊነታቸውና በአገራቸው ፈጽሞ የማይደራደሩት ኢትዮጵያውያን በፍጹም ጨዋነትና ጽናት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ተሰልፈው በመምረጥ ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርገዋል ።
በአጠቃላይ በ2013 ዓ/ም እንደ አገር ብዙ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ቢገጥሙንም ፈተናዎቹ ከመሰበር ይልቅ አጠንክረውንና አነድነታንን አጠንክረውን አልፈዋል። በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ሆነን ያስመዘገብናቸው አስደናቂ ድሎችም አዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ አዲስ የተስፋና የብልጽግና ጸሐይ የሚፈነጥቅበት እንደሆነ አመላካች ናቸው!
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2014