አልማዝ ከማዕድናት ሁሉ የከበረ ሲሆን፤ በሰይፍና በጎራዴ ቢቀላ፤ በመጋዝ ቢገዘገዝ፣ በድንጋይ ቢቀጠቀጥ አልማዝን በዓልማዝ ካልሆነ በስተቀር በሌላ በማንኛቸውም ምድራዊ ቁስ መቁረጥ አይቻልም። ኢትዮጵያም ልክ እንደ አልማዝ ናት። ከጥንት እስከዛሬ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ኢትዮጵያዊያንን ለማዋረድ ያልተቀነባበረ ሴራ የለም። ነገር ግን ኢትዮጵያ ምን ፈተናዋ ቢበዛ ነብር ዠንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን አይቀይርም።
ኢትዮጵያዊ ነጻነቱን ከሚያጣ ከፍ ብሎ አንገቱን ዝቅ ብሎ ባቱን በሰይፍ ቢቀላ ይመርጣል። በዚህም አይበገሬ ማንነቱም ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ጊዚያት ስለነጻነታቸው በአንድነት ቁመው በከፈሉት መራራ መስዋዕትነት የዓለም የጥቁር ህዝብ የነጻነት ተጋድሎ ቀንዲል፤ የድል ብስራት ለመሆን በቅተዋል።
እንደብረት ቀጥቅጦ እንደሰም አቅልጦ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ካንዴም ሁለት ጊዜ ባህር ተሻግሮ የመጣውን የፋሽስት ጣሊያንን ሰራዊት ጀግኖች አባቶቻችን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው አንገቱን አስደፍተው ወደመጣበት መልሰዋል። በዚህ ድላቸውም የመላው ዓለም ተፈጥሮአዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር አድሰዋል፤ በእውነትና በፍትህ ህልውና እና ምልዓት ላይ የተሰካ ትልቅ ጥርስ የተነቀለው … በአድዋ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ድል ነው።
በድል፣ በብሄር ብሄረሰቦች፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በእሴት በወግና በትውፊት የደመቀችው አልማዟ ኢትዮጵያን አንገት ለማስደፋትና ለመውረር የመጣ ወራሪ ሃይል ሁሉ ውርደትን ተከናንቦ ተመልሷል። ኢትዮጵያውያንም በተሰለፉበት የጦር ግንባር ድል እንጂ ሽንፈት ገጥሟቸው አያውቅም። ይህም ኢትዮጵያዊነት መራራ መስዋዕትነት የተከፈለበት፤ ማንም ሊያራክሰው የማይችል፣ በዋዛ ያልመጣ፣ በጀግንነት፣ በድል አድራጊነት፣ በአልበገር ባይነት፣ ተቻችሎ በመኖር እና በጠንካራ አንድነት የታጀበ ነው።
ታዲያ ኢትዮጵያ አልማዝ መሆኗን የተረዱ የምንጊዜም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች፤ “እሾህን በሾህ” እንደሚነቀሰው፤ “አልማዝን በአልማዝ” እንደሚቆረጠው ሁሉ ደደቢት በረሃ የመሰረቱትን አሸባሪው የሕወሓት ባንዳ ቡድን እሽኮኮ ብለው አራት ኪሎ ቤተመንግስት አስገብተውታል። በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ባስቀመጡት አሻንጉሊት መንግስት ባለፉት 27 ዓመታት በእጅ አዙር ኢትዮጵያን ቅኝ ሲገዙ ነበር ማለት ይቻላል።
በዚህም ላለፉት 27 ዓመታት ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ በአራቱም የአገሪቱ ማዕዘን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ህልቆ መሳፍርት የሌለው መከራና ግፍ በአሸባሪው ሕወሓት አገዛዝ ተቀብለዋል። ይህ የሽብር ቡድን ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ዜጎችን ጨለማ ቤት ሲያስር፣ ጥፍር ሲነቅል፣ ሲያኮላሽ፣ ህዝብ ከህዝብ ሲያናክስ፣ የአገር ሃብት ሲመዘብር፣ አገር ሲሸጥና ሲገነጥል ኖሯል። በጥቅሉ ኢትዮጵያዊያን ላለፉት 27 ዓመታት ሰማይ ተደፍቶብን ነበር ማለት ይቻላል።
ነገር ግን ሌሊቱ ይረዝማል እንጂ የማይነጋ ሌሊት የለም። መከራው ይበዛል እንጂ የማያልፍ የለም እና ያ የ27 ዓመት የጨለማና የባርነት አገዛዝ በኢትዮጵያ ህዝብ መራራ ትግልና በለውጡ ቀማሪ የለውጥ ሃይሎች ከተገረሰሰ ሶስት ዓመታት ተቆጥረዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቱ የታየውን እውነተኛ የለውጥ ሂደት በመቀልበስ ዳግም በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግስት በመመስረት ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ለመግዛት የቋመጡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እንዲሁም ባልበላውም “ጭሬ ላበላሽው እንዳለችው” እንስሳ ቀኑ የመሸበት ባንዳው የሕወሓት ቡድን “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም” ቢሆን እንወርዳለን በሚል የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ይገኛል።
ይህ አሸባሪ ቡድን የጌቶቹን ራዕይ ለማሳካት ባለፉት ሶስት ዓመታት ያልገባበት ጉድጓድ የለም። በተለይ ከጥዋት ከማታ ሳያስበው ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት በምን ታምር ተነቅሎ ትግራይ ክልል እንደከተመ እንቆቅልሹ ዛሬ ድረስ ያልተገለጠለት የአሸባሪው ቡድን “እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል” በሚል የሞኞች ብሂል አገሪቱን ለማፍረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።
እንዲሁም በአገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ ለውጡን ቀልብሶ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ፊጥ ለማለት አልያም ኢትዮጵያን አፍርሼ የዘረፍሁትን ሃብት በጎጥ ተከልየ እበላለሁ በሚል እሳቤ ከህዝብና ከአገር የዘረፈውን ገንዘብ አዕምሯቸው ለተደፈነና ሆዳቸው አምላካቸው ለሆኑ አረመኔዎች እየረጨ ህዝብን ከህዝብ ማናከሱን፣ ማፈናቀሉን፣ በጅምላ ሰውን ማስገደሉን ቀጥሎበታል።
መንግስት ተረጋግቶ አገሪቱን በለውጡ ምህዋር አስገብቶ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲና ብልጽግና ጎዳና እንዳያሻግር ባንዳው ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ በእያንዳንዱ ሳምንት በሚፈጽመው የሽብር ድግስ የመንግስት ስራ እሬሳ መቅበር እና ማልቀስ እንዲሆን በማድረግ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ከ113 በላይ ግጭቶችን በመቀስቀስ ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ቤንዚን ሲያርከፈክፍ ከርሟል። ለገዳዮችና ለአራጆች የስልጠና የሎጅስቲክ ድጋፍ በማድረግ በአገሪቱ ሰው ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ ተገሏል። ሴቶችና ህጻናት ሳይቀር በጅምላ ተገድለዋል።
እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ተሰሚነት ያላቸውን ግለሰቦች በሴራ በማስገደል አገሪቱ ወደለየላት የእርስ በእርስ ብጥብጥ እንድትገባ ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። መንግስትን ለመገልበጥ ያልገባበት ቀዳዳ የለም። በጥቅሉ ያጣውን ስልጣን ለማስመለስ አገሪቱን አኬልዳማ አድርጓል።
ጁንታው መንግስት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንደ ፍርሃት በመቁጠር ግፍና በደሉን ግፋ በለው ያለው አገር ገንጣዩ የማፊያው ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ከጀርባው በመውጋት የአገርን ህልውና አደጋ ላይ በመጣል የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽሟል።
በዚህም መንግስት ሳይወድ በግድ በክልሉ ህግን የማስከበር ዘመቻ በገባ በ15 ቀን ውስጥ ጁንታው ተንኮታክቶ ትቢያ ለብሶ ዋሻ ለዋሻ “ከእንቡር ተጋዳለይ ወደ እምቡር ተንከባላይ” ሊቀየር ችሏል። ጁንታው ተራ ሽፍታ ሆኖ በተራዘመ ጦርነት አገር ለማፍረስ ያቀደውን ሴራ የተረዳው መንግስት የትግራይ አርሶ አደር እርሻው ፆም እንዳያድርና የጁንታው እርዝራዦች ጉዳዩን ቆም ብለው እንዲያስቡበት የጽሞና ጊዜ ለመስጠት ክልሉን ለቆ ወጥቷል።
ነገር ግን ጁንታው ሁሌም የሰላም ጸር ነውና ከገባበት ጉድጓድ አፈሩን አራግፎ ወጥቶ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን” በሚል በመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጦርነት አውጇል። በተለይ የትግራይን ህዝብ ከ12 አመት ህጻን እስከ 74 ዓመት አዛውንት ጦር ሜዳ የእሳት እራት በማድረግ የትግራይ እናቶችን ዛሬም እንደትናንቱ የወላድ መካን አድርጓል።
ይህ አሸባሪ ቡድን ትናንት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በሴራ የኢትዮጵያን ህዝብ ሲከፋፍል እንዳልነበር ሁሉ፤ “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ” አበው የሽብር ቡድኑ እኩይ ተግባር እያደር የተገለጠለት የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የምስጋና ይግባውና ጁንታው አሁን ላይ እየወሰደ ባለው የክፋት እርምጃ ኢትዮጵያዊያንን ዳግም እንደ አደዋ ላይለያዩ በአንድነት አቁሟቸዋል።
ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተሰልፈው በድል ላይ ድል እንጂ የሚያስመዘግቡት አፍረው አያውቁም። በዚህ የውስጥ ባንዳ ላይ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ በተባበረ ክንዱ ባሳረፈው በትር የሽብር ቡድኑ ተዳክሞ ምላሱ ብቻ ስለቀረ ዳግማዊ አድዋ የድል ብስራት የምንቀዳጅበት ቀን ቅርብ ነው። ኢትዮጵያን አፍርሰው በኢትዮጵያውያን ውርደት ሊሳለቁ ያሰፈሰፉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን አንገት የምናስደፋበት ቀን እሩቅ አይደለም።
በመሆኑም “ሊነጋ ሲል ይጨልማል ነውና” አሁን ላይ ከውጭም ከውስጥም ፈተናው የበዛው የድል ብስራቱ በመቃረቡ ነው። ለአብነት በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ቬትናም አሁን ላይ ኢትዮጵያ እንደገባችበት አይነት ፈተና ውስጥ ገብታ ነበር። ቬትናም በአንደኛው የዓለም ጦርነት በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ተይዛ የነበረች አገር ናት። ነገር ግን ህዝቦቿ በከፈሉት መራራ መስዋዕትነት ከቅኝ ግዛት ተላቃ ነጻ ሀገር ለመሆን በቅታለች።
ታዲያ መዝረፍ የለመዱ ቅኝ ገዥ አገራት ጥቅማቸው ሲቀርባቸው የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለምና፤ በቬትናም የአሻንጉሊት መንግስት በማቋቋም እንደለመዱት አገሪቱን ለመመዝበር በአገሪቱ በደቡባዊ ክፍል ከመንግስት ያፈነገጠ አንድ አማጺ ቡድን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አቋቋሙ።
ይህ አማጺ ቡድንም ልክ እንደ ጁንታው በአሜሪካ፣ በፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ወ.ዘ.ተ በመሳሰሉ ምእራባውያን አገሮች የሚደገፍ ስለነበር፤ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የነበረውን የአገሪቱን መንግስት ማወኩን ተያያዘው። በዚህም አማጺ ቡድኑ የህዝብ ቅቡልነት በነበረው የቬትናም መንግስትና ህዝብ ላይ ፈርጀ ብዙ ጦርነት ከፈተ። ልክ ጁንታው አሁን ላይ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ላይ እንደከፈተው። ነገር ግን የምዕራባውያን ሴራ የገባቸው ሰፊው የቬትናም ህዝብ አንድነቱን አጥብቆ ከመንግስት ጎን ተሰለፈ።
ሰፊው የቬትናም ህዝብ ድርና ማግ ሆኖ የአማጺ ቡድኑን ሴራ በመመከት አላፈናፍን ማለቱን አሜሪካና ምዕራባውያን ሲረዱ፤ ከእጅ አዙር ጦርነት በግልጽ ወደ ማጥቃት ተዘዋውረው በቬትናም ህዝብ ላይ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጭምር አዘነቡ። በዚህም አሜሪካና ምዕራባውያን በሚሊዮን የሚቆጠር ንጽኋን ቬትናማዊያንን እስከ ወዲያኛው ቢያሰናብቱም ቬትናማውያንን ግን ድል ማድረግ አልተቻላቸውም። ይልቁንም በተባበረ የቬትናም ህዝብ ክንድ አሜሪካና ምዕራባውያን የሽንፈት ጽዋን ተጎነጩ እንጂ። ቬትናሞች ለአገራቸው ነጻነት በአንድነት ተሰልፈው ድል አድርገው ዛሬ ድረስ ነጻነታቸውን አውጀው እየኖሩ ይገኛሉ። የዓለም የነጻነት ተምሳሌትም ለመሆን በቅተዋል።
ከቬትናም ህዝብ ታሪክ የምንማረው ህዝብ አንድ ከሆነ አይደለም የውስጥ ባንዳ ቀርቶ ምንም አይነት ምድራዊ ሀይል የሚያሸንፈው እንደሌለ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ትናንት አደዋ ላይ በአንድነት ተሰልፈን ለዓለም የጥቁር ህዝብ የድል ብስራት ያበሰርን፣ የነጻነት ፋና የለኮስን ነን። ስለዚህ የቬትናምም ሆነ የኛ ታሪክ የሚያስተምረን ኢትዮጵያውያን አንድነታችን አጠናክረን ከያዝን አይደለም የአሜሪካ እና የምዕራባውያን ሴራ ቀርቶ አለን በሚሉት ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ ጦርነት ቢከፍቱ ኢትዮጵያን ማንበርከክ አይችሉም።
አሁን ላይ ከውስጥ በባንዳዎች ከውጭ በፋሽስቶች የተከፈተብን ጦርነት “ይዘገያል እንጂ አህያ የጅብናት” እንደሚባለው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ በቅርብ ቀን ድል ማድረጉ አይቀርም። እንደተለመደው ድሉ የኢትዮጵያ ነው። የተጀመረው እውነተኛ የዲሞክራሲ ግንባታም በለውጡ ሃይል ተጠናክሮ ኢትዮጵያ ወደ ልዕልና ማማው መውጣቷ አይቀሬ ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደጀመረው አንድነቱንና እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል አሸባሪውን ቡድን እስከወዲያኛው ታሪክ ማድረግ አለበት። የለውጡ ሃይልም ልክ እንደቬትናም መንግስት ጥርሱን ነክሶ ከውስጥም ከውጭም የተጋረጠበትን ፈተና ሁሉ ህዝቡን አስተባብሮ በመመከት ለመጪው ትውልድ ነጻነቷ ተጠብቆ፣ የበለጸገች፣ እውነተኛና ዴሞክራሲ እና ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማስረከብ ይኖርበታል። ይህ ደግሞ በለውጡ ማግስት መንግስት እንደ መንግስት ህዝባችንም እንደ ህዝብ የገቡት የድል ቃል ኪዳን ነው ። ይህ ቃል ኪዳን ሙሉ ድል ሆኖ እንደ ሀገር የሚበሰርበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም !
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ. ም