በ2022 ኳታር በምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን በሚካሄደው የምድብ ማጣሪያ በምድብ ሦስት ከጋና፣ደቡብ አፍሪካና ከዚምባብዌ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ዙር ጨዋታውን ትናንት ከዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድን ጋር በባሕርዳር ስታድየም አድርጓል:: የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከጨዋታው በፊት ‹‹አሸንፈን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአዲስ ዓመት ስጦታ እናበረክታለን›› እንዳሉት ቃላቸውን ጠብቀዋል::
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የድል ገድ በሆነው ባህርዳር ስታድየም ተመልካች እንዲገባ ባይፈቅድም ዋልያዎቹ በመጨረሻ ሰዓት ላይ ጦረኞቹን አንድ ለዜሮ በመርታት በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ለሕዝባቸው ውድ ስጦታ ማበርከት ችለዋል:: በጨዋታ እንቅስቃሴና በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ዋልያዎቹ 30ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታ አቀጣጣዩ ሽመልስ በቀለ በጉዳት በታፈሰ ሰለሞን ተቀይሮ ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ ለግብ የሚሆኑ እድሎችን እንደ ልብ ለመፍጠር ሲቸገሩ ታይተዋል:: ጦረኞቹ ከሜዳቸው ውጪ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት መከላከልን መሰረት ያደረገና በመልሶ ማጥቃት ጉልበት የተቀላቀለ ጨዋታ በመምረጣቸው ዋልያዎቹ ግልፅ የግብ እድል ለመፍጠር ተቸግረዋል:: ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች እየነጎዱ በሄዱ ቁጥር ውጥረት ውስጥ የገቡት ዋልያዎቹ 78ኛው ደቂቃ ላይ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ባደረጉት ስኬታማ የተጫዋች ቅያሬ የተሻለ የግብ
እድል ለመፍጠር ሲጥሩ ታይተዋል:: አስራት ቱንጆን በሱሌማን ሀሚድ፣ አምበሉና አጥቂውን ጌታነህ ከበደን በአቤል ያለው እንዲሁም አማካኙን መሱድ መሀመድን በአማኑኤል ዮሐንስ ቀይረው ያስገቡት አሰልጣኝ ውበቱ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ አጥቂው አቡበከር ናስር ላይ በተፈፀም ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል:: ጦረኞቹ ፍፁም ቅጣት ምቱ እንዳይቆጠርባቸው የስነልቦና ጫና ለመፍጠር ከዳኞች ጋር ለረጅም ደቂቃ እሰጥ አገባ ውስጥ የገቡበት አጋጣሚም አስገራሚ ነበር:: ያም ሆኖ አስቻለው ታመነ ፍፁም ቅጣት ምቱን በአግባቡ በመጠቀም ዋልያዎቹም በመጨረሻ ሰዓት ለድል አብቅቷል::
ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ፉክክሩ ከዚህ በኋላ በሚኖሩ ጨዋታዎች ትልቅ ተስፋና ትርጉም ያለው ቆይታ እንዲኖራቸው የትናንቱን ጨዋታ ማሸነፍ ግዴታቸው ነበር:: ለዚህም ነው ድሉ ውድ የአዲስ ዓመት ስጦታ የሆነው:: ዋልያዎቹ በሜዳቸው ያውም በማጣሪያ ድልድሉ ከሌሎቹ ተጋጣሚዎች አንፃር ቀላል በሆነችው ዚምባብዌ ነጥብ ጥለው ቢሆን ኖሮ በቀጣይ በዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ጉዞና ተስፋ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም ነበር:: እጅግ ወሳኝ የሆነውን ሦስት ነጥብ በሜዳቸው በማሳካታቸው ግን በቀጣይ ጨዋታዎች ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ቢከብድም በቡድኑ ስብስብና ተስፋ ላይ ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥር እርግጠኛ መሆን ይቻላል::
በተለይም ባለፈው አርብ ምሽት በሜዳዋ ዋልያዎቹን ያሸነፈችውና የምድቡ ጠንካራ አገር የሆነችው ጋና በሁለተኛው የማጣሪያ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ በደቡብ አፍሪካ አንድ ለዜሮ መሸነፏ ኢትዮጵያና ዚምባብዌ በምድቡ ያላቸውን ተፎካካሪነትና የዓለም ዋንጫ ተስፋ ለማቆየት የትናንቱን ጨዋታ ወሳኝ አድርጎታል:: ዋልያዎቹም ከዚህ ጨዋታ የሚፈልጉትን ውጤት ይዘው መውጣታቸውን ተከትሎ ምድቡን በእኩል ሦስት ነጥብ ከጋና ጋር በሁለተኝነት መምራት ችለዋል:: ደቡብ አፍሪካ ጥቁር ከዋክብቱን በሜዳዋ ማሸነፏን ተከትሎ ባለፈው አርብ ከዚምባብዌ ጋር አቻ የተለያየችበት ውጤት ተደምሮ ምድቡን በአራት ነጥብ መምራት ችላለች:: ዚምባብዌም በአንድ ነጥብ ብቻ የመጨረሻውን ደረጃ ለመያዝ ተገዳለች:: ኢትዮጵያና ዚምባብዌ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገናኙበት ከ1984 ጀምሮ የትናንቱን ሳይጨምር በሁሉም ውድድሮች በሶስት ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ሁለቱን ጨዋታዎችም ዋልያዎቹ በድል ተወጥተዋል::
የዋልያዎቹ ስብስብ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለት ጨዋታዎች ያሳዩት አቋም በብዙዎች አድናቆት የተቸረው ሲሆን አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ወጣትና ነባር ተጫዋቾችን አዋህደው የተሻለ የቡድን ግንባታ ላይ እንደሚገኙ በግልፅ አሳይተዋል:: የዋልያዎቹ ስብስብ በቀጣይ ጊዜ እየጠነከረ ሲሄድም በመጪው ጥር በሚካሄደው የካሜሩኑ አፍሪካ ዋንጫ ላይ ከተሳትፎ የዘለለ ቆይታ ሊኖረው እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነው::
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2013