እነሆ ዛሬ ከብዙ ጭንቅና መከራ በኋላ የተቀበልነው የ2014 አዲስ ዓመት ራሱን ለሌላ ተተኪ አሳልፎ በመስጠት እሱም በተራው ከአሮጌዎች ተርታ ሊሰለፍ ሩጫውን ተያይዞታል።ይህንን ሩጫ ለመቅደም ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች ደግሞ እኛ ነን።ምክንያቱም ዘመን የሚለካው በስራችን መጠን እንጂ በሚቆጠሩት ሰዓታት ልክ ብቻ ስላልሆነ።የመኖር ትርጉሙም የሚለካው በምንሰራው ስራ ልክ ነውና፡፡
ዛሬ ላይ ሆነን ያለፈውን ዓመት ስንቃኝ ምናልባት የእያንዳንዳችን የእይታ መጠን ቢለያይም ብዙዎቻችን ባይሆን ብለን የምናስበው የመከራውን ጊዜ ነው።በዓመቱ ውስጥ ያሳለፍናቸው የመከራ ወቅቶች መምጣት ያልነበረባቸው፤ ነገር ግን ባንፈልግም ያጋጠሙንና ብዙ ዋጋ የከፈልንባቸው ወቅቶች ነበሩና።ከዚህ አንጻር በተለይ በአሸባሪው ህወሓት የገጠመን የጦርነት ፈተናና የሱ ተባባሪ በሆኑት የአሸባሪው ሸኔ እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በቋመጡ የውጭ ሃይሎች የደረሰብን ፈተና ትልቁ ነው።
ያም ሆኖ ግን እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ወገብን የሚያጎብጡ እና የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ በምንፈልገው ልክ በፍጥነት እንዳንጓዝ መሰናክል ቢሆኑም ጉዟችንን መግታት ግን አልቻሉም።ለዚህም በዓመቱ ውስጥ እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች እየተጋፈጥን ያሳካናቸው ድሎች ምስክሮች ናቸው፡፡
ከዚህ አንጻር ባለፈው ዓመት እንደ አንድ ስኬት የሚታየው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራችን ተጠቃሽ ነው።ይህ ስራ በዓመቱ ውስጥ ካጋጠሙን ፈተናዎች ውስጥ ሁሉ አንዱና ዋነኛው እንደነበር የሚታወስ ነው።በዚህ ስራ ላይ በግብጽ አስተባባሪነት ኢትዮጵያን ለማንበርከክና ከዚህ ስራ ለማደናቀፍ ከተሰለፉ ሃገራት መካከል ደግሞ የዓለም የዴሞክራሲ ቁንጮ ነኝ ከምትለው አሜሪካ ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የዓረብ ሊግና ሱዳን እንዲሁም ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በውሃ ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት ቀርባ ስለጉዳዩ እንድትናገር የተደረገችበት መንገድ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ከዚህም አልፎ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጭምር የህዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል “ግብጽ ግድቡን በቦምብ ልታፈነዳው ትችላለች” የሚል እጅግ ወገንተኝነት የተንጸባረቀበት ሃሳብ እስከማቅረብና ከዚህም አልፎ በተለያዩ መንገዶች በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ የሄዱበት ርቀት ማሳያ ነው።በተለይ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ የተደረጉ ጫናዎች እጅግ ፈታኝ እንደነበሩ የሁላችንም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህና መሰል ጫናዎች ሁሉ ሳይበግራት ኢትዮጵያ የሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በማካሄድ ለህዝቦቿ ጥቅም እስከሆነ ድረስ የልማት ስራዋን በማንም ማስፈራሪያ እንደማታቆም በግልጽ ለዓለም ማህበረሰብ አሳይታለች፡፡
ሌላው የ2013 ዓ.ምን ለኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና እንዲሆን ያደረገው አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት ነው።ምንም እንኳን ጦርነት አውዳሚ ቢሆንምና ኢትዮጵያ ወደዚህ የመግባት ዘመኑን የማይመጥን ተግባር ቢሆንም ለኢትዮጵያ ግን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በግድ የገባችበት እና ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ጦርነት ነው።አሸባሪው ቡድን ላለፉት ሦስት ዓመታት ሙሉ አንዴ በሽምግልና ሌላ ጊዜ ደግሞ በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሰላማዊ መንገድ ከመንግሥት ጋር እንዲሰራ ቢለመንም አሻፈረኝ በማለት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሃገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጦርነት ከፈተ።በዚህ መልኩ የጀመረው ጦርነትም የብዙ ዜጎችን ህይወት እንዲቀጥፍ አደረገ።በቢሊየን የሚቆጠር ሃብትም ለውድመት ዳረገ።
የአሸባሪው ቡድን ጥፋት በዚህ ብቻ አላበቃም።መንግሥት ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ የእርሻ ወቅት በደረሰበት ወቅት አርሶ አደሩ ተረጋግቶ እንዲሰራ ለማድረግና ህብረተሰቡም የጥሞና ጊዜ አግኝቶ ወደሰላም እንዲመለስ ለማድረግ ትግራይን ለቆ ሲወጣ አሸባሪው ሃይል አንዴ የጦርነት አዙሪት ውስጥ የገባ ነውና መንግሥትን ተከትሎ የአማራና የአፋር ክልሎችን በመውረር ከባድ ሰብዓዊ ጥፋት ፈጸመ።በዚህም በርካቶች ህይወታቸው አልፏል፤ ንብረትም ወድሟል።ከዚህም ባሻገር አርሶአደሩ የእርሻ ስራው እንዳያከናውን አድርጓል፡፡
ሆኖም መንግሥት ትዕግስቱ ሲያልቅ መልሶ በሚወሰደው የማጥቃት እርምጃ ይህ ቡድን ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል።በአሁኑ ወቅትም አብዛኛው የቡድኑ አባላት በመበታተናቸው ተደብቆ የሽብር ድርጊት ከመፈጸም የዘለለ የተደራጀ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳልሆኑ መንግሥት አሳውቋል፡፡
በመሆኑም አሁን እየሄድን ያለነው ወደ ተስፋና ወደ ብርሃን ነው።ያለፈውን መከራ እንደ ክረምቱ ተሻግረነው- ተስፋችንን እንደ አደይ አበባ አፍክተነው በመጓዝ ላይ ነው ያለነው።ያ ከባድ የጨለማና የመከራ ጊዜ አልቆ ከፊታችን የብርሃን ዘመን ተዘርግቷል፡፡
በቀጣይ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በህዝብ የተመረጠው አዲሱ መንግሥት ወደሥራ ይገባል።ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማሻገር የተያዘውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የተሻለች ሃገር ለመፍጠር የተጀመረውን እድል ሙሉ ለሙሉ ወደተግባር ለመቀየር የሚያስችል ትልቅ እድል ነው።
ከዚህም ጎን ለጎን በአዲሱ ዓመት ላለፉት አሥር ዓመታት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲጠብቀው የኖረውና እያንዳንዱ ዜጋ አሻራውን ያሳረፈበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ብርሃን መፈንጠቅ የሚጀምርበት ወቅት በመሆኑ የብዙዎቻችን ልብ ከወዲሁ በሃሴት እንዲሞላ አድርጓል።
ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችውን የልማት አጋሮቿን የማጠናከር ስራ በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን እየሰራች ነው።ለዚህ ደግሞ ፓንአፍሪካኒዝም በማጠናከር ከጠንካራ ወዳጆቿና የልማት አጋሮቿ ጋር ወደልማት ለመጓዝ የምታደርገው ጥረት ማሳያ ነው።በተለይ ከአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጋር በመሆን የጭለማ አህጉር የሚል ስያሜ የተሰጣትን አፍሪካ ለመቀየር የተጀመረው ስራ በስኬት የሚጠናቀቅበት ዓመት እንዲሆን ሁላችንም ባለን አቅም ልክ በመስራት የየራሳችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅብናል።
አዲስ ብርሃን ለመታየት የሚታገልበትን የሀገራችንን የፖለቲካ ሠማይ አዲሱ ዓመት የተሟላ ንጋት ያላብሰው ዘንድ በጋራ፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመደመር ለነጋችን ድምቀት ጠንክረን እንደምንሰራ ሁላችንም ቃልኪዳን እንግባ!
አዲስ ዘመን መስከረም 2/2014