በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዜጎችን ከጎዳና ላይ የማንሳቱ ጅምር እሰከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 10ሺህ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገለፀ፡፡
ከዚህ ውስጥም በጎዳና ያሉ 5 ሺህ ሰዎችን የከተማ አስተዳደሩ በመደበው በጀት ሲያነሳ ቀሪዎቹን ደግሞ ከአለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ተፈፃሚ እንደሚሆን በአስተዳደሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ችግር ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው አበራ በተለይ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም በጎዳና ላይ ያሉ ዜጎችን በማንሳት መልሶ ለማቋቋም 100 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በመጀመሪያ ዙር ከጎዳና ላይ ዜጎችን የመታደግ ስራ 3 ሺህ 147 ሰዎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን አቶ እንዳሻው ገልፀዋል፡፡
በአሁን ሰዓትም እነዚህን ዜጎች በጊዜያዊ ማቆያ ተቋም በማስጠለል መሰረታዊ ፍላጎቶች ተሟልቶላቸው የስነልቦና ስልጠና እየወሰዱ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ሆኖም በተቋሙ ድጋፍ ለማግኘት የገቡ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ተቋሙን ለቀው የወጡ አንዳንድ ሰዎች እንዳሉና በተቋሙ ድጋፍ ለማግኘት የሚፈልጉ የጎዳና ተዳዳሪዎች መኖራቸውንም ቢሮው አስታውቋል፡፡
በመጀመሪያ ዙር ከጎዳና ከተነሱ ዜጎች መካከል ከ92 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከተለያዩ ክልሎች የመጡ በመሆኑ በነበሩበት አካባቢ እንዲቋቋሙ እንደሚደረግም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም የጎዳና ተዳዳሪዎቹ የግል ፍላጎትና አቅም ተፈትሾ በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጎዳና ህይወታቸውን የሚመሩ ዜጎችን ለመደገፍ መንግስት ከመደበው በጀት በዘለለ ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ተቋቁሞ ፣ህብረተሰቡን የሚያሳትፍ 6400A የአጭር ፅፉፍ መልዕክት አገልግሎት ይፋ ተደርጓል፡፡
የጎዳና ተዳዳሪዎችን ህይወት በዘላቂነት ለማቋቋም የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የጋራ ቅንጅታዊ ጥረትና እገዛ እንደሚጠይቅ ቢሮው አስታውሷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2018 ጀምሮ በ11 ከተሞች በተጠናው ጥናት በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ በጎዳና ላይ ህይወታቸውን የሚመሩ 88 ሺህ 960 ዜጎች እንዳሉ ተለይቷል፡፡
ከዚህ ውስጥ 50 ሺህ 820 ያህሉ በአዲስ አበባ ከተማ ወስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡