ድል በብዙ መልኩ ዋጋ ተከፍሎ የሚገኝ የብስራት ቃል ነው ። በዋጋ የሚገዛ በመሆኑም ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው። ድሉ ከግለሰብና ከቡድን መንፈስ ከፍ ብሎ ማህበረሰብን እንደ ማህበረሰብ ፤ ሀገርንም እንደ ሀገር የሚመለከት ከሆነ ደግሞ የሚያስከፈለውም ዋጋ ሆነ የድሉ ትርጓሜ ሀገራዊና ማህበረሰባዊ ብስራት ተደርጎ ይወሰዳል። ድሉም ለትውልዶች የሞራል አቅም ከመሆን ባለፈ ትውልዶችንም ባለ ታሪክ የሚያደርግ ይሆናል።
ድል በባህሪው ውጤት ከመሆኑ አንጻር ፤ባለድል ሆኖ በታሪክ ውስጥ ለመገለጽና በታሪክ ምእራፎች ውስጥ ሰፊ ስፍራ ለማግኘት እንደ ሀገርና ህዝብ የድል አምጪ እሴቶች ባለቤት መሆን ፤ ከዚህም በላይ እነዚህን እሴቶች በማሳደግ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማሸጋገር ያስፈልጋል ።
የእነዚህ የድል አምጪ እሴቶች ባለቤት የሆነ ማህበረሰብ በህይወት ጉዞ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች የሚጋፈጠው በድል ቃል ኪዳን ውስጥ ሆኖ ነው ።ይህ ደግሞ በአብዛኛው ከይቻላል የአሸናፊነት መንፈስ የሚቀዳ በመሆኑ የድል ጉዳይ ይዘገይ ይሆናል እንጂ የሚቀር አይሆንም።
ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ካጋጠሙንና እያጋጠሙን ካሉ ተግዳሮቶች አንጻር ሕይወታችን በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞሉ ናቸው። እነዚህን ተግዳሮቶች በድል ተሻግረን ዛሬ ላይ እንደ ህዝብና ሀገር መድረስ የቻልነው አብዛኛው ማህበራዊ እሴቶቻቸው ለድል ቅርብ የሚያደርጉን በመሆናቸው ነው።
አንድም ማህበራዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን በይቻላል የአሸናፊነት መንፈስ የተቃኙ መሆናቸው ፤ ከዛም በላይ በዚህ የተቃኙት እነዚህ እሴቶቻችን በየዘመኑ የአሸናፊነት አቅም ሆነው በተጨባጭ ማየታችን እና የሀገራዊ ኩራት ምንጭ የመሆናቸው እውነታ ነው።
በቀደሙት ዘመናትም ሆነ ዛሬም ቢሆን በብዙ መልኩ እንደ ሀገር አበቃላቸው የተባልነውን ያህል ይህንን የሟርት ቃል የሚያመክኑ ብዙ የድል ብስራት ያስተናገድነው ከድል ጋር ባለን ቃል ኪዳን ነው። ይህ ደግሞ እንዲሁ በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን በየዘመኑ ትውልዶች በከፈሉት ከፍ ያለ መስዋዕትነት የተገኘና ከማንነታችን ጋር በታሪክ የተሳሰረ ስለሆነ ጭምር ነው።
እነዚህ በየዘመኑ ያስተናገድናቸው የድል ቃል ኪዳን ብስራቶች በቀላሉ የተገኙ ሳይሆን በይቻላል እና በአሸናፊነት መንፈስ በተከፈሉ ብዙ እና ከፍ ባሉ መስዋእትነቶች የተገኙ ናቸው ።የብስራት ድምጾቹም ድሉን እንደ ሀገርና ህዝብ አጣጥመን ለማለፍና በታሪካችን የጎላ ስፍራ እንዲይዝ በማድረግ ትውልዶች በብዙ የተማሩባቸው ናቸው። ይህም የድል አድራጊነት መንፈሱ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር አድርጎታል።
ዛሬ ላይ ቆመን ነገን አሻግረን የብልጽግና ህይወትን ተስፋ ስናደርግም ሆነ ተስፋችንን በቋንቋ ስንገልጽ በዚሁ የይቻላል የአሸናፊነት መንፈስ ላይ ሆነን ነው።ተስፋችን ውስጥ ድሉ ቃል ኪዳን ሆኖ አለ። የድሉ ብስራት ቀኑ ግን የሚወሰነው ለድል ቃል ኪዳኑ ባለን ቁርጠኝነትና ከዚህ በሚመነጨው ተጨባጭ ተግባራችን ነው።
እንደ አገር አሁን ላይ እያጋጠመን ያለው ተግዳሮት እና ከዚህ የሚመነጨው ፈተና ሁሉ ይህን በእጃችን ያለውን በቃላችን የታሰረውን ድል ለማስጣል የሚደረግ መሆኑ ግልጽ ነው። ፈተናዎቹ ግን የቱንም ያህል ፈተና ቢሆኑ በቃላችን ውስጥ ካለው የድል ቃል ኪዳን የበለጡ ሊሆኑ አይችሉም፤ መሆንም የሚያስችል አቅምም ቁመናም የላቸውም።
እየተፈተንን ያለነው በያዝነው የድል ቃል ኪዳናችን ልክ ነው ።ፈተናዎቹ ብዙ ሊገዳደሩን ቢችሉም ለድል ቃላችን ስኬት ባለን ቁርጠኝነት ልክ ፈተናዎቹን እያሸነፍን፤ የአሸናፊነት ጉዟችንን አስጠብቀን የመጨረሻው የድል ቃል ኪዳን ብስራታችንን ማሰማታችን አይቀሬ ነው ! በአጠቃላይ በአምላኳ እርዳታና በህዝቦቿ ብርቱ ጥረት የኢትዮጵያ የድል ብስራት ቅርብም ተጨባጭም ነው!
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ. ም