ጀግንነት ከፍ ካሉ ሰብዓዊ እሴቶች የሚፈጠር በራሱም ከፍ ያለ ሰብዓዊ እሴት ነው። ከዚህ የተነሳም ሰብዓዊ እሴቶቻቸው ከፍ ባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ጀግኖች በስፋት የመገኘታቸው እውነታ የተለመደና ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
ጀግና ከፍ ላሉ ሰብዓዊ እሴቶች የታመነ፤ በእነዚህ እሴቶች የተገነባ ስብዓና ባለቤት ነው። ውልደቱም ዕድገቱም በእነዚህ እሴቶች ላይ የተመሰረተ ስለሆነና እሴቶቹ በማንነቱ ውስጥ ካላቸው ከፍ ያለ ስፍራ የተነሳ ጀግና ያለመሆን ዕድልም ሆነ እጣ ፈንታ የለውም።
ጀግንነት ለግለሰብ ጀግና ሆነ ጀግንነት ማህበረሰባዊ መለያው ለሆነው ማህበረሰብ የተሰራ ማንነት መገለጫ ባህሪ ነው። ከፍ ያሉ ሰብዓዊ እሴቶች እስካሉ ድረስ ጀግንነትም እንደ ግለሰብ ሆነ እንደ ማህበረሰብ አብረውት ይኖራሉ።
ጀግንነት ከፍ ላለ ዓላማ ራስን ለመስዋዕት ማዘጋጀትን የሚያስችል የህይወት ዝግጅት ነው። ሕይወት በራሱ ካለው ፍጥረታዊም ሆነ ማህበራዊ ዋጋ አንጻር ከሱ ከፍ ያለ ዓላማ ባለቤት መሆንም በራሱ በቀላል ስሌት የሚሰላና የሚደረስበት እውነታ አይደለም። ከሁሉም በላይ ሰው መሆንን የሚጠይቅ ነውና!
ጀግንነት በማሸነፍና በመሸነፍ፣ ያሰቡትን ከፍ ያሉ ሀሳቦች በማከናወንና ባለማከናወን የሚሰላም አይደለም። ከዚህ በላይ ሆኖ መገኘትን የሚጠይቅ ነው። ራስን ከፍ ላለ ሰብዓዊ እሴት ማስገዛት ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት ባለቤት መሆንን የሚጠይቅ ነው።
ኢትዮጵያውያን በዘመናት ታሪካቸው በብዙ ከፍታዎችና ዝቅታዎች መኖራቸው ከዓለም ያልተሰወረ የአደባባይ እውነታ ነው። በእነዚህ ዘመናት ውስጥም የጀግንነት ተምሳሌት የመሆናቸው እውነታም እንዲሁ አደባባዮችን የሞላ የህዝባችን እና የሀገራችን አንዱና ዋነኛ መገለጫ ነው።
ይህ የህዝባችን ጀግንነት አንድም ሕዝባችን እንደ ህዝብ ከፍ ያሉ የሰብዓዊ እሴቶች ባለቤት ከመሆኑ የመነጩ ሲሆኑ፣ ከዚህም በላይ ለእነዚህ እሴቶች በህይወት የመወራረድ እና ራስን ከእሴቶች በታች አድርጎ የማየቱ እውነት እንደሆነ ይታመናል።
ለሌሎች እራስን አሳልፎ የመስጠት የሰማእትነት መንፈስ ለዘመናት በሀይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶቹ ውስጥ ሲቀባበለው የመጣ፣ በትውልድ ማንነት ግንባታ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ የያዘ ማህበረሰባዊ እሴት ነው።
አንዳንዶች ይህንን ከፍ ያለ ማህበረሰባዊ እሴት ለመሸርሸር በግልጽም ይሁን በስውር ብዙ ስራዎችን ቢሰሩም ሕዝባችን እንደ ህዝብ አሁንም የዚህ ማህበራዊ እሴት ባለቤት ነው። እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም እንደ ሀገርና ህዝብ የጀግኖች ሀገር እና ህዝብ የመሆኗ ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
ኢትዮጵያውያን ዛሬም እንደ ትናንቱ ከራሱ ማንነት ለሚመነጨው የሀገር እና የዜጎች ክብር ለመሞት የሚከለክል የማንነት መዋዠቅና፣ የራስ ወዳድነት እርግማን ጥላ ውስጥ አይደሉም። ለሀገር እና ለዜጎች ክብር መሞት ደበዘዘ ሲባል የሚጎላ ፤ ጠፋ ሲባል ከፍ ባለ ድምቀት የሚገለጥ የማንነታቸው መገለጫ ነውአ እንጂ።
ትናንት የብዙ ጀግኖች መፍርያ፤ የጀግንነት ተምሳሌት የመሆናችንን ያህል ዛሬም የብዙ ጀግኖች መፍርያና የጀግኖች ተምሳሌት ነን። ከጀግንነታችን በስተጀርባ ያሉ ሰብዓዊ እሴቶቻችንን ለማፍረስ ጠላቶቻችን በብዙ ቢጥሩም የደከሙትን ያህል አልተሳካላቸውም።
እንደ ህዝብና ሀገር የተገዛንላቸው የፍቅር፣ የአንድነትና የመተሳሰብ እሴቶቻችንን በየዘመኑ ባሰብነውም፣ ባላሰብነውም፤ በመሰለንም፣ ባልመሰለንም መልኩ በታሪካዊ ጠላቶቻችን በብዙ ተፈትነዋል።
ፈተናዎቹ በፈጠሩት ግራ መጋባት ብዙ ውጣ ውረዶችንና ብዙ ጽልመት የተሞሉ ህይወቶችን ለማለፍ ተገደናል። በእነዚህም እንደ ሀገርና ህዝብ ብዙ ዋጋ ከፍለናል። አበቃላቸው ተብለን ሲታሰብም በሚደንቅ መልኩ ተነስተን፣ ቆመን፣ መራመድ ችለናል።
ሰው ሰው ከሚሸተው መለያ ጠረኖች የሚመነጨው ስብእናችን የጀግንነታችን መሰረት በመሆን ዘመናትን አሻግሮናል። ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ወንድሞቻችን የማንነት ስብራት ፈውስ በመሆን ለነጻነታቸው ቀንዲል መሆን ችለናል።
ብዙዎች ከነበሩበት የህይወት ስብራት ወጥተው፣ የተሰረቀ እውነተኛ ማንነታቸውን አውቀው፤ በተለወጠ ማንነት፣ በልበ ሙሉነትና በሚጨበጥ ሰብዓዊ ተስፋ አዲስ የህይወት ምዕራፍ እንዲጀምሩ እድል ፈንታ ሆኗቸዋል።
ዛሬም እንደ ሀገርና ህዝብ ርቆን የቆየውን የብልጽግና ህይወት ተስፋ ለማስመለስ በአዲስ የጀግንነት ታሪክ ጅማሬ ውስጥ እንገኛለን። ይህ ጅማሬያችን እንደቀደመው ዘመን የነጻነት ትግል ብዙ ተግዳሮት ይዞብን ቢመጣም፣ ተስፋና እምነታችን በሚፈጥረው ቁርጠኝነትና ከዚህም በሚወለደው ጀግንነት መሻገራችን የማይቀር ነው።
በዚህም እንደሀገር በምንፈጥራቸው ጀግኖችና የብልጽግና ህይወት የብልጽግና ተስፋና እምነታቸውን ለተነጠቁ ህዝቦች አዲስ መነቃቃትና መነሳሳት በመፍጠር እንደቀደመው ዘመን ለእነዚህ ህዝቦች አብሪ ኮከብና፤ ለራሳችንም አዲስ የመልማት ጀግንነት ታሪክ ባለቤት መሆናችን አይቀሬ ነው!
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4 ቀን 2013 ዓ.ም