በሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ከአራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ ተከፍሏል

– በኮሪደር ልማቱ 79 የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ይገነባሉ

አዲስ አበባ፦ በሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት በመሬትና ካሳ ምትክ እስካሁን ድረስ ብቻ ከአራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ እንደተከፈለ ተገለጸ። በኮሪደር ልማቱም 79 የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች እና 114 የታክሲ እና አውቶቡስ መጫኛ እና ማውረጃን ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራተኛ ዓመት ሶስተኛ መደበኛ የካቢኔ ስብሰባው ሁለተኛ ኮሪደር ሥራን በጥልቀት ገምግሟል ። ግምገማው በዋናነት ትኩረት ያደረገው የልማት ተነሺዎች የተስተናገዱበትን አግባብ መሆኑን ተመልክቶ፤ በዚህም ለግል ተነሺዎች በካሳ የሶስት ዓመት የቤት ኪራይ እና ምትክ መሬት መውሰዳቸውን እንዲሁም የትራንስፖርት አቅርቦትና የሞራል ካሳ በሕጉ መሠረት የተከፈለ መሆኑን በኮሪደር አስተባባሪዎች ሪፖርት ቀርቧል።

በተጨማሪም መሬት እና ካሳ ምትክ እስካሁን ድረስ ብቻ ከአራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ መከፈሉን፤ የሁለት ዓመት የቤት ኪራይ መከፈሉን እና ቀሪ ተነሺዎችም ቅድመ ዝግጅት ሂደት ካቢኔው በጥንካሬ ገምግሟል ።

በሌላ በኩል መረጃን የሚያዛቡ እና ሀገር እንዳትለማ ውዥንብር በሚፈጥሩ የተለያዩ ዝንባሌዎች የሚያሳዩ የመረጃ ምንጮችን እና አካላት ላይ ሕጋዊ ርምጃ መወሰድ እንደሚገባ ካቢኔው በአጽንዖት መገምገሙን አስታውቋል።

የልማት ተነሺዎች የማህበራዊ ኑሯቸው ሳይበታተን እድር ፤ ማህበር እና አብሮነታቸው የመሠረቱት ማህበራዊ መስተጋብር እንደተጠበቀ የተስተናገዱበት አግባብ እና ከከተማ እስከ ፌዴራል ተቋማት የመሠረተ ልማት ቅንጅት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ካቢኔው በጥንካሬ ተገምግሟል ሲል ጠቅሷል ።

የመንግሥት ቤት የሚኖሩ የነበሩ የተነሱበት አግባብ መሠረተ ልማት የተሟሉላቸው ስለመሆኑ እና አንዳንድ ሳይቶች ላይ የመንገድ ደረጃውን ለማሻሻል ግንባታ እየተካሄደ ስለመሆኑ ሪፖርት ቀርቦ ካቢኔው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ውሳኔ አስተላልፏል።

ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ 2 ሺህ 879 ሄክታር ስፋት፤ 135 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ 240 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ 237 የእግረኛ መንገድ ፣ 32 የህፃናት መጫዎች ቦታዎች ፣ 79 የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ፣ 114 የታክሲ እና አውቶቡስ መጫኛ እና ማውረጃን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

58 የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎች፣ 368 ሄክታር አረንጓዴ ልማት ሽፋን ያላቸው ቦታዎች፣ የ 111 ኪሎ.ሜትር ሳይክል መንገድ ፣ 17 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ 106 የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ 121 ኪሎ.ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ፣ 182 ኪ.ሜ የፍሳሽ ማስወገጃ (ድሬኔጅ) መስመር ፣ 50 የተሽርካሪና እግረኛ መተላለፊያ ፣ 75 ኪሎ .ሜትር የድጋፍ ግንብ (ሪቴይኒንግ) ሥራዎችን የሚያካትት ነውም ተብሏል ::

ይህንኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ክትትል ማሳደግ፤ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ የተተገበሩ የ አንደኛ ዙር ኮሪደር ልማት ልምዶች ተቀምረው ለሁለተኛው ዙር በተሻለ ብቃት መሥራት እንደሚያስፈልግ ፤ ቅንጅታዊ አሠራርም በተጠናከረ መልኩት አሳድጎ በጥንካሬ አሁን ካለው በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ካቢኔው አሳስቧል ሲል አስታውቋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You