በአፍሪካ ምድር ሥራ አጥነት ችግር ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ አንገብገቢ አጀንዳ መሆን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።የአህጉሪቱ ኢኮኖሚም በየዓመቱ እየጨመረ ለሚመጣው የወጣቶች የሥራ እድል ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሆነለት አይመስልም። ጥያቄው ሁሉም አገራት ላይ ሲነሳም ‹‹እየሰራን ነው›› የሚለውም የመንግሥት አመራሮች ምላሽ አስቀድሞ የሚታወቅና የተለመደ ሆኗል።
ኢትዮጵያም የሥራ ፈጠራን በማበረታታትና ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ ብትቆይም የዜጎች ‹‹የሥራ ስጡን›› ጥያቄ እና አገሪቱ የምትፈጥራቸው የሥራ እድሎች መጣጣም ቀርቶ መቀራረብ አልቻሉም።
ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት በአንፃሩ መንግሥት የፌዴራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንን በማዋቀር ለሥራ እድል ፈጠራው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።ክልሎችም በየፊናቸው በሥራ እድል ፈጠራው ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው።የኦሮሚያ ክልልም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም ክልሉ ባሳለፍነው በጀት ዓመት በሥራ እድል ፈጠራው ያከናወናቸውን ተግባራት የተገኙ ውጤቶች፣ድክመቶችና ቀጣይ እቅዶች የሚመለከት የተለያዩ ጥያቄዎች በማንሳት ከክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቦጋለ ፈለቀ ጋር ቃል ምልልስ አድርጓል።ቃለ ምልልሱንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ቢሮው የተሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ እቅድና አፈፃፀሙ ምን እንደሚመስል ቢገልፁልን?
አቶ ቦጋለ፡- በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ቢሮው የተሰጠው ተልእኮ የኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን የሥራ እጥነት ቁጥር ሊቀንሱ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ነበር።በዚህም የክልሉ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር የሚችለውን የሥራ እድል በተቻለ መጠን አሟጠን ለመጠቀም ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጠናል።ለተፈፃሚነቱም ልዩ እቅድ በማውጣት በክልሉ የሚገኙ ሥራ አጦችን ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራትን ስናከናውን ቆይተናል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ አስቀምጠን ነበር። ይሁንና በአፈጻጸሙ ሲገመገም ከታቀደውም በላይ ማሳካት ችለናል። ከእቅዱ በላይ ለአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር ችለናል።
ከሥራ ፈጠራው ባሻገር በመንግሥት በኩል የሚሰጡ ተያያዥ ድጋፎች አሉ። ብድር ማቅረብ መቻል አለብን። አጫጭር ስልጠናዎች መሰጠት አለባቸው። ቁጠባን ማሰባሰብ ያስፈልጋል። ኦዲት የሂሳብ አያያዝ አገልግሎቶች መሰጠት ይኖርባቸዋል። ወጣቶቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮ በትኩረትና በስፋት ተሰርቷል።ከሌሎች ደጋፊ ተቋማት ጋር በመሆን አጫጭር ስልጠናዎች ተሰጥተዋል።በእነዚህ ሁሉ መመዘኛዎች የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ውጤቶችን ማግኘት ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- በሥራ እድል ፈጠራ ከተለያዩ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሥራ ማግኘት ያልቻሉ ወጣቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል?
አቶ ቦጋለ፡- ከሥራ እድል ፈጠራው ባሻገር በተለይ የተማሩ ዜጎችን ተሳትፎ በማጎልበት ረገድ ስኬታማ ሥራዎችን ማከናወን ችለናል።ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ተማሪዎች ድርሻ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
ቢሮው ቴክኒክ እና ሙያ እንዲሁም በዲግሪ የተመረቁ ወጣቶችን ለብቻ የሚይዝበት አግባብና አሰራር አለ። አካል ጉዳተኞችን፣ከስደት ተመላሾችን እንዲሁም ሴቶችን ለብቻ ይይዛል።በዓመቱ የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ከ 79 ሺ በላይ የሚሆኑት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተመረቁ ናቸው። ይሁንና በየዓመቱ በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት እየተመረቀ በሚወጣበት ክልል ውስጥ ይሄ በቂ ነው ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የሥራ እድል ፈጠራ ሥራ የሴቶች ተሳትፎ ከዓመት ዓመት ዝቅተኛ ሆኖ ይስተዋላል፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ይህ ምስል ተለውጧል ?
አቶ ቦጋለ፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ቢሆን በሥራ እድል ፈጠራው የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ነው። አፈፃፀማችንም ዝቅተኛ ነው።አቅደን የተነሳነው ለ50 በመቶ ሴቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ነበር።ይሁንና በእቅድ አፈፃፀሙ የሴቶች ተሳትፎ 33 በመቶ አልተሻገረም። ይህ አሳሳቢ ነው።በመሆኑም አስቀድሞ ሴቶችን በማሳመን ጓዳ ውስጥ ከመዋል ወደ መመዝገቢያና ማጣሪያ ጣቢያዎች በመምጣት እንዲመዘገቡ ማድረግ እና በተለየ ሁኔታ በማደራጀት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠይቃል።የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ከእኛ ጋር ተቀራርበውና ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ቢሮው በቁጠባ ማሰባሰብ በብድር አቅርቦት ረገድ ያከናወናቸው ተግባራት እና ውጤታቸውን ቢገልፁልን?
አቶ ቦጋለ፡- በቁጠባ ረገድ በተጠናቀቀው በጀት ዓመቱ ወደ ስምንት ቢሊዮን ብር ለመቆጠብ እቅድ ተቀምጦ ነበር።ይሁንና በእቅድ አፈፃፀሙ ከስምንት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን በላይ መቆጠብ ተችሏል።በዚህም አፈፃፀም ትልቅ ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል።
እንደሚታወቀው ለዜጎች ብድር ማቅረብም ሆነ ማመቻቸት የሚቻለው ቁጠባ ሲኖር ነው።ምንም እንኳን ሰፊ የሆነ ቁጠባን ማሰባሰብ ብንችልም ከብድር አቅርቦትና አሰጣጥ ረገድ ክፍተቶች አሉ።የእቅድ አፈፃፀማችንም ዝቅተኛ የሚባል ነው።ማበደር የተቻለው ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር አካባቢ ነው።ይህም በዓመቱ ከታቀደው 45 በመቶ እንደማለት ነው።አፈጻፀማችን ብድር ላይ ሰፊ ትኩረት ሰጥተን ማሰራት እንዳለብን ያመላክታል።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የብድር አሰጣጥ ቅልጥፍና ደካማ እንደሆነ ይነገራል፣በዚህ ረገድ ቢሮው የሚሰጠው ምላሽ ምንድ ነው?
አቶ ቦጋለ፡- በብድር አሰጣጥ ረገድ በሚፈለገው ፍጥነት ማበደር ባለመቻላችን ቀዳሚ ሆኖ የሚነሳው በታችኛው እርከን ያሉ ቢሮክራሲያዊ አሰራር ነው።በተለይም ብድሩን ለመፍቀድ ቅድመ ሁኔታዎችን ማብዛት ነው።ባለፉት ዓመታት የተመጣበት መንገድ እና የታለፉ ልምዶች የገንዘብ ተቋማትን ያዝ እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል።በዚህ ረገድ አፈፃፀማችን ደካማ እንደሆነ ተነጋግረናል።በጋራም ገምግመናል።በዚህ በጀት ዓመትም ይሻሻላል ተብሎ ይጠበቃል።
ቀደም ሲል የእኛ ብድር አቅራቢ ተቋም ኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር ነው። ማህበሩ ወደ ስንቄ ባንክ ተሸጋግሯል።ወደ ባንክ ቢሸጋገርም እንደ አንድ ኮር ቢዝነስ የወጣቶችን ብድር አቅርቦት ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ይታሰባል። ለዚህም በጋራ አቅደንና በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመለከትናቸውን ክፍተቶች ለመፍታትና በተቻለ መጠን የፋይናንስ ተደራሽነትን ለገጠሩ እና በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ለማድረስ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው።በዚህ ረገድ መሻሻሎች ይኖራሉ ብለን እንጠብቃለን።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል የተሰጡ ብድሮችን በማስመለስ ረገድ ቢሮው ያከናወናቸውን ተግባራት እንዴት ይገለፃል?
አቶ ቦጋለ፡- በዓመቱ በእቅድ ደረጃ ያስቀመጥነው የተሰጠ ብድር መቶ በመቶ መመለስ አለበት የሚል ነው።በእርግጥ ወደ ሥራ የገባነው የበለጠ ግብ ይዘን ነው።ይህን አሳክታችኋል ተብሎ ከተጠየቀ መልሱ ማሳካት አልቻልንም ነው።በበጀት ዓመቱ ከተሠጠው ብድር ውስጥ ማስመለስ የቻልነው 86 በመቶ ነው።ይህም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀም ጥሩ የሚባል ነው።ይሁንና የተሰጠ ብድር መመለስ አለበትና ቀሪ ሥራዎች የሉም ለማለት አያስደፍርም።
በጀት ዓመት የከረሙ ብድሮችን በሚባሉ በተለይ በክልሉ ነባራዊ ሁኔታ የወጣቶች ፈንድ የብድር ስርጭት ጋር በተያያዘ ጥሩ እንድምታዎች አልነበሩም።በጣም በርካቶች የተበደሩትን ይዘው የጠፉበት ሁኔታ አለ። አይመለስም የሚባሉ ብድሮችም ሁሉ ነበሩ።በዚህ ረገድ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር አካባቢ እናስመልሳለን ብለን አስበን ነበር።በዚህ በጀት ዓመት ከአራት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለስ ችለናል።የተመለሰውም 42 በመቶ አካባቢ ነው። ይህ በጣም ትልቅ አፈፃፀም ነው።
አዲስ ዘመን፡- የ42 በመቶ አፈፃፀም ውጤታማ ነው ለማለት ያስደፍራል እንዴ?
አቶ ቦጋለ፡- አፈፃፀሙ ውጤታማ ነው የምንልበት ምክንያት አለን።ማስመለስ የቻልነው ብድር ከሁሉ በላይ የጠፋ ከሚባሉት ወገን ሊካተት የሚችል ስለነበር ነው።ከዚህ ባሻገር በየደረጃው ያለው መዋቅርና አመራር ጠፍተዋል ሲባል የነበረው ብድር ማን ጋር ነው ያለው የሚለውን ማወቅ እና ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራበት ብድሩን ማስመለስ እንደሚችል ማረጋገጥ የተቻለበትን ምህዳር ፈጥረናል። በአጠቃላይ በብድር አመላለስ ረገድ ቀደም ሲል ከነበሩት ዓመታት በተሻለ ውጤታማ ተግባራት ማከናወን ችለናል።ያልተመለሱትም ብድር ቢሆን ቢያንስ ማን ወሰዳቸው የሚለውን መለየት እና ማወቅ ብሎም በመረጃ መያዝ ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ በመሬት አቅርቦት እንዲሁም ሼዶችን ለወጣቶች በማስተላለፍ ረገድ የተከናወኑ ተግባራትን እንዴት ገመገማችሁት?
አቶ ቦጋለ፡- እንደሚታወቀው ከክልሉ ትልቁ አቅም መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚነሳው የግብርና ዘርፉ ነው።ለዚህ ደግሞ መሬት ያስፈልጋል። በበጀት ዓመቱ በከተማም ሆነ በገጠር ከ47 ሺ ሄክታር መሬት በላይ ወጣቶችን በማደራጀት መሬት ማቅረብ ተችላል።ይህም ትልቅ ስኬት ነው።
ሼዶችን በማቅረብ ረገድም በእቅዱ ከተቀመጠው የተቀራረበ አፈፃፀም አስመዝግበናል።1ሺ735 የሚሆኑ ሼዶችን መስጠት ችለናል።ከዚህ ባሻገር በህገ ወጥ መልኩ የተያዙትን በማስለቀቅና ለሚገባቸው ወጣቶች በማስተላለፍ ውጤታማ ተግባራት ተከናውኗል።
ይሄ የቢሮው አፈጻጸም ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸርም ከፍተኛ መሻሻሎች የተዘመገቡበት ነው። በክልሉ ከሚስተዋለው የሥራ እጥነት ችግር ጋር ሲነፃፀር ሰፊ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠይቅ የሚያመላክት መሆኑን መስማማት ላይ ደርሰናል።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች በሥራ እድል ፈጠራው ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ምን ይመስላል?
አቶ ቦጋለ፡- ክልሉ እንደ አገር ካለው የመልክአምድራዊ አቀማመጥና ሃብት አንፃር ለኢንዱስትሪ ምቹ መሆኑ እርግጥ ነው።በክልሉ ከነባር ኢንዱስትሪዎች ባሻገር በርካታ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች እየመጡ ናቸው።በዚህ በጀት ዓመት ውስጥ ተጠናቀው ወደ ሥራ ገበያው የተቀላቀሉ፣ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ኢንዱስትሪዎች አሉ።በየከተሞቹ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ሰፊ የሆነ የኢንዱስትሪ አቅም አለ።
ኢንዱስትሪው እያደገ ነው።ለእነርሱ ምቹ ሁኔታ እስከፈጠርንና ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ ማነቆዎችን መፍታት እስከተቻለ ድረስም በዚህ ረገድ ሰፊ የሥራ እድል እንደሚፈጠር እናምናለን።በዓመቱም ነባር ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር በተለይም ያሉባቸውን ማነቆዎች በመፍታት ለአብነትም የኃይል አቅርቦት፣የማስፋፊያ እንዲሁም ከሰራተኛ ጋር የተያያዘ ጥያቄና ችግሮች በመፍታት ኢንዱስትሪዎቹ ተጨማሪ ሰው ኃይል እንዲፈጥሩ ተሰርቷል።በዚህም አማካኝነት የተለያዩ የሥራ እድሎን መፍጠር ችለናል።በርካታ ወጣቶች ተቀጥረዋል። ተሳትፎአቸው ከፍተኛ ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ በሥራ እድል ፈጠራው ላይ ጎልተው የተስተዋሉ ድክመቶች እና ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ቦጋለ፡- ከሁሉም በላይ ከብድር አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ብዙ መስራት ይቀረናል።የክልሉ የመልማት አቅም በጣም ትልቅ ነው። እያንዳንዱ በክልሉ ውስጥ የሚካሄድ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለሥራ እድል ፈጠራው የራሱ የሆነ አበርክቶ ሊኖረው የግድ ይላል። በሥራ እድል ፈጠራ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን ብንችልም ከክልሉ አቅም አንፃር በሚፈለገው ልክ ሰርተናል፤ ተጠቅመናል ብለን አንወስድም።
የክልሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚፈጥረውን የሥራ እድል አሟጦ የመጠቀም እና የመስራት ድክመንት እንደ አንድ ውስንነት መውሰድ የሚቻል ነው።ከዚህ ባሻገር ሌላኛው ውስንነት በአስፈፃሚ አካላት ዘንድ የማስፈፀም ልዩነት ነው።በክልሉ ከእቅዳቸው በላይ መፈፀምና ከ130 እስከ 160 በመቶ ማሳካት የቻሉና ከእቅድ በታች የፈፀሙ አሉ። በቀጣይ የአፈፃፀም ልዩነት በማጣጣም ስኬታማዎችን የማስቀጠል ደካሞቹን የማሻሻል ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ ነው።
በየደረጃው ያሉ የሥራ እድል ፈጠራ ምክር ቤቶች በተመሳሳይ ሁኔታ እኩል ጊዜ ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ነው ብሎ መውሰድም አይቻልም።እንደ ክልል ያለን ነባራዊ ሁኔታ ግምገማችን ላይ እንዳየነው ምክር ቤቶቹ ተገናኝተው አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ የቻሉት ከ75 በመቶ በማይልቅ ጊዜ ነው ። ይህ ቢቻል ከመቶ በመቶ በላይ መሆን አለበት።ምክንያቱም ትልልቅ አቅጣጫዎችን የሚፈጥር በክልል ያሉትን የሥራ እድል መፍጠሪያ አቅሞች የሚለይ የሚገመግም ስህተት ሲፈጠር የሚያስተካክል አደረጃጀት ነው።ይህ አለመሆኑ ትልቅ ክፍተት ነው ብለን ወስደነዋል። መስተካከልና መጠናከር ይጠበቅብናል።
በተለይ በኢንዱስትሪው በኩል የታቀዱና በርካታ የሥራ እድል ይፈጥራሉ ለተባሉ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የገንዘብ ተቋማቱ በምንፈልገው ፍጥነት ድጋፍ መስጠት አለመቻላቸውም በበጀት ዓመቱ አፈጻጸም የተለዩ ውስንነቶች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በዘንድሮ በጀት ዓመት በሥራ ፈጠራ ምን አቅዳችኋል?
አቶ ቦጋለ፡- በተጠናቀቀው ዓመት የተገኙ ስኬቶችን የማስቀጠል እና ለተስተዋሉ ችግሮች ፈጣን መፍትሄ መስጠት የበጀት ዓመቱ ልዩ ትኩረት የሚሠጠውና ዋነኛ የማጠንጠኛ ተግባር ነው።በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ለመፍጠር አቅደናል።በሥራ ፈጠራው በፆታ ስብጥር 50 በመቶ ለሴቶች በማድረግ እስካሁን የሚታየውን ልዩነት ለማቀራረብ ትኩረት ይሠጣል።
በቁጠባ ረገድም ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዷል።243 ፕሮጀክቶችን በማስተዋወቅ ለባንክ አቅርበናል። በፍጥነት የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተወስኗል።ትልቅ ግብ በመሆኑ ፕሮጀክቶቹን ሥራ ማስጀመር ከቻልን ኢንዱስትራላዜሽኑን ያሳልጠዋል የሥራ እድል ፈጠራውን ያፋጥንልናል።ሞዴል እና የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንፃር ሰፊ ግቦች ተይዘዋል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ቃለ ምልልስ በዝግጅት ክፍሉ ስም እናመሰግናለን።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ. ም