“ታላቅ መሆንን የሚፈልግ፤ በታናሽነት ዝቅ ብሎ ያገለግል!” የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ መሠረታዊ አስተምሮ “We Trust in God” እያለች ዶላሯን በመንፈሳዊ ብሂል ላወዛችው “ታላቋ!” አሜሪካ የሚዋጥ መልዕክት አይደለም:: “መሠረታችን የጸናው በቀደምት አባቶቻችን (For Fathers) ጸሎት ላይ ነው” የሚለው መፈክርም በወቅታዊ መሪዎቿ ዘንድ አጅግም ቅቡልነት ያለው አይመስልም፡፡
አልሆነላትም እንጂ ቢሆንላት ኖሮማ አሜሪካ ይሏት ሀገር ሁሉም ቢሰግድላት፣ ዓለም ቢያጎነብስላት ደስታዋ ነበር:: ሲበረታ በጦር ኃይሏ ጡንቻ፣ ሲያሻት በሰብዓዊ ርዳታ ደረጎት ንፈገቷ፣ ይሄ ሁሉ አልሳካ ሲላት ዲፕሎማሲ በሚሉት ጨዋታ ሉዓላዊ ሀገራትን አስገብራ ከእግሯ መዳፍ ሥር ብትረግጥ ምኞቷ ነበር፡፡
ይህ ጸሐፊ በደጋግ የአሜሪካ ዜጎች መካከል ኖሮና በታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎቿ ውስጥ ገብቶ በመማሩ ባለውለታ መሆኑን አይክድም:: የዚህ ጽሑፍ ቀስት የሚያነጣጥረው በሀገሬ ላይ በትረ ሥልጣናቸውን እየሰነዘሩ ካልቆነጠጥኩሽ እያሉ በሚያሴሩት መሪዎቿ ላይ እንጂ ተራብን ስንል በረዱን፣ ተቸገርን ስንል የበጎነት እጃቸውን በዘረጉልን፣ በታክሳቸው ብቻ ሳይሆን ከኪሳቸውም ጭምር ገንዘባቸውን ሆጨጭ እያደረጉ በተራድኦ ድርጅቶቻቸው አማካይነት ስንቅ አሲዘው እየላኩ “አይዟችሁ!” እያሉ ከጎናችን የሚቆሙትን ዜጎቿን በምልዓት አይመለከትም፡፡
ያለመታደል ሆኖ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ “ታላቋንi” ሀገር ለመምራት ዕጣ የወደቀባቸው መሪዎቿና ፖሊሲያቸው ጀብደኝነት የተሞላበትና “ረግጠህ ግዛው” ይሉት ዓይነት ባህርይ እንደሚስተዋልበት በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ:: የእነዚሁ መሪዎቿ የጓዳ ምክክርና የአደባባይ ዲስኩር በይዘትም ሆነ በድምጸት የሰማይና የምድር ያህል እንደሚራራቅ ማስረጃ እያጣቀሱ የጻፉ ብዙዎች ናቸው፡፡
ታላቅነትን በተግባር ከማረጋገጥ ይልቅ በታናሽ አስተሳሰብ መንፈራገጥ ያደረሰባቸውን “ውርደትና ስብራት” እንኳ ቆም ብለው በማስተዋል ለማረምና ለማከም ግትር አቋም የሚስተዋልባቸው መሪዎቿ የሞራል ብቃት አልታደሉም:: በማያገባቸው እየገቡ በሉዓላዊ ሀገራት ጉዳይ ውስጥ ጥልቅ በማለታቸው የደረሰባቸውን ቅሌትና ውርደት ለመዘርዘሩ ባይገድም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላልሆነ የማልፈው በድርበቡና በተራ ዜጋ ተራ ትዝብት ብቻ ይሆናል፡፡
“ያገኘም ያጣና፤ ያጣም ያገኝና፣ያስተዛዝበናል ይኼ ቀን ያልፍና፡፡” አለች ይባላል ቀን የጨለመባት ተስፈኛ አንጎራጓሪዋ ስሜየለሽ እህታችን፡፡
“አህያ ሞተች ተብሎ ጉዞ አይቀርም!” እንዲሉ ለምን ይሆን አሜሪካ በሉዓላዊ ሀገራት ላይ ማዕቀብ በመጣል የእብሪት አራራዋን ለማርካት የምትጣደፈው? ፍላጎቷን የተረዱ ወይንም ጥያቄው የገባቸው የንባብ ማኅበርተኞች ይህን ጉዳይ አፍታትተው ቢያስረዱን መልካም ይሆናል፡፡
የኢትዮ አሜሪካ ይፋዊ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከተመሠረተ እ.ኤ.አ ከ1903 ዓ.ም ጀምሮ ዘመኑን ስናሰላ እነሆ ከተወዳጀን የ118 ዓመታት መስቀሎች ተተኩሰዋል:: በጠበኝነት ጀርባ ለጀርባ የተገፋፋናቸውን የዘመነ ደርግ 17 ዓመታት ይሁን ብለን ብንቀንስ እንኳን ድፍን አንድ መቶ ዓመታትን በወዳጅነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እየተደጋገፍን ስለመኖራችን ግርድፍ ስሌታችን ያመላክታል፡፡
በዚህ የአንድ ክፍለ ዘመን “የወዳጅነት ጉድኝት” በሁለቱ ሀገራት መካከል መልካም ውጤቶች መመዝገባቸው አልቀረም:: በዘመነ ደርግ አገዛዝ ዘመንም እኮ ቢሆን የግንኙነቱ ሰንሰለት “The weakest link” ይሉት ብጤ ካልሆነ በስተቀር ሙሉ ለሙሉ ደጃፍ ተዘጋግተን ነበር ለማለቱ ያዳግታል:: ለነገሩ በዚያም ዘመን ቢሆን ለድርቅ ችግራችን ፈጥነው እጃቸውን የዘረጉልን እና የልማት ድጋፎችንም ይቆነጥሩልን እንደነበር ባናስታውስ ውለታ በልነት ይሆናል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት በጀብደኝነት እየፎገላ ከምንግዜውም በከፋ ሁኔታ ለምን በሀገሬ ጉዳይ ላይ ክንዱን ለማሳየት እንደሚፎክር አይገባኝም:: ለምን ይሆን? በምንስ ምክንያት? የሚሉትን መሪ ጥያቄዎች አፍታትቶ የሚያስረዳን ቢኖር ለጸሎትም ይሁን ለዕውቀት በእጅጉ ፍንጭ ይሰጠን ነበር:: በቋሚነት የምንቆዝምበት ይህ የነፃ መድረክ ገጽ ወርድና ስፋት ስለሚገድበን የምንፈልገውን ሁሉ አጥንተን ለማቅረብ አያስችለንም እንጂ የጽሑፉ መድረክ ወደ አዳራሽ ውይይት ሰፋ ብሎ ቢመከርበት ብዙዎቹን ገመናዎቻቸውን እየዘከዘኩ ማሳየት በተቻለ ነበር፡፡
በግሌ አመለካከት “የታላቋi” የአሜሪካ መሪዎች በሀገሬ ላይ ፊታቸውን ከስክሰው በማጨፍገግና ልባቸውን ቋጥረው በሻከረ አቀራረብ በራሳችን ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ካልገባን እያሉ መወራጨት የጀመሩት አሸባሪው ትህነግ ከመንበረ ሥልጣኑ ተወርውሮ ወደ ተወለደበት የደደቢት በረሃ ማህጸን ውስጥ ዳግም ከተመለሰ በኋላ ይመስለኛል:: የኩርፊያው ምክንያት ደግሞ “ለምን የጡት ልጆቼ ተነኩ?” የሚለው “የጡት አባትነት – God Father አደራው” አሜሪካኖቹን ግድ ሳይላቸው አልቀረም:: ለኩርፊያቸው ፍንጭ የሚሰጠን በህዳሴ ግድባችን ላይ የተንሻፈፈው አቋማቸውን ስናስተውልና የብልጽግናው ጉዞ የተስፋ ነፀብራቅ የውስጥ ትምክህት አይናቸውን መውጋት በመጀመሩ ይመስለናል፡፡
ይህ የኩርፊያ ጉርምርምታ ይበልጥ ድምጹ እየጎላ መሄድ የጀመረው የአሸባሪውን የትህነግ ቡድን እብሪት ለማረቅ ከተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል:: ሉዓላዊው የሀገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ” ብሎ በሕግ የወሰነበት ይህ ቡድን ለምን ይነካል በማለት ኡኡታ ማሰማት የተጀመረው ከዚያ በኋላ ነበር:: መከላከያ ሠራዊትን ያህል ታላቅ ኃይል በተቀናበረ የትዕቢት ሴራ ሲደፈር ዝም ብለው አንድ ተራ የሽፍቶች ቡድን ሲሸነቆጥ ምን ሲደረግ ብሎ ማቅራራትና ማስፈራራት ህሊና ቢስነትና “ዲሞክራሲና ሰብዓዊነት” እያሉ በሚያላዝኑበት እሴት ላይ መቀለድ ይመስላል፡፡
ንፁሐን ዜጎች በአማራና በአፋር ክልል በግፍ ተጨፍጭፈው ደማቸው ወደ መንግሥትና ወደ ፀባኦት ሽቅብ ሲጮኽ ጆሯቸውን ጥርቅም አድርገው ደፍነው አሸባሪዎቹ ለሚፈጽሙት ግፍ መራር የቅጣት ዋንጫቸውን ሲጎነጩ ግን አፈጉባዔያቸው በመሆን ለማዕቀብ መሽቀዳደማቸውን ስናስተውል “ግብዝን ሁለት ጊዜ እባብ ነደፈው” ብለን ልንተርትባቸው ግድ ይሏል፡፡
የእነርሱ የማዕቀብ ፉከራ አንሶ የአውሮፓ ሀገራትን ሳይቀር ሀገሬ ብድርና የልማት ድጋፍ እንዳታገኝ እየፈጠሩ ያለው ጫና ከህሊና ሙትነት ሌላ ምን ይባላል:: ስለዚህም ነው ኢትዮጵያ የእነርሱን የጠቆረ ፊት በነጋ በጠባ ከማየት ብላ ወደ ሌሎች ፊታቸው ወደ ፈካ ወዳጆች ጎራ በማለት ራዕዩዋን ለመተግበር ቀን ከሌት እየደከመች ያለቸው:: ይህም እርምጃዋ ቢሆን አላስደሰታቸውም:: “ከእኛ ወዲያ እንዴት ይሞከራል!” በሚለው የትምክህት ዛቻ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለታቸው በገሃድ እየታየ ነው፡፡
ከቅርብ ወራት በፊት የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የቪዛ ዕቀባ እንደተደረገባቸው ይፋ ስታደርግ ግርምት ፈጥሮ ነበር:: “በምን ምክንያት?” ተብለው ቢጠየቁ ይሄ ነው የሚባል ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይኖራቸውም:: የሚያሳምን መከራከሪያ ስላላቸው ብቻ ሳይሆን የጡንቻቸውን አቅም ለማሳየት ስለፈለጉም እንደሆነ ገብቶናል:: ይሄው ጉዳይ በመላው ዓለም ዘንድ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ቁጣ ቀስቅሶ አደባባይ ሲውሉ እንኳን “አሜሪካ” የፌዝ ውሳኔዋን ለማጤን ጊዜ አልወሰደችም:: ይብስ ብላ ዲፕሎማቶቿንና የሀገሬን ውድቀት የሚመኙ ሹማምንቶቿን እያንቀሳቀሰች እርሷ የገመደችውን ሸምቀቆ ሌሎች እንዲያጠብቁላት ትተጋ ነበር፡፡
ይህም አነሰ ተብሎ በቅርቡ AGOA (The African Growth and Opportunity Act) በመባል የሚታወቀውን እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተከፈውን የቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል እንዲቃረጥ መወሰኑ በታሪካችን ውስጥ የምንጽፈው ሌላው የግፍ ውሳኔ ነው:: እ.ኤ.አ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የAGOA የንግድ ዕድል ፕሮግራም የተነደፈውና እንዲተገበር የተወሰነው በዋነኛነት ከሰሃራ በታች ላሉት የአፍሪካ ሀገራት ነበር:: ይህንን ዕድል በመጠቀምም ሀገሬ የአልባሳት፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳና በጥቂቱም ቢሆን የእርሻ ውጤቶችን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ ገበያዎች በማስገባት ተጠቃሚ ሆና ነበር:: እንደ እውነቱ ከሆነ ዕድሉን በስፋት ለመጠቀም ባንችልም በተሞከረው መጠንም ቢሆን ለሀገራችን ኤኮኖሚ ማገገም ድጋፉ የማይናቅ አስተዋጽኦ ማድረጉ አልቀረም፡፡
ይህ የAGOA የንግድ ዕድል በይፋ በተጀመረበት ዓመት ይህ ጸሐፊ በዚያው አሜሪካ በትምህርት ላይ ነበር:: ፕሮግራሙ አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብም ሀገሬ ተበረታታ እንድትገፋበት ለማገዝ በማሰብ (www. EthioIndexe.com) በተባለ ድረ ገጽ አማካይነት በቀጥታ ይተላለፍ በነበረ የኢንተርኔት ስርጭት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ኢትዮጵያዊያንን በመጋበዝ ለማወያየት መሞከሬን አስታውሳለሁ፡፡
ሜይ 18 ቀን 2003 ዓ.ም የተካሄደው ይህ ዓለም አቀፍ ውይይት ርዕሱ “African Growth and Opportunity Acts (AGOA) and Ethiopia: Current Issues and Awareness” የሚል ነበር:: እንደማስታውሰው በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ተወያይ የነበሩት እንግዶች የወቅቱ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ፕሮሞሽን ኤጀንሲ ይባል የነበረው ተቋም ጄኔራል ዳይሬክተሩ አቶ ግዛው ሞላ፣ AGOA Linkages in COMES ለተባለው አፍሪካዊ ድርጅት የፕሮግራም ዳይሬክተር የነበረችው የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪዋ ወ/ሮ ሚሚ ዓለማየሁ እና የአፍሪካ ኢኒሼቲቭ ዳይሬክተሩ አቶ ክቡር ገና ከአዲስ አበባ ነበሩ፡፡
ይህ ውይይት በወቅቱ ለጥሩ መነቃቃት በጎ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሳለሁ:: በዚሁ መሠረትም ካልተሳሳትኩ በስተቀር በዚያው ዓመት የዕድሉ ተጠቃሚ የነበሩት የሀገራችን ኤክስፖርተሮች የ822 ሺህ ዶላር ግብይት እንደፈጸሙ ሪፖርቱ ያመላክታል:: ይህ ዕድል እየሰፋ ሄዶ ምንም እንኳን 1800 ያህል ሸቀጦች ለማስገባት ዕድሉ የተመቻቸ ቢሆንም በ2020 ዓ.ም በጣት ከሚቆጠሩትና ወደ አሜሪካ ከተላኩት የተለያዩ አልባሳት ዓይነቶች ግብይት ሀገሬ ወደ 525 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታ ነበር፡፡
ሰሞኑን አሜሪካ የጣለችው ማዕቀብ ይህ ዕድል መክኖ ኢትዮጵያ ለእነርሱ የጨነገፈ አስተሳሰብ እንድታጎበድድ ታስቦ ይመስላል:: ይህ ውሳኔ በእጅጉ እንደሚጎዳን ባይካድም “ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነፃነት ስለሚበልጥ!” ሌሎች ሰፋፊ የገበያ አማራጮች እየተፈለጉ ጉድለቱ የሚቀረፍበት መንገድ እንዲመቻች በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ሁሉ ሊያስቡበት ይገባል:: ማዕቀብ የመጣል ሱስ እያናወዘው ያለው የአሜሪካ አስተዳደርም ወደ ቀልቡ ተመልሶ ውሳኔውን እንዲያጤን ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚያስፈልገው ይታመናል:: በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ይህ ጫና እንዲቀል አቅም በፈቀደ ሁሉ የአሜሪካ መንግሥትን እንዲሞግቱ መልዕክቱ ይድረስ ብያለሁ:: ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com