በቀጣዩ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ቀጠናን (ሴካፋ ዞን) የሚወክለው ክለብ ዛሬ ይለያል።በሴካፋው ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ እና የውድድሩ አስተናጋጅ የሆነው የኬንያው ክለብ ቪሂጋ ኪዊንስ ወደ አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍ የሚያስችላቸውን ትኬት የሚቆርጡበት ጨዋታ ዛሬ 10፡00 ላይ ይደረጋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የሚያዘጋጀው ቻምፒዮንስ ሊግ በግብጽ አዘጋጅነት በቀጣዩ ዓመት የሚካሄድ ሲሆን፤ በአህጉሩ የሊግ አሸናፊ ክለቦችም በስድስት ዞኖች ተከፋፍለው የማጣሪያ ውድድሮችን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ለአራት ጊዜያት ቻምፒዮን መሆን የቻለው ስኬታማው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም፤ ከስድስቱ ዞኖች መካከል አንዱ በሆነው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮና (ሴካፋ ዞን) በመሳተፍ ለፍፃሜ ቀርቧል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የንግድ ባንክ ቡድን በኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ሲሆን፤ ይህም በሴካፋ ቻምፒዮንስ ሊጉ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ቅድመ ውድድር እንዲካፈል አድርጎታል።በውድድሩ አስፈሪ ክለብ ሆኖ የቀረበው ኢትዮጵያዊው ክለብ አንድ እግሩን ወደ ቻምፒዮንስ ሊጉ ተሳታፊነት ያስገባ ሲሆን፤ የዛሬው ጨዋታም እጣ ፋንታውን የሚወስን ይሆናል።የዛሬውን የፍፃሜ ጨዋታ ለማሸነፍ ከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ የሚገኙት የንግድ ባንክ ተጫዋቾች፤ በጉዳት ላይ የነበሩት ህይወት ዳንጌሶ፣ መዲና አወል እና ቡዛየሁ ታደሰ ማገገማቸውም ተሰምቷል። ቡድኑ ለጨዋታው የሚረዳውን ቀላል ልምምድም በጅምካና ስፖርት ክለብ ማዕከል ትናንት እንዳደረገ ከስፍራው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የምድብ ተፋላሚዎቻቸውን ጥለው ለፍጻሜው የበቁት ሁለቱ ክለቦች በአንድ ምድብ እንደመገኘታቸው በመጀመሪያ ጨዋታቸው እርስ በእርስ ተገናኝተው ነበር።ክለቦቹ ባደረጉት ትንቅንቅም ንግድ ባንኮች የበላይነቱን በመያዝ 4ለ2 በሆነ ውጤት አሸንፈው ሶስት ነጥብ ማሳካታቸው አይዘነጋም። ንግድ ባንኮች ከዚህ ከቀደም በምድባቸው ባደረጓቸው ጨዋታ ያሳዩት ድንቅ አቋምና በተጋጣሚያቸው ላይ ያስቆጠሩት ከሁለት ደርዘን ያላነሰ ግብ ተዳምሮ በዛሬው ጨዋታ ላይም የኬንያውን ተወካይ በማሸነፍ ለቻምፒዮንስ ሊጉ የመብቃት እድላቸው የሰፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።የክለቡ አምበል ሎዛ አበራ ጨዋታውን በተመለከተ ‹‹የቀጠናውን ጨዋታ አሸንፈን በግብጽ ለሚካሄደው ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ተቃርበናል፤ ለዚህም ጠንክረን እየሰራን ነው›› ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
የግማሽ ፍጻሜ ተጋጣሚውን ረትቶ ለመጨረሻው ጨዋታ የደረሰው የኬንያው ቭሂጋ ኩዊንስ በቀጠናው ካሉ ጠንካራ ክለቦች አንዱ ነው።በማጣሪያው 23 ግቦችን በማስቆጠር ሁለተኛው ክለብ ነው።በመጀመሪያው ጨዋታ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ አራት ያስተናገደው ይህ ክለብ የዛሬውን ጨዋታ በቁጭት እንደሚጫወት አሰልጣኝ ቻርለስ ኦኬሬ ኦኮዝ ጠቁመዋል።ጨዋታውን በሚመለከት በሰጡት አስተያየት ‹‹በደንብ ተዘጋጅተናል ይህንንም ሊደርሱበት አይችሉም፤ ፍጻሜው ቀላል አይሆንም›› ማለታቸውን ስፖርት ኒውስ አፍሪካ የተሰኘው ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በዚህ ውድድር በተጋ ጣሚዎቻቸው ላይ 25 ግቦችን አስቆጥረው 4 ደግሞ ተቆጥሮባቸዋል።ክለቡ ካስቆጠራቸው ግቦች መካከል 21ዱ በሎዛ አበራ እና መዲና አወል የተመዘገቡ ናቸው። ጸጋነሽ የሱስ ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር፣ አረጋሽ ካልሳ እና እመቤት አዲሱ ደግሞ አንድ አንድ ግቦችን በስማቸው ማስቆጠር ችለዋል።13 ግቦችን ማስቆጠር የቻለችው ሎዛ አበራ በሴካፋ ዞን እንዲሁም በአጠቃላይ 6ቱም ዞኖች በከፍተኛ ግብ አግቢነት እየመራች ሲሆን፤ የክለብ አጋሯ መዲና አወል ደግሞ በ8 ግቦች ተከታዩን ስፍራ ይዛ ትገኛለች። ንግድ ባንኮች በኬንያ እያሳዩ ባሉት አስደናቂ አቋም አሰልጣኙ ብርሃኑ ግዛው እንዲሁም ተጫዋቾቹ በአፍሪካ ክለቦች ዓይን በመግባታቸው በተለያዩ ክለቦች በጥብቅ እየተፈለጉ እንደሚገኙ ዘገባዎች ያመላክታሉ።ንግድ ባንክ ለቻምፒዮንስ ሊጉ እንዲረዳው የተጫዋቾችንና አሰልጣኙን ውል በቅርብ ማደሱ የሚታወስም ነው።
በቀጠናው የ9 ሊጎች አሸናፊዎች ሲሳተፉ፤ የውድድሩ አስተናጋጅ የኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዛንዚባር፣ ጅቡቲ፣ ሩዋንዳ እና የብሩንዲ ክለቦች ተሳታፊ ናቸው።የሱዳን እና ኤርትራ ቻምፒዮኖች ደግሞ በካፍ መስፈርት መሰረት በክለብነት መመዝገብ ባለመቻላቸው ተካፋይ መሆን አልቻሉም።በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲካሄድ በቆየው ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድብ ሁለት ከኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዛንዚባር ክለቦች ጋር ነበር የተደለደለው።በውድድሩ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ተሳትፈው ጨዋታዎችን ሲመሩም ቆይተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2013