-ኢትስዊች ካፒታሉን ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችሏል
-ከአንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ አስመዝግቧል
አዲስ አበባ፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሀገሪቱ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ከፍተኛ እምርታ አሳይቷል ሲሉ ኢትስዊች ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ደስታ ገለጹ። ኢትስዊች ካፒታሉን ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረሱንና ከአንድ ቢሊዮን 55 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውቀዋል።
የኢትስዊች አክሲዮን ማህበር የባለአክሲዮኖች 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በትናንትናው እለት ተካሂዷል።
የኢትስዊች አክሲዮን ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ደስታ ዓመታዊ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የመንግሥት ለዲጂታል ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው። በዚህም የሀገሪቱ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ከፍተኛ እመርታ አሳይቷል።
ኢት ስዊችም ብሔራዊ ስዊች እንደመሆኑ በፋይናንስ ተቋማት መካከል ተናባቢነትን በመፍጠር፤ ዘመናዊ ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና አካታች ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት በመፍጠር ሂደት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ኢትስዊች አክሲዮን ማህበር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸም አመርቂ መሆኑን ጠቁመው፤ በገቢ ማስገኛ፣ በኦፕሬሽን ሥራዎች፣ በፕሮጀክት ትግበራ እና በፖሊሲ ዘርፍ ላይ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
ማህበሩ ባለፈው ዓመት እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ የተፈረመ ካፒታሉን ወደ ሁለት ቢሊዮን 987 ሚሊዮን 832 ሺህ ብር እንዲሁም የተከፈለ ካፒታል ወደ አንድ ቢሊዮን 789 ሚሊዮን 390 ሺህ ብር ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
ማህበሩ የተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የኦፕሬሽን ገቢው አንድ ቢሊዮን 130 ሚሊዮን 69 ሺህ 398 ብር ማድረሱንና ከታክስ በፊት አንድ ቢሊዮን 55 ሚሊዮን 312 ሺህ 826 የተጣራ ትርፍ ማዝመዝገቡን ገልጸው፤ ይህም ካለፈው ዓመት የትርፍ መጠን ጋር ሲነፃፀር የ97 በመቶ ጭማሪ ያሳያል ብለዋል።
የትርፍ መጠኑ መጨመሩን ተከትሎ የአንድ ባለ አንድ ሺህ ብር አክሲዮን የትርፍ ድርሻ ወደ 73 ነጥብ 7 በመቶ አድጓል። ይህም ሊሆን የቻለው የኩባንያው ገቢ እንዲጨምር በመሠራቱ እና ጥንቃቄ የተሞላበት የወጪ አስተዳደር ተግባራዊ በመደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኦፕሬሽን ሥራዎችን በተመለከተ በሒሳብ ዓመቱ በአጠቃላይ የብር መጠኑ 399 ነጥብ 63 ቢሊዮን እንዲሁም ብዛቱ 146 ሚሊዮን 407 ሺህ 829 የሆነ የኤቲኤም እና የፖስ አገልግሎት የተሰጠ መሆኑን አመልክተው፤ ከዚህም ውስጥ የብር መጠኑ 270 ነጥብ 7 ቢሊዮን እንዲሁም ብዛቱ 49 ነጥብ 69 ሚሊዮን የሆነ በሞባይል ከፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ወደ ሌላ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገንዘብ የማስተላለፍ (PP2P transfer) አገልግሎት መከናወኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ኩባንያውን ከገጠሙት ተግዳሮቶች መካከል ሕጋዊ አግባብነት የሌላቸው የግብር ውሳኔዎች የሚጠቀሱ ናቸው ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ለዚህም አስተዳደራዊ እንዲሁም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ሕጋዊ መፍትሔ እንዲሰጠው እየተሞከረ ይገኛል ብለዋል።
ከእርስ በእርሱ ተናባቢ ከሆነ የኤቲኤም እና የፖስ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የእርስ በእርስ ተናባቢነትን ወደ ኋላ የሚጎትቱ አሠራሮችን ተግባራዊ የሚያደርጉ የፋይናንስ ተቋማት መኖራቸው ሌላኛው ተግዳሮት እንደሆነ አውስተው፤ የፋይናንስ ተቋማት እነዚህን አሠራሮች እና ተግባራት በማስቀረት ዘመናዊ እና ደረጃውን የጠበቀ የክፍያ ሥርዓት ለመፍጠር ተቋማዊ ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም