ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ሰብሎችን መሰብሰብ ይገባል

አዲስ አበባ፡- በህዳር ወር በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመኸር ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ ሰብሎችን የመሰብሰብና በአግባቡ የመከመር ተግባራትን ማከናወን እንደሚኖርበት የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስትቲዩቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በያዝነው የህዳር ወር በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር ስለሚችል በመኸር ሰብል ስብሰባና ድህረ ሰብል ስብሰባ ተግባራት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል አርሶ አደሮችም ሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ልዩ ትኩረት በመስጠት የደረሱ ሰብሎችን በሚኖሩት ደረቅ ሰሞናት የመሰብሰብና በአግባቡ የመከመር ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል።

በሚቀጥሉት የህዳር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ለዝናብ መኖር አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እንደሚኖሩ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ እና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጿል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በተለይም በደቡብ ምዕራብና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋና ሰፊ ቦታዎችን የሚያካትት ከቀላል እስከ ከመካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አመላክቷል።

በሌላ በኩል በመካከለኛው፣ በምስራቅ፣ በሰሜን ምስራቅ፣ በሰሜን እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎች ይገልጻሉ ብሏል።

ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት በተለይም ከሳምንት አጋማሽ በኋላ አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት ከአማራ ክልል በምዕራብ፤ ሰሜን፣ ማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር፣ ምስራቅ፤ ምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም እና ባህርዳር ዙሪያ፤ ሰሜንና ደቡብ ወሎ) ዋግህምራ፤ ሰሜን ሸዋ፣ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን፣ ከትግራይ ክልል የሰሜን ምዕራብ፤ የምዕራብ፣ የደቡብና የደቡብ ምስራቅና ዞኖች፣ ከአፋር ክልል ፋንቲ፤ ማሂ፣ ሃሪ፣ እና ጋቢ ዞኖች ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ)) አዲስ አበባ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች በተለይም በጥቂት ቀናቶች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች የሚያመላክቱ መሆኑን አመልክቶ፤ በሚኖሩት ደረቅ ቀናቶች የደረሱ ሰብሎች መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ይጠቁማል።

በሚቀጥሉት የህዳር ሁለተኛው አስር ቀናት የሚኖረው እርጥበት ዘግይተው ተዘርተው በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎች እንዲሁም በመኸር ወቅት መጨረሻ ላይ በአፈር ውስጥ በተከማቸ እርጥበት በመታገዝ ለተዘሩ እንደ ሽንብራ እና ጓያ ለመሳሰሉት የጥራጥሬ ሰብሎች የተሟላ እድገት እንዲኖራቸው ከማድረግ አንፃር አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብሏል።

አርሶ አደሮች በወቅቱና የአየር ሁኔታ ምቹነትን ባገናዘበ ሁኔታ ሰብሎችን መሰብሰብ ያስፈለጋል ብሏል ኢንስትዩቱ በመግለጫው።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You