የአየር መንገዱን ተቋማዊ ግዝፈት የሚያጎላ ተጨማሪ ስኬት!

የብሄራዊ ክብራችን መገለጫ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከከፍታ በላይ ከፍ ብሎ እየበረረ ያለ የሕዝብ እና የሀገር አለኝታ ነው። አየር መንገዱ አሁን ላይ በአፍሪካ ቀዳሚ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከ100 አየር መንገዶች 36ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም መዳረሻዎቹን በማስፋት በሀገር ውስጥ በሚሰጣቸው አገልግሎቶቹ የዜጎች አለኝታ መሆን የቻለ ነው ፡፡

አየር መንገዱ ከምስረታው ጀምሮ ላለፉት 78 ዓመታት የኢትዮጵያን ባንዲራ ከአድማስ በላይ በማውለብለብ የሀገር እና የሕዝብ ባለውለታ ነው። በእነዚህ ዓመታትም ከፍተኛ ውድድር ባለበት የአቬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ በስኬት መቆየት የቻለ፣ ከሀገር አልፎ የአፍሪካ ኩራት የሆነ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ ብቃት መሳያ ተደርጎ የሚወሰደው አየር መንገዱ፣ በስሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ ያተረፈ የበረራ ትምህርት ቤት፣ ግዙፍ ሆቴል፣ የአውሮፕላን ጥገና ተቋም፣ ለበረራ የሚያስፈልጉ ምግቦችን የሚያዘጋጅ ድርጅት / ካተሪንግ/ ባለቤት ነው።

መንገደኞችንና ዕቃዎችን በማጓጓዝ በዓለም አቀፍ ፣ በአፍሪካ እና በሀገር ውስጥ በርካታ መዳረሻዎች ያሉት፤ ኢትዮጵያዊ በሆነው መስተንግዶው ከፍተኛ ከበሬታ ያተረፈ እና ተመራጭ የሆነ ፣ በዚህም በየጊዜው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የዕውቅና ሽልማቶችን ማግኘት የቻለ ነው።

በኮቪድ 19 ወቅት ሁሉም አየር መንገዶች ሊባል በሚችል መልኩ ሥራ ባቆሙበት ወቅት፣ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው ያጋጠመውን ፈተና ወደ መልካም ዕድል በመለወጥ ፣ ለወረርሽኙ ተጠቂዎችና የህክምና ተቋማት መድኃኒትና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማጓጓዝ ከፍ ያለ ከበሬታን አትርፏል።

ራሱን ዘመኑ በደረሰበት የአቪየሽን ቴክኖሎጂ በማዘመን ፣ ተወዳዳሪነቱን በየጊዜው እያሳደገ፣ ለረጅም ዓመታት በኢንዱስትሪው ውስጥ በስኬት መቆየት የቻለ ነው። አዳዲስ አውሮፕላኖችን ቀድሞ በማዘዝ እና ወደ ሥራ በማስገባት ከሌሎች ገናና አየር መንገዶች በቀዳሚነት የሚጠቀስም ነው።

አየር መንገዱ ሰሞኑን የተረከበው ‹‹ኤር ባስ ኤ 350- 1000 ለዚሁ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። አውሮፕላኑ ወደ ሥራ መግባቱ በአቪየሽን ቴክኖሎጂ ያለውን ቀዳሚ ስፍራም የበለጠ የሚያጠናክርለት እንደሆነ ይታመናል።

አውሮፕላኑ ዘመኑን የዋጁ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት መሆኑ፣ ለመንገደኞች የበለጠ ምቾት ይዞ መምጣቱ፣ ነዳጅ ቆጣቢ እና በአካባቢ ላይ ሊደርስ የሚችልን ብክለት የሚቀንስ መሆኑ፤ አየር መንገዱ ይዞት ለመጣው ስኬት ተጨማሪ ጉልበት የሚሰጠው ነው። ለአፍሪካ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ዘላቂነትም ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ነው።

ለአፍሪካ የአቪየሽን ዘርፍ አዲስ ደረጃን ይዞ የመጣ፣ የአየር መንገዱን የ2035 ራዕይ ለማሳካት ለሚከናወኑ ተግባሮች ትልቅ አቅም በመሆን እንደሚያገለግል፤ ይህም አየር መንገዱ በአቪየሽን ኢንዱስትሪ ያለውን ከፍታ አስጠብቆ በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል የሚያስችለው ነው። የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት ያለውን ቁርጠኝነትም በተጨባጭ ያመላከተ ነው፡፡

አየር መንገዱ አሁን ላይ በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን፤ በአፍሪካ ሁለተኛ የሆነውን አየር መንገድ በእጥፍ የሚበልጥ አቅም በመፍጠር ላይ የሚገኝ ፤ በቀጣይ በዓመት ከ100 እስከ 130 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ ፤ በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ መሆን ብቻ ሳይሆን፤ ባለትልቁ አውሮፕላን ማረፊያም ይሆናል።

ይህም አየር መንገዱ አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ክብርና ዝና በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን አስተዋጽኦ ወደላቀ ደረጃ የሚያሻግር፣ ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ስትራቴጂክ አቅም ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል ተቋማዊ ግዝፈት የሚፈጥር ተጨማሪ የስኬት ታሪክ ምእራፍ ነው!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You