ኢትዮጵያ በዘመናትመካከል ያጋጠሟትን ፈተናዎች እና የተጋጠሟትን የክፋት ኃይላት ሁሉ ድል በመንሣት ታፍራና ተከብራ ነጻነቷን አስጠብቃ ኖራለች። ጀግኖች እናቶችና አባቶች የውጭ ወራሪዎችን ብቻ ሳይሆን የውስጥ ባንዳዎችን በማንበርከክ የዛሬዪቱን ኢትዮጵያ በነፍሳቸው ተወራርደው አቆይተዋታል።
በታሪክ አጋጣሚ ዛሬም ኢትዮጵያ የአጠባጡቷን፣ የአጎረሰ እጇን የሚነክሱ ከሐዲዎች፣ሊያዳክሟትና ሊበትኗት ከቅርብና ከሩቅ ከተነሡ ኃይላት ጋር በመመሳጠር አቆብቁበው ተነስተዋል።ኢትዮጵያ ‘ ከእርሷ በፊት እኔን ‘በሚሉ ልጆቿ መስዋዕትነት ዛሬም እንደ ትናንቱ ድሉ የእርሷ ይሆናል።በእርግጥም የፈተናዎች መደራረብ ፣የወጀቡ ሃይል ሚዛን ፣የውስጥና ውጭም ጠላቶቿ መቀናጀት ተሰባሪ ሊያስመስላት ይችል ይሆናል።ይህ ኢትዮጵያን ከድል አያግዳትም።እስቲ ይመስክር አድዋ !
የአድዋን ድል ለመቀዳጀት አያስችሉ የነበሩት በርካታ ፈተናዎች ነበሩ።በመጀመሪያው ደረጃ የከብት እልቂትን እናስታውስ። ፋሺስት ጣሊያኖች የኢትዮጵያንና የመንግሥቷን አቅም ለማዳከም የሚያስችል ስልት ነድፎ ተንቀሳቅሷል ። ከስልቶቹ አንዱም የሀገሪቱ ሀብት መሠረት የሆነውን ግብርናዋን ማሽመድመድ መጉዳት ነበር።ይህንን ሲያስቡ ግብርናዋን ለመጉዳት የከብት ሀብቷን መጨረስ ነበር ።
የከብት በሽታ እንዲገባ በማድረግ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ‹‹ክፉ ቀን›› በመባል የሚታወቀውን ረሀብና ችጋር አመጣ። የሚበላ ነገር ጠፍቶ ዋልካ አፈርና ሳር ቅጠሉ ሁሉ የተበላበት ዘመን ነበር። ሕዝቡ ደቀቀ፤አለቀ ። ሀገሪቱ ተሽመደመደች።አያቶቻችን የአገርን ህልውና ለማስከበር የተነሱት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነበር።
ሌላው የትጥቅ እና የሎጅስቲክስ ዝግጅት እጅግ ውስንነት ነበር። ፋሽስት ጣሊያን በወቅቱ ኃያላን ከሚባሉ የአውሮፓ ሀገራት አንዱ ነበር። እንደ ኃያልነቱም ከ20 ሺ በላይ ለሆነው እና ላሰለፈው ጦሩ ዘመናዊ መሣሪያ በነፍስ ወከፍ ከማስታጠቁም ባሻገር ሠራዊቱ በወጉ የተደራጀ ዘመናዊ የውትድርና ሥልጠና የወሰደ ባጠቃላይ ከበቂ በላይ የትጥቅ ዝግጅት የነበረው ነበር። በእኛ በኩል የነበረው ደግሞ ባጋጠመው የረሀብና አስከፊ ችጋር የደከመ ሠራዊት ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ የሆነ የስንቅና ትጥቅ አቅርቦት ችግር ነበረበት።
የታጠቀው መሣሪያም ቆመህ ጠብቀኝ በሚባል የሚታወቁ ኋላ ቀር መሣሪያ ሆኖ ይሄንንም ቢሆን የያዙት ከሠራዊቱ እጅግ ጥቂቶቹ ነበሩ ፤ የተቀረው ግን የያዘው ጦርና ጋሻ ጎራዴ ነበር። ሲሰልስ ደግሞ የባንዶች ሚናና የጠላት የመከፋፈል ስልት ትልቁ ፈተና ነበር ።
ፋሽስት ጣሊያን የኢትዮጵያን ሠራዊት ለማዳከም ከተጠቀመበት ስልት ሌላኛው ባላባቶችንና መሳፍንቱን እስከ ራሶች ድረስ እንዲከዱ በማድረግ ከጎኑ ማሰለፍ ነበር። ጥቂት የማይባሉትንም በማስካድ አገራቸውን እንዲወጉ አድርጓቸዋል።እንግዲህ እነዚህና ሌሎች ሊታለፉ የማይችሉ እንደተራራ የገዛዘፉ ከባባድ ደንቀራዎችን ፈተናዎችን በእግዚአብሔር ቸርነት በሐበሻነት ጽናት እናት አባቶቻችን አልፈው ነው የአንባላጌውን፣ የመቀሌውን፣ በመጨረሻም የአድዋን ድል ለመቀዳጀት የቻልነው ።
ይህ ኢትዮጵያዊነት በእሳት የተፈተነ የድል አርማ መሆኑን መገንዘብ ይጠይቃል።የሰው ልጆች የነጻነት ቀንዲል አርማ የሆነውን የአድዋ ድልን መቀዳጀት የተቻለው በውስብስብ ፈተና ውስጥ በማለፍ ፣ የአገርን ክብር ከራስ አስበልጦ በማየት፣የአገር ሉአላዊነት ከውስጥ ልዩነት እንደማይበልጥ አምኖ መዋደቅ በመቻሉ የተገኘ አንጸባራቂ ድል ነው።ታዲያስ ትናንት በአድዋ የታየው ድል ዛሬ የማይደገምበት ምን ምክንያት ይኖራል።ከሆነው ስንነሳ ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ በድል መንገድ ላይ መሆኗን – ይመስክር ህዳሴ !!
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአድዋ ጦርነት በመቀጠል የኢትዮጵያውያን አንድነትና ትብብር የታየበት ዳግማዊ አድዋ ሲሉ ብዙዎች ይገልጹታል። በአድዋ ጦርነት ወቅት አባቶቻችን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ብለው አንድነታቸውን አጠናክረው የውጭ ወራሪን በመመከት ጊዜ የማይሽረው ታሪክ ሰርተው ዛሬን አስረክበውናል።
በእኛ ትውልድ ደግሞ በህዳሴ ግድብ /በልማቱ/ ተደግሟል።በተለይ ደግሞ ከፍትህም ከርትዕም ያልተዛመደው የግብጽ እና ሱዳን ጩኸት የግድቡን ግንባታ ለማሰናከል ለሚደረጉ ጥረቶች እጅ ሳይሰጥ ሁለተኛውን ዙር 13ነጥብ4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ሙሌት ማከናወን ተችሏል ።
የህዳሴው ግድብ የግንባታ ሂደት ለማሰናከል አገሪቱን ውጥረት ውስጥ ለማስገባት ከግብጽ እና ከሱዳን በበለጠ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በመሪ ተዋናይነት መሳተፋቸው የችግሩን ክብደት ያስረዳናል ።ነገር ግን በፈተና ብዛት ፣በወጀቡ ክብደት ፣በጠላት መብዛት የማይሸበረው ኢትዮጵያዊ መንፈስ በጽናት በመቆም ዛሬም የአባቶቹን ድል ደግሞ አሳይቷል።ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ በድል መንገድ ከመጓዝ አንዳች ኃይል እንደማያስቆማት በህልውና ጦርነቱን ቀጥለን ስንመለከት – ትመስክር ወያኔ!!
የፋሽስት ጣሊያን የመንፈስ ልጆች በሰሜን እዝ ላይ የመጀመሪያዋን ቃታ በመሳብ የጦርነት አዋጅ ከመንፋታቸው አስቀድመው ያሰቡት ምን እንደነበር እናስታውስ። የኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነው መሳሪያም ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነበር ። የሀይል ሚዛኑ ማለትም የኢኮኖሚ ዝግጁነት ፣የወታደራዊ ኃይል ዝግጁነት ፣የመንግሥታዊ ውቅር አንጻር ትግራይ ክልል የነበረውን ከሌሎች ክልሎች ሲወዳደር የሚመጣጠን አልነበረም።
በኢትዮጵያ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ላይ በብሄር ፣በሃይማኖት ፣በድንበር ወዘተ ግጭቶች በመፍጠር ማዕከላዊ መንግሥቱን በውጥረት እንዲቆይ አድርገዋል።ዝግጅቱ በዚህ ብቻ አላበቃም ። ‘ባንኩም ታንኩም ‘ በእጃቸው መሆኑን በመገንዘብ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲፈጠር የኢኮኖሚ አሻጥር በመስራት ህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ ፊቱን እንዲያዞር የቤት ሥራ ሲሰሩ ነበር።
የፋሽስት የመንፈስ ልጆች ሸፍጥ ከአገር ተሻግሮ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከሚሏቸው አገራት ጋር በመጣበቅ አገሪቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማፍረስ ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል።አገርን ለማጥፋት ይህን የመሰለ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ነበር ጦርነቱን የጀመሩት።
ኢትዮጵያ ትናንትም በብዙ ፈተናዎች ተሸብባ ክብሯን አሳልፋ ሰጥታ አታቅም። ኢትዮጵያ ‘ ከእርሷ በፊት እኔን ‘በሚሉ ልጆቿ መስዋዕትነት ዛሬም እንደ ትናንቱ ድሉ የእርሷ መሆኑን በአፋር ፣በአማራ ክልል በተደረገው የህልውና ጦርነት አስመስክራለች።
የፈተናዎች መደራረብ ፣የወጀቡ ሃይል ሚዛን ፣የውስጥና ውጪም ጠላቶቿ መቀናጀት ተሰባሪ ሊያስመስላት ይችል ይሆናል።ይህ ኢትዮጵያን ከድል አያግዳትም።ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ በድል መንገድ!! መጓዟንም ትቀጥላለች።ድል አብሳሪ በሆኑ ልጆቹዋ ነገም ለትውልድ የሚተርፍ የድል ብስራት እንሰማለን ።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ. ም