“የአዲስ አበባ ውሃ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው ገቢያችንና የውጭ ምንዛሬ አቅማችን ሲያድግ ነው” – አቶ ፍቃዱ ዘለቀ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የውሃ አቅርቦትና ስርጭት ምክትል ሥራ አስኪያጅ

አዲስ አበባ፦ አዲስ አበባ ከንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር የምትወጣው ገቢያችንና የውጭ ምንዛሬ የማግኘት አቅማችን ሲያድግ መሆኑን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የውሃ አቅርቦትና ሥርጭት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ዘለቀ አስታወቁ።የንጹህ ውሃ አቅርቦት ችግሮቻቸውን የፈቱ ሀገሮች ድህነትን ያሸነፉ መሆናቸውን አመለከቱ፡፡

አቶ ፍቃዱ ዘለቀ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የንጹህ ውሃ አቅርቦት ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ነው።ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ የሚታየውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ገቢያችንና የውጭ ምንዛሬ የማግኘት አቅማችንን ማሳደግ ይገባል።

የንጹህ ውሃ አቅርቦት ሥራ እንደፋብሪካ አንድ ጊዜ ተገንብቶ በቃ አሁን አለቀ የምንለው አይደለም ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ፤ የኢኮኖሚ አቅማችን እያደገ ሲመጣ የውሃ ፍላጎታችን ያድጋል ፤ ፍላጎቱ የሆነ ጊዜ ተጀምሮ የሆነ ጊዜ የሚጠናቀቅ አይደለም፤ ማህበረሰቡም የችግሩን ስፋት በዚህ ደረጃ ሊመለከተው ይገባል ብለዋል።

አሁን እያጋጠመን ያለው እጥረት የድህነትና የፋይናንስ ችግር ነው፤ ስናድግ እና ገንዘብ ሲኖረን ችግሩ በዘለቄታው ይፈታል ያሉት አቶ ፍቃዱ ፣ ከእኛ የባሰ በረሃ ውስጥ ያሉ ሀገሮች ገንዘብ ስላላቸው ብቻ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር የለባቸውም ፤ ችግሩን የተሻገሩ ሀገሮች ድህነትን ያሸነፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ከፋይናንስ አቅም ጋር የሚገናኝ መሆኑን አመልክተው፤ በዘርፉ እያጋጠማት ያለው ችግር የሚቀረፈውም የተጠኑ የውሃ ግድብ ፕሮጀክቶችን መገንባት ስንችል ነው ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት በቀን 677 ሺህ ሜትር ኪዩብ ንጹህ ውሃ እያመረተ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው ፤ ከተማዋ የሚያስፈልጋት ግን አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአቅርቦቱ እና በፍላጎቱ መካከል የሚስተዋለውን ክፍተት ለማጥበብ የውሃ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆኑ ገልጸዋል። ለዚህም የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል።

ሞገስ ተስፋና መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You