“የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ያወጣሁት በፍላጎቴ ነው።መታወቂያው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል መጠቀም የሚቻልበት በመሆኑ መታወቂያውን ለመመዝገብ የነበረኝ ዝግጁነትና ጉጉት ከፍ ያለ ነው” ይላሉ አቶ ረቂቅ በኃይሉ።
የቀበሌ መታወቂያ ነዋሪ መሆን እና የመሳሰሉትን ቅድመ ሁኔታዎች አሉት።ፋይዳ ግን ማንነትን በደም ዓይነት፣ በዓይን ብሌን፣ በዐሻራ እና በመሳሰሉት መንገዶች ያረጋግጣል ያሉት አቶ ረቂቅ፤ “ኢትዮጵያዊነቴን የሚገልጥ መታወቂያ ስላገኘሁ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።
“የቀበሌ መታወቂያ ሳይኖረኝ በወር ከ10 ሺህ ብር በላይ ለመንግሥት ግብር እከፍላለሁ።ይህ ማለት መንግሥት ዕውቅና ሳይሰጠኝ ከእኔ ግን ተገቢውን ጥቅም እያገኘ ነው ማለት ነው።ይህም ኢ – ፍትሃዊ በመሆኑ እንደዜጋ እኩል ተጠቃሚ እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ነበር። አሁን ግን በዜግነቴ ብቻ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ሆኛለሁ” ነው ያሉት።
መንግሥት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የያዘ ሰው ማንነትን በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ መፍቀዱን ሲሰሙ እንደተደሰቱ ገልጸው፤ መንጃ ፍቃድ ለማውጣት ወደ ተለያዩ ማሠልጠኛ ተቋማት እንደሄዱ ተናግረዋል።
ሆኖም በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ማግኘት እንደማይችሉ በሰሙ ጊዜ ደስታቸው መጨናገፉን ገልጸው፤ በአሁኑ ጊዜ ግን በመታወቂያው የመንጃ ፈቃድ አገልግሎት ማግኘት ተችሏል። ይህም የበርካቶች ተጠቃሚነትን ያንጸባረቀ እንደሆነ ተናግረዋል።
መታወቂያው በኢንተርኔት አማካኝነት በመላ ሀገሪቱ የተሳሰረ በመሆኑ ሰርቆ ማምለጥ፤ በተለያየ ማንነት የሀገርን ሀብት መበዝበዝና ከወንጀል ነፃ መሆን የመሳሰሉ ችግሮችን ለመከላከል ያግዛል ብዬ አስባለሁ ሲሉም ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በመታወቂያው አገልግሎት አንሰጥም ከሚሉ ተቋማት ጋር ስምምነት ማድረግ ካልተቻለ በሕግ ማስገደድ ይገባል ነው ያሉት።
ከምዝገባው ጎን ለጎንም በበይነመረብ የሚኖረውን ትስስር በማጠናከር የአገልግሎቱን ተደራሽነት ማሳደግ እንደሚገባ የገለጹት አቶ ረቂቅ፤ በእርግጥ አሁን ጥቂት የባንክ እና የፋይናንስ፣ የመንጃ ፈቃድ እና የሌሎች ተቋማት አገልግሎቶች በመታወቂያው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ወደፊት መታወቂያው ፈርጀ ብዙ ጥቅም ይኖረዋል።ከዚህ አኳያም ሁሉም ሰው ፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ እንዲያወጣም መክረዋል።
መታወቂያውን የሚሰጠው አካልም ግለሰቦችን ተመዝገቡ ከማለት ባለፈ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ስምምነት በመፍጠር ሕዝቡ ጠቀሜታውን በመገንዘብ መታወቂያውን እንዲያወጣ መደረግ ይኖርበታል።ይህንን በማያከብሩ ተቋማትና ግለሰቦች ላይም የማያዳግም ርምጃ ሊወሰድ ይገባል ነው ያሉት።
በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ቃልኪዳን አብርሃም በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር ይሠራል። ይህም የዜጎችን ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።
ለአብነት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ከባንኮች ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ከክልል ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ዜጎች የባንክ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታዎች መዘርጋት ተችሏል። ከዚህ በፊት አገልግሎቱን ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታዎች እንደነበሩ ገልጸዋል።
ሌላው ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በተደረገው ስምምነት በግብር ከፋዩና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ግልጽ በማድረግ ሕገወጥ ተግባራትን መቀነስ ተችሏል። በቀጣይ የግብር ቁጥርንና የፋይዳ መታወቂያን የማስተሳሰር ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ስደተኞች የንግድ ሥራ ለመጀመር እና የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማግኘት የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸው ነበር። አሁን ግን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ከተለያዩ ተቋማት ጋር ባደረገው ስምምነት የፋይዳ መታወቂያን በመያዝ አገልግሎቱን በቀላሉ እያገኙ መሆኑን ይናገራሉ።
የፋይዳ ቁጥር በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ለሚያሟሉ ነዋሪዎች የሚሰጥ ባለ 12 አኃዝ ልዩ መለያ ቁጥር ነው። ይህንን ቁጥር (ዲጂታል መታወቂያ) የያዙ ነዋሪዎች በሀገሪቱ ውስጥ ማንነትን በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት ያስችላል።
ከዚህም ባለፈ የባንክ ሒሳብ ለመክፈት፣ ሥራ ለማመልከት እና የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት እንዲሁም ለተለያዩ ዓላማዎች ለመጠቀም የማንነት መሠረታዊ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል። የሚቀርበውም መረጃ ትክክለኛ መሆኑን በማረጋገጥ ከመጭበርበር እና ተመሳሳይ ድርጊቶች ለመከላከል ይረዳል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ግለሰቦች ማንነታቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችል እና ለአገልግሎት አቅራቢዎች ታማኝ ዲጂታል ማረጋገጫ ሆኖ እንዲያገለግል ተደርጎ የተዘጋጀ ነው። ከ2014 ዓ.ም በፊት በኢትዮጵያ በባዮሜትሪክስ የታገዘ መታወቂያ እንዳልነበረ ይታወቃል። በአሁኑ ጊዜ ግን በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አማካኝነት የተመዝጋቢዎች ቁጥር ከዘጠኝ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ደርሷል።
ይህም ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዋሪዎችን የተመጠነ የባዮሜትሪክ እና ዴሞግራፊክ መረጃ በመሰብሰብ “አንድ ሰው አንድ ነው” በሚል መርህ አንድን ሰው ልዩ በሆነ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ሥርዓት ነው።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በ2018 ዓ.ም መጨረሻ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ90 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት ማቀዱን ያስታወቀ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባን በተለያዩ ቦታዎች እያከናወነ እንደሚገኘ ተገልጿል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም