ህልማችን የገዘፈ፣ ጎዳናችን በእሾህ የተከበበ፣ መዳረሻችን እጅጉን የራቀ ቢመስልም፤ ህልማችንን አስበን ጉዞ ከጀመርን፣ መንገዳችንን አስተውለን ከተራመድን እና መዳረሻችንን አውቀን ከተጋን ያሰብነው የማይሳካበት፣ ያለምነው የማይሰምርበት፣ ከግባችን የማንደርስበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም።
ይህ እንዲሆን ደግሞ ኢትዮጵያውያን በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋን ይዘን ጉዞ ስንጀምር፤ የድል ቃል ኪዳን ብስራት ቀንን ምክንያት በማድረግ በየዘርፉ ብዙ ቃል ገብተናል፤ ብዙ ልንሠራም አቅደናል፤ ስለምኞታችን መሳካት ተስፋ አድርገን እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቤተሰብ፣ እንደ ማህበረሰብ እንዲሁም እንደ ተቋምና አገር እነሆ ዛሬ ዕርምጃችንን አንድ ብለናል።
ዛሬ በህይወትና የኑሮ ዕርምጃችን አንድ ብለን የጀመርነው ምዕራፍ፤ ገና 364 ምኞታችንን ተጨባጭ የምናደርግባቸው የዕርምጃ ቀናት እና የተግባር ምዕራፎች አሉን። እነዚህ ቀናት እያንዳንዳቸው የራሳቸውን የዕድልም፣ እውቀት ላይ የተመሰረተ ተግባርም የሚሹ የስኬታችን መዳረሻ ደረጃዎች ናቸው።
እነዚህን ደረጃዎች በጥንቃቄና በአስተውሎት ከተራመድንባቸው ወደስኬታችን ጫፍ፤ ወደ ምኞታችን ማማ እንደሚያደርሱን እሙን ነው። በዚህ ረገድ 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያን ታላቅነት ከፍ የምናደርግባቸው፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች ግን የማይፈልጓቸው ሦስት መሰረታዊ ድሎችን የምናስመዘግብበት ዓመት መሆኑ አይቀሬ ይሆናል።
የመጀመሪያው ጉዳይ ኢትዮጵያ በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ የተመረጠ አዲስ መንግሥት እውን የምታደርግበት ዓመት መሆኑ ነው። ሁለተኛው ጉዳይ የዘመናት ምኞታችን የነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚጀምርበት መሆኑ ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ለዘመናት ሲያባላ የቆየው አሸባሪው ህወሓት ፍጻሜው የሚበሰርበት ዓመት መሆኑ ነው።
በመሆኑም 2014 ዓ.ም የእነዚህ ሦስት መሰረታዊ ድሎች የሚሳኩበት ዓመት ሲሆን፤ በእነዚህ ስኬቶች እውን መሆን ውስጥ ደግሞ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብልጽግና መሰረት የሚጣልበት ይሆናል። በ2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ያለፉበት ውጣ ውረድ የበዛበት መንገድ፣ የተሻገሩት የበዛ መሰናክል፣ በጥበብ ያለፉት በጠላቶች የተሸረበ ሴራ እና እውን ያደረጉት በኩራት የሚነገር የድል ገድል ይህ እውን እንደሚሆን ህያው አብነት ነው።
በዚህ ረገድ ከግለሰብ እስከ ህዝብ፣ ከተቋም እስከ አገር፣ ሁሉም በየፈርጁ በአዲስ ዓመት አዲስ ህልምና ተስፋ ይዟል፤ ይሄን ግለሰባዊም ሆነ አገራዊ ህልም እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ ደግሞ አዲሱ ዓመት አዲስ ህዝባዊ መንግሥት የሚመሰረትበት ነው። የሚመሰረተው መንግሥት ደግሞ የበዙ የቤት ሥራዎችና ኃላፊነቶች ያለበት ከመሆኑ አንጻር፤ ህዝቡ ህልሞቹ እውን ይሆኑለት ዘንድ ከዚህ መንግሥት ጋር ተናብቦና ተቀናጅቶ መሥራት ይጠበቅበታል።
ምክንያቱም ይህ ወቅት ኢትዮጵያ የችግሮቿን አቧራ አራግፋ ከችግሮቿ ትብታብ ለመውጣት ጫፍ የደረሰችበት መሆኑ ነው። በርሷ የደረሰ ችግር በወንድም አፍሪካ አገራትና ህዝቦች ላይ እንዳይደርስም የቀደመ ኃላፊነቷን ለመወጣት እየተጋች ትገኛለች። ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርሆዋም፣ አፍሪካውያን በጋራ እንዲሰባሰቡና የተባበረ አቅም ፈጥረተው እንዲሠሩ የማንቃትና የማስገንዘብ ተግባሯን ጀምራለች። ተስፋ ሰጪ ምልክቶችም መታየት ጀምረዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ በውስጥ የምታስመዘግባቸው ድሎችም ሆኑ አህጉራዊ ትስስርና ትብብር እንዲፈጠር የምታከናውናቸው ተግባራት ዛሬም እንደ ትናንቱ ሁሉ ጠላቶቿን የማያስደስቱ መሆናቸው አይቀሬ ነው። ሆኖም ኢትዮጵያ የምትሠራው እንደ ትናንቱ ሁሉ ለህዝቦቿ ሰላም፣ ሉዓላዊነትና ብልጽግናና ደስታ እንጂ ሌሎች የውጭና የውስጥ ጠላቶችን ለማስደሰትና ፍላጎታቸውን ለማሳካት አይሆንም።
ከዚህ አኳያም በ2014 ዓ.ም በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋና መንግሥት ተይዞ የሚደረገው ጉዞ፣ ለብልጽግናው እውን መሆን መሰረት የሚጣልበት ብቻ ሳይሆን፤ የታላቁ ህዳሴ ግድባችን ኤሌክትሪክ የሚያመነጭበት፤ የአሸባሪው ህወሓት ፍጻሜ የሚበሰርበት እንዲሁም አፍሪካውያን በተባበረ ክንዳቸው ከተጽዕኖ ተላቅቀው ለጋራ ልማትና ብልጽግናቸው በጋራ የሚሠሩበት ይሆናል። እናም አዲሱ ዓመት ለእኛ ኢትዮጵያውያን ትልማችን የሚጨበጥበት፣ ህልማችን የሚዳሰስበት፣ ግባችንም የሚሳካበት ይሆናል! መልካም አዲስ ዓመት!
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም