በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ ሰርግ ላይ በተተኮሰ ጥይት የሙሽሪት ሕይዎት አልፏል።
ድርጊቱ የተከሰተው ትናንት የካቲት 17/2011 ዓ.ም ነው፤ ቦታው ደግሞ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ። ቤተሰብ ልጃቸው ለወግ ማዕረግ በመብቃቷ ሙሽሪትም ወደ ትልቁ የሕይዎትና የኃላፊነት ምዕራፍ በመሸጋገሯ ደስታ ላይ ነበሩ። ቤተዘመድም የደስታ ተካፋዮች ናቸውና በስፍራው ታድመዋል።
በድንገት ግን ሠርጉ የሀዘን ጉም ለበሰ። ሙሽሪት በጥይት ተመትታ ሕይዎቷ አልፏልና።
ሰርጉን ለማድመቅ ተብሎ ከቤተ ዘመድ የተተኮሰ ጥይት የሙሽሪትን ሕይዎት ቀማ፤ ደስታውም ወደ ሀዘን ተቀየረ።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ተወካይ ምክትል ኃላፊ አቶ ገብረኢየሱስ ወንድሙ ለአብመድ እንደተናገሩት ጉዳዩን ለመመርመር ከጎንደር ከተማ አሥተዳደርና ከአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ቦታው ተልከዋል።
አሳዛኝ ክስተቱም የመሳሪያ አያያዝና አጠቃቀም ችግርና ክልከላን የመተላለፍ ውጤት መሆኑን ነግረውናል።
በጎንደርና አካባቢው ሰሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ ከፀጥታ አካላት ውጪ የጦር መሳሪያ መያዝና መንቀሳቀስ መከልከሉ ይታወሳል። እንደ አቶ ገብረኢየሱስ መረጃ ለሙሽሪት ሞት ምክንያት የሆነው ተኩስ ክልከላውን መተላለፍን ያሳያል።
የመሣሪያ አሥተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 44/2001 በገበያ ቦታ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎች፣ በመዝናኛ ቦታዎች፣ በሆቴሎችና በመጠጥ ቤቶች የጦር መሣሪያ መያዝን ይከለክላል ሲል የዘገበው አብመድ ነው።