ወይዘሮ መንበር ማዘንጊያ ይባላሉ፤ በድሮው ስሜን አውራጃ ጃናሞራ ወረዳ ነው ትውልድና ዕድገታቸው። ብልሹ አሠራርን ከተመለከቱ ለነገ የሚል ቀጠሮ አይሰጡም፤ ለድሀ በመጮኽ የፍትሕ ተሟጋችነት ስማቸው በጃናሞራ በእጅጉ ከፍ ብሎ ይታወቃል፡፡
በዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሴቶችን በመወከል ለፓርላማ ለመወዳደር ድምጽ በማሰባሰብ በአካባቢው የመጀመሪያና ፈር ቀዳጅ ሴት ናቸው። ነገር ግን በወቅቱ ሕዝቡ ሴቶችን ለሕዝብ ተወካይ ለመምረጥ የነበረው አመለካከት ዝቅተኛ ስለነበር አልተሳካላቸውም።
በደርግ ዘመንም በተመሳሳይ ለሕዝብ ዘብ በመሆን ሰላማዊ ትግል በማድረግ ትግላቸውን ቀጠሉ፤ በዚያ ብዙዎች ዝምታን ሌሎች ደግሞ የትጥቅ ትግልን አማራጭ ባደረጉበት ዘመንም ሰላማዊ ታጋይ ነበሩ፤ ወይዘሮ መንበር።
ኢሕአዴግ ሀገሪቱን ተቆጣጥሮ ኤርትራን ለመሸኘት ሕዝበ ውሳኔ ሲያደርግ ሴቶችን በመወከል በጎንደር ተሳታፊ ነበሩ። በወቅቱም ሁለት ጊዜ የመናገር ዕድል አግኝተው ‹‹አባቶቻችን አንድ አድርገው ያቆዩዋትን ሀገር መገነጣጠል አይገባም፤ ውሳኔው ተገቢም ጠቃሚም አይደለም›› በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል። በኋላም በኢሕአዴግ አገዛዝ የተመለከቱትን ብልሹ አሠራር በመቃወም በየቢሮው በመሄድ መልካም አስተዳደር እንዲመጣ ለበርካታ ዓመታት የሐሳብ ትግል አድርገዋል።
ይሁን እንጅ ከዚህ በተቃራኒ የመንግሥት ብልሹ አሠራር እየተባባሰ በመሄዱ ሰላማዊ ትግል በማደረግ በምርጫ ለመወዳደር ወሰኑ። መንግሥትን መቃወም ይቅርና በነፃነት ሐሳብን መግለፅ በማይቻልበት በ1987ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ‹‹ኢዲዩ›› የተሰኘውን የፖለቲካ ፓርቲ በመወከል መኖሪያ ቤታቸውን ቢሮ በማድረግ በርካታ ወጣቶችን በማስተባበር ተወዳድረዋል።
በ1997 እና በ2002 ዓ.ም ምርጫዎችም ከኢሕአዴግ ተቃራኒ በመሆን ዕጩ ተወዳዳሪ ነበሩ። የወይዘሮ መንበር የትግል ስልት ሕዝብ በሚገኝበት በቀብር፣ በዝክር፣ በሕዝባዊ ስብሰባዎችና በመሳሰሉት የፖለቲካ አጀንዳ በማንሳት አስተሳሰብ በመገንባት ላይ የሚያተኩር ነው።
የመንግሥትን ብልሹ አሠራር በመቃወም ለምርጫ የሚዘጋጁት እንደ እኛ ሀገር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫ ሲመጣ ብቻ ሳይሆን የቀን ከቀን ሥራቸው አድርገው ዘወትር በመሥራት ነው። ከዚህ ባሻገር በማንኛውም ማኅበራዊ አጋጣሚ ወይዘሮ መንበር እጅግ ቅርብ ናቸው። በተለይ በቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ ሟቹን በማወደስ በተካኑት ቅኔ ያስገጥማሉ።
ወይዘሮ መንበር የዓላማ ፅናታቸው ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለወጣቶች፣ ለሴቶች፣ ለፖለቲከኞች አርአያ ያደርጋቸዋል። ወይዘሮ መንበር ማዘንጊያ ‹የአፍሪካ ታሪክ የተቆለፈበትን› የግዕዝ ቋንቋ እንደፈለጉ አሞናሙነው ይናገሩታል፤ ቅኔም በመዝረፍም ይራቀቁበታል፡፡
ግጥምን በግዕዝ ቅኔ ሲቀኙ ከንፈርን በእጅ አስጭነው የትካዜ ባሕር ውስጥ ያስገባሉ፡፡ ‹‹በምንም ጥቅማጥቅም ወገናቸውን አሳልፈው የማይሰጡት ጀግናዋ ሴት በዓላማ ፅናት ለወገናቸው የተሟገቱና አሁንም የሚሟገቱ የፅናት ማሳያ አርበኛ ናቸው›› ይሏቸዋል በቅርበት የሚያውቋቸው ሁሉ፡፡
ምንጭ አብመድ