ማሪያ ሙኒር ይባላሉ። የህግ ባለሙያና ጠበቃ ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን ከመሠረቱት መካከል አንዷ ናቸው። በተለይ ግን የሚታወቁት በቀድሞ ስሙ ፆታዊ ጥቃት ተከላካይ ማሕበር በአሁን ደግሞ የሴቶች ማረፊያና ልማት ማሕበርን ተመሳሳይ ራዕይ ካላቸው ሴቶች ጋር በመሆን መስርተው የሴቶችን እንባ ጠራጊ በመሆናቸው ነው። ከ15 ዓመታት በላይ ድርጅቱን በሥራ አስኪያጅነት እየመሩ ከስምንት ሺህ በላይ ሴቶችና ከዘጠኝ ሺህ በላይ ልጆቻቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መስመር ዘርግተዋል።
ማህበሩ የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴት ልጆችና ወጣቶችን ሥልጠናና የህግ ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን፤ የራሳቸው ገቢ ኖሯቸው የተሻለ ህይወት እስኪኖሩ ድረስ የሚያግዝ ነው። ድርጅቱ በኦሮሚያና ሐዋሳ ላይ ሁለት ቅርንጫፎችን በመክፈት፤ በደሴና በአዲስ አበባ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ይሰራል።
እንዲሁም በቅርቡ በአፋር እየደረሰ ያለው መፈናቀልና የሴቶች ጥቃት ማህበሩ ስላሳሰበው አገልግሎቱን ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቋል። ለዚህ ደግሞ መሪነቱን እየተጫወቱ ያሉት እርሳቸው ናቸውና ለመልካምነታቸው የበጎሰው ሽልማት በዘንድሮው ዓመት ተሸላሚ አድርጓቸዋል። እኛም የመልካምነት ቀንን ምክንያት በማድረግ የእርሳቸውን ተሞክሮ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር እንዲያጋሩን ጠይቀናቸዋል። ሀሳባቸውን ለህይወታችሁ መርህ ታደርጉት ዘንድም ጋብዘናችኋል።
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ እይታ መልካምነት እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ ማርያ፡- ለእኔ መልካምነት ቃላት የሚወስኑት አይደለም። ከቃል በላይ የሆነ በተግባርና በስሜት ውስጥ ያለ፤ በህይወት የሚኖሩት ልዩ ፍላጎት ነው። መልካም መሆንን የማስበው ብዙ ገንዘብ በመስጠት ልክ አይደለም። ለታይታ በሚለካ መልኩም እንዲሆን አልፈልግም። ለምስጋና ለክብር ወይም የተሻለ ነገር ለራስ ከመፈለግ አንጻርም አይደለም። መልካም መሆን ያለን ማካፈልና ከትንሹ ላይም ቢሆን ቀንሶ መስጠትን መጀመር ነው ብዬ አምናለሁ። ለራስ የሚመኙትን ለሌሎችም ማድረግ ነው።
መልካምነት ከጥሩ ሰላምታ ይጀምራል። ከጥሩ መልስ የሚመጣና የሚመነጭ ነው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም መልስ ሰጪውንም ተቀባዩንም ይቀድሳል ወይም ያረክሳል። የቀን ውሎን ብሩህ ያደርጋል ወይም ያጨልማል። በሌላ በኩል መልካምነት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ እርዳታ ማድረግ ነው። ከአገር አልፎ ዓለምን የተሻለ ለማድረግ ያለ ምኞት ነው። ክፉና በስቃይ ላይ ያለን መርዳት ነው።
በሰው አስተሳሰብ ውስጥ ሁሉ ነገር መልካምነት ያለው ብቻ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። ደግነትም ክፋትም ይኖራሉ። እነዚህ ነገሮች ደግሞ በሰው ልጆች የዕለት ተለት ኑሮ ውስጥ በየጊዜው የሚያጋጥሙም ናቸው። ይህ መሆኑ ደግሞ ‹‹መልካምነት ጨው›› እንዲሆን ያደርገዋል። ከብዙዎች ውስጥም ነጥረው የሚወጡ መልካሞች የሚታዩት ለዚህ ነው። ማንም ሰው በውስጡ መልካምነት ሳይኖረው ደስተኛ መሆን ፣መርካት፣ጥሩ እንቅልፍ መተኛት፣በፍቅር መኖር፣ ጤናማ መሆን ወዘተ አይችልም:: ስለዚህ ትንሽም ቢሆን ሰዎች ውስጥ መልካምነት ይኖራል። ያንን እንዲያብብ ማድረግን ግን ይጠይቃል።
መልካምነት ሀገር የለውም፣ ድንበር አይወስነውም። በብሔርና በሀይማኖት አይገደብም። ሰው ሁሉ የሚኖረውና የሚያደርገው ነው። በነፃ አገልግሎት ወገንን ማስደሰት፣ ሁል ጊዜ ለሰው መድረስ ብቻ የሚታሰብበትም ነው። በአጠቃላይ ውለታ የሚጠበቅበት አይደለም። ምክንያቱም መልካምነት ነጻ ፍላጎትና ነጻ ተግባር ነው። ስለዚህም መልካም አድራጊ ሁሉ የወገኑ ደስታ ያስደስተዋል፤ የወገኑ ርሃብና ጥም ይሰመዋል። በዚህም ወደመፍትሄ ሀሳብ እንዲገባ ያደርገዋል።
በእርግጥ መልካምነት ጅማሮው ቤት መሆን አለበት። መሰረት ያልጣሉት ነገር አድጎ ህይወት አይሰጥምና። እናም ከቤታችን የሚጀምር ልጆችንም ሆነ የምንመራውን ቤተሰብ የሚያሳድግና የልጆቻችን የወደፊት እጣ ፋንታ የምንወስንበት ስለሆነ በየቀኑ እያሰብነው እየኖርነው የምናደርገው መሆን ይኖርበታል። ከጎረቤቶቻችን ጋር የምንዛመድበት ፤ ከማናውቀው ሰው ጋር ጭምር የምንግባባበትና የደም ትስስር የምናደርግበት መንገድም ነው። ይህንንም ማጠንከር መልካምነታችንን እንዲያብብ ማድረግ ነውና ልንጠቀምበት ይገባል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- መልካምነትን አንዴት ማሳየት ይቻላል፤ መንገዱስ ምን መምሰል አለበት ይላሉ?
ወይዘሮ ማርያ፡- ይህ ባህሪ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ። ባህሪ ከሆነ ለመለወጥ ያስቸግራል፤ ተግባር እንጂ ወደኋላ ማለት አይታከልበትም። በፈተና ውስጥ ተሆኖ እንኳን ማለፍ ይቻላልን የሚያስነግብ ነው። ምክንያቱም መልካምነት ማለት እንክብካቤ ፣ትኩረትና ድጋፍ እንዲሁም ምላሽ ሰጪነት ነው።
ስለዚህም ይህን ዝርዝር ለማሟላት ብዙ ሥራን ይጠይቃል። አንዱ ቤተሰብን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ መስራት ነው። በጥሩ ሁኔታ የአንድ ንቁ የሕይወት አቋም መገንባትንም ይጠይቃል። ይህ ማለት ሥነ-ምግባር፣ ጥንካሬ እንዲሁም የአመለካከት እና ስሜት ድብልቅ የሆነውን መልካምነት በእያንዳንዱ አዕምሮ ውስጥ ማስቀመጥ ለስኬት ያበቃል። ስለሆነም ይህ መተግበር መቻል አለበት እላለሁ።
መልካምነት እንዴት ይታያል ለተባለው በእያንዳንዱ ችግር ውስጥ እኔ ብሆንስ እያሉ በማሰብ መስራት ሲቻል ነው። የሰዎችን ችግር በመፍታት ደስተኛ መሆን ሁልጊዜ ተግባራችን ከሆነም መልካምነት ታየ ሊባል ይችላል። ደሃ ሃብታም፣ ወንም ሴት ሳንል ለሁሉም በእኩል ማድረግ ስንጀምርም አሁንም ይታያል። በተለይ ግን ከራስ ወዳድነት ስንርቅና ቅድሚያ ሌሎችን ስናስብ የሚጎላ ነው። ሁልጊዜ መስጠት ፣ ሁልጊዜ ማድረግና መርካትን ልምድ ስናደርግ መልካምነታችን እየታየ እያበበ ይመጣል። የመልካምነት ትርፉ የህሊና ሰላም፣ ፍቅርና ደስታ እንደሆነ ስናምንና ስንኖረውም መታየት ብቻ ሳይሆን መጎልበት ይጀምራል። ለጤናና በረከታችን አስበን ስናደርገውም መልካምነታችን ይጎላል።
አዲስ ዘመን፡- መልካምነት መገለጫ አለው ይላሉ?
ወይዘሮ ማርያ፡– እንደእኔ እምነት መልካምነት ውስን አድርገን መገለጫዎችን ልናስቀምጥለት የምንችለው አይደለም። ብዙ ትርጓሜ የሚሰጠውና ከብዙ ነገሮች ጋር የሚተሳሰር ነው። ለአብነት መልካምነት ቅንነት ነው፤ በጎ ማድረግም ይሆናል፤ መልካምነት አማኝነትም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ምክንያቱም ከአደረግነው ሳይሆን ከአላህ ክብርና ሞገስን የምናገኝበት ፤ በረከትን የምንሰጥበት ነው። ስለዚህም ይህንን ለማግኘት በእነዚህ ሁሉ ትርጉሞች ውስጥ ሆነን መስራት አለብን። ሰውን እንደሰውነቱ ማክበርም ተደርጎ ይወሰዳል። ስለዚህ መልካምነት ከቃላት እስከ ሥራ ድረስ የሚጓዝ መገለጫዎች ያሉት ነው። በየደረጃውና በየሁኔታው ተለዋዋጭነትም አለው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ መልካም ማድረግን መቼ ጀመርኩ፤ ከማን ተማርኩ ይላሉ ?
ወይዘሮ ማርያ፡- እኔ ያደኩት ብዙ ቤተሰብ ባለበት ቤት ውስጥ ነው። እናታችን ደግሞ ለዚህ ሁሉ ሰው በእኩል ደረጃ ተመግቦ እንዲያድር ትፈልጋለች። ሰራተኛ እንኳን ከልጆች እኩል ሆኖ እንዲኖር ነው የምትፈልገው። ማንም ሰው ተቸግሮ ማየትን አትሻም። ሲበዛ ደግና ሩህሩህ ነች። አወኩት አላወቅሁትም የምትለው ሰው የላትም። ላላወቀችው ሰው ሁሉ ተቸገርኩ ካላት ወርቋን ጭምር ሸጦ እንዲጠቀም ታግዘዋለች። ስለዚህም እናቴ እኔን በመልካምነት ሰርታኛለች ብዬ አስባለሁ።
በእርግጥ በዚህ ደግነቷ ብዙዎች ሞኝ ናት ይሏታል። ነገር ግን በጎነትና መልካምነት መቼም ሞኝነት እንዳልሆነ በተግባር ጭምር እያረጋገጠች ነው የምታልፈው። ይህ ባህሪዋ ደግሞ እኔ ላይ ተጋብቶብኛል ብዬ አስባለሁ። ምንም አይነት ፈተና ውስጥ ቢኮን ደግነት በውስጥ ያለ ከሆነ ማንም ሊያግደው እንደማይችል ከእርሷ ተምሪያለሁ። ስለሆነም የመጀመሪያ የመልካምነት ትምህርትቤቴና መምህሬ እናቴ ነች።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ትምህርት ቤት ላይ የማከናውናቸው ተግባራት መልካም ሆኜ እንድወጣ አስችሎኛል። ቅዳሜና እሁድ ህጻናት ማሳደጊያዎች ውስጥ መዋል ልምዳችን ነው። ከትምህርት በኋላም ቢሆን እንዲሁ በየመንደሩ ውስጥ እየሄድን ችግረኞችን በተለያየ መንገድ እንድናግዝ ይደረጋል። የበጎአድራጎት ሥራዎችን ማከናወን አንዱ ትምህርታችን ነበር። በዚህም አረጋዊያንና የታመሙ ሰዎችን ቤት ከመጥረግ፣ ልብስ ከማጠብ ባለፈ አስፈላጊ ነገሮችን እናደርጋለን። በዚህም መልካምነትን ቋሚ ስራችን አድርገን እንድንወስደውና ዛሬ ድረስ ለእርሱ እንደተፈጠርን እንዲሰማን ሆነናል።
በጣም ከፍ ስንልም ቢሆን በጎ ከማድረግ አልተቆጠብንም ነበር። እንደውም የወሴክማና ወክማ አባላት ሆነን በወሎ አካባቢ በድርቅ የተጎዱ ሰዎችን ከሚበሉትና ከሚዘሩት እህል ባለፈ የሚያርሱበት በሬ ጭምር በመግዛት በጥምረት እንዲሰሩ በማድረግ ከቀያቸው የተፈናቀሉትን ወደ ቤታቸው መመለስ ችለን ነበር። ይህ የሆነውም በጨቅላ አዕምሯችን አውጥተንና አውርደን የሙዚቃ ዝግጅት በማዘጋጀትና ዳቦ ቆሎ ቆርጦ በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ በመሰብሰብ ነው። ለዚህ ደግሞ ትንሽነታችንን ሳይንቁ የተባበሩን ኦኬስትራዎች ነበሩ። እንዲመጡ የጠየቅናቸው ትልልቅ ሰዎችም በቦታው ተገኝተውልናል። እናም መልካም ለማድረግ ሰው መነሳት ብቻ እንደሚጠበቅበት በዚያ እድሚያችን ላይ ተምረናል።
መልካም ማድረግ መጀመሪያ ራሱን እንደሚያስደስትም በእነዚህ ተግባሮቻችን በበቂ ሁኔታ ተምረናል። ውጤቱን መቅመስ እንደሚቻልም በብዙ ነገር ማየት የቻልንበት ነው። ዛሬም ቢሆን የሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበርን ለመመስረት ያስቻለኝ ይህ እድገቴ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ማረፊያው በመከፈቱ ከስምንት ሺህ በላይ ሴቶች ከዘጠኝ ሺህ በላይ ልጆች እንዲጠቀሙ ሆነዋል። እንባቸውን ጠርጎላቸው ልጆቻቸውን ደስተኛ ሆነው እንዲያሳድጉም አግዟቸዋል። ለእኔም ቢሆን የሁልጊዜ መጽናኛዬና ሁሌም መልካም ማድረግ እንድችል ብርታት ማግኛዬ እንዲሆንልኝ አድርጎኛል።
ሴቶቹ ሲገቡ በተለያየ ችግር ውስጥ አልፈው ነው። ራሳቸውን ለማጥፋት፣ ልጆቻቸውን ለመግደል የሚሞክሩ ፤ አልጠቅምም፣ መኖር የለብኝም ብለው የሚያስቡ ናቸው። ሆኖም በተደረገላቸው እንክብካቤ አዲስ ሰው ሆነው ለራሳቸውም ለአገራቸውም መልካም ሰሪ እንዲሆኑ በማህበሩ መሰራቱን ሳይ ደስተኛ ያደርገኛል። የመልካምነት ውጤቱ ይህ ነው እንድልም ያደርገኛል። ከዚያ አልፎ ሱሴም ኑሮዬም እንዲሆን እድል ሰጥቶኛል።መልካምነትን በዚህ ደረጃ የሚያይ ሰው ደግሞ ክፉውን ሳይሆን ተስፋውን ፣ መድሀኒቱን ብቻ ነው የሚያስበው። እኔም አንድ ነገር ሲፈጠር መፍትሄውን ማየት የምችለው በበጎ ስፈልገው እንደሆነ የተረዳሁት በእነዚህ መምህራንና ተግባራት ነው።
እኔ መልዕክተኛ እንጂ አድራጊ፣ ፈጣሪ አይደለሁም፤ በጎ ለማድረግ ስነሳ መፍትሄዎቹን የሚሰጠኝ ፈጣሪ ነው። እርሱ ይጨምርበታል ብዬ ስለማምንም እያደረኩትም እንድቆይ ሆንኩ። ወደፊትም እድሜ ከሰጠኝ አደርገዋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከታሪክ አንጻር ስናይ ኢትዮጵያዊያን መልካምነትን የተለየ ዋጋ ይሰጡታል። ለመሆኑ ይህ እንዴት ይታያል?
ወይዘሮ ማርያ፡- መልካምነት እንደተባለው በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ እንዳለ እናያለን። ካለው ላይ ቆርሶ ለሚያውቀው ሳይሆን ለማያውቀው ሰው ጭምር ይሰጣል፤ ቤት የእግዚአብሔር ነው ብሎ ያሳድራል፤ እንግዳ የሆነ ሰውን በአክብሮት አምነውት እንዴት እንደሚያስተናግዱት በየጊዜው የምናየው ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያዊያን ለእኔ ሳይሆን ለእኛ የሚሉ ዜጎች ናቸው። አብሮ መብላት፣ ያለን መካፈል፣ በችግር ጊዜ መረዳዳት፤ በደስታም ጊዜ አብሮ መደሰትን የሚመርጥና በህይወቱም እነዚህ ነገሮች ልዩ ባህሪው አድርጎ የሚኖር ህዝብ ነው።
ከተሞች አካባቢ እነዚህ ነገሮች እየተሸረሸሩ ናቸው፤ገጠሩም ላይ ቢሆን አሁን አለመተማመኖች ይስተዋላሉ። ለዚህ ደግሞ ፖለቲካው ትልቅ ሥራ ሰርቷል። መለያየትን ሰብኮ ታሪክን፣ ባህልንና መልካም ስብዕናን እንዲመናመን አድርጎታል። ግን ሙሉ ለሙሉ ጠፋ ብሎ ማሰብ ጨለምተኛ መሆን ነው። ብዙዎች ጋር እንዳሉ ማመን ያስፈልጋል። ምክንያቱም አሁንም ይህ ነገር በብዙዎች ውስጥ አለ። መጥፎዎች ገነው ስለወጡ እንጂ ብዙ መጥፎ ስላለ አይደለም። ብዙ በጎ ሰዎች ዝም ስለሚሉ ጥቂቶቹ ክፉ ሰዎች በሚሰሩት ሥራ ስለጎሉ የተከሰተ ነው። እናም ዝም ባዮቹን መልካሞች ማጉላትና እንዲበረታቱ መስራት ያስፈልጋል።
በጎ ሰዎች መልካም ሥራ መስራታቸው እንዲታወቅላቸው አለመፈለጋቸውንና በዝምታ ውስጥ መጓዛቸውን በትንሹም ቢሆን መግታትና ለሌላው ወጥተው በመታየት አርአያነታቸውን ማሳየትም ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሲሆን ጥቂቶቹ ክፉዎች ይጠፋሉ። ስለዚህም መጥፎዎቹን ለማረምና ከስህተታቸው ለመመለስ ሲሉ መልካሞች መውጣት መቻል አለባቸው። ዛሬ ኢትዮጵያ ጎረቤት ተቆጥቶ በመልካም ስብዕና የሚያሳድገው ልጅ ያስፈልጋታል። እናም ማህበረሰቡ በቀደመ ማንነቱና መልካምነቱ ሁሉንም ልጅ መስራት ይኖርበታል።
የእከሌ ዘር፣ የእከሌ ልጅ የሚባል ነገር አሁን መቆም አለበት። ሁሉም ህዝብ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ልጆች ያገባዋል። ምክንያቱም እነዚህ ልጆች ሲያድጉ አገርን ይመራሉ። አገር ደግሞ የሁሉም እንደሆነች ግልጽ ነው። ለዚህ ደግሞ ከልጅነታቸው መስራት ካልተቻለ ካደጉ በኋላ ለማረም መሞከር መስበር እንጂ ማቃናት አይሆንምና የቀደመ ታሪካችንንና መልካምነታችንን ከፈለግን እነዚህን እንተግብር።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ምሁራን ኢትዮጵያ መልካምነቷን እየለቀቀች ነው ይላሉ። እርስዎ ይህንን እንዴት ያዩታል፤ መልካምነታችንን የሚሸረሽሩ ነገሮችስ ምንድናቸው ይላሉ?
ወይዘሮ ማርያ፡- እውነትነት አለው። ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያው ፖለቲካዊ አሰራሩ የተበላሸ መሆኑ ነው። አገር ተረካቢውም መልካም ስብዕና እንዳይኖረው አድርጎታል። ቀደም ሲል ያደግነውና ዛሬ ድረስ ጓደኛ የሆንን ልጆች በምንም መልኩ ብሔራችንን ተጠያይቀን አናውቅም። ማን ምን እንደሆነም ጉዳያችን ሆኖ አያውቅም። ጓደኝነታችን በኢትዮጵያ ባህላችንና በሰውነታችን ብቻ የታነጸ ነው። ይህ ደግሞ መሰረቱ የማይናድ እንዲሆን አድርጎታል። በችግሮቻችን ቀድመን የምንደራረስና ከቤተሰብ በተለየ መልኩ የምንመካከር እንድንሆንም አግዞናል። ዛሬ ግን መቀራረብ ሲጀመር እንኳን በአካባቢ፣ በሰፈርና በብሔር ሆኗል።
ማን ከማን አገር እንደሚወጣ በማይታወቅበት ሁኔታ አንተ ውጣልኝም እየሰማን ነው። ለዚህ ደግሞ ለረጅም ዓመታት በወጣቱ ላይ የተዘራው ክፉ አስተሳሰብ መሰረት ነው። ሰብስቦ ትንሽ ገንዘብ ከፍሎ ከመልካሙ ይልቅ ክፉ መርዝ መስጠት ከዚህ የተለየ ነገር ሊያመጣ አይችልም። የመጠላላት ፖለቲካ ሲሰራም ትርፉ ይህ ነው። የጥላቻ ዘሩ አድጎና አብቦ እዚህ ላይ አድርሶናል። በተለይም ከአንድ ወገን ብቻ ድምጾች ከፍ ብለው መሰማታቸውና ማህበረሰቡ ምንም እንዲል አለመፈቀዱ ብዙ ዋጋ እንድንከፍልም አድርጎናል። በተለይም ምንም የማያውቀውን ወጣት በአንድ መስመር ብቻ እንዲጓዝ አድርጎታል።
በሌላ በኩል የመልካምነት ነቀርሳዎች ክፉ ሀሳቦች ፤ አሳቢ መስሎ ምንአገባሽ ባዮች፤ የጉዳዮች ቶሎ አለመፈጸምና ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች መደራረብ ናቸው። የቢሮክራሲ መብዛትና ፈጥነው ከተደረጉም ውለታ እንዳለብሽ ማሰብ ወደኋላ የሚጎትቱ ነገሮችም ይሆናሉ። ለግል ጥቅም እንደሚደረግ ማሰብም እንዲሁ መልካምነትን የሚሸርሽር ነገር ነው።
ኢትዮጵያን እኮ ከራሳቸው አልፈው የውጪ ዜጎችን ጭምር የሚያስጠልሉ ናቸው። እንደውም ከአገራቸው ልጆች ይበልጥም ሲንከባከቡ የምናየው። ነገር ግን በተዘራብን ክፉ ዘር መገፋፋትን ጀምረናል። ይሁን እንጂ ይህ ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም። ዛሬ መሽቷል ማለት አያስፈልግም። ሥራዎችን ከሰራን ቶሎ የምንፈውሰው ሰው ብዙ እንደሆነ ማመን አለብን። መልካምነቱ ከውስጡ ያልጠፋ ብዙ ወጣት፣ ብዙ ማህበረሰብ አለና ይህንን መጠቀም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው የእልህና ያለመደማመጥ የፖለቲካ ስሪት መልካምነታችንን መሸርሸሩ የተፈጠረ ነው ብለው ያስባሉ?
ወይዘሮ ማርያ፡- አዎ። ከላይ እንዳልኩት ሲገዛ ከነበረ አካል ከተደረገና ለዘመናት ከቆየ የፖለቲካ ስሪቱ ብልሽቱ መልካምነትን በብዙ መልኩ ሸርሽሮታል። ምክንያቱም እኛ ጭምር ስንት ጊዜ ሄደን መልካምነት ፤ ይቅር መባባል ለአገር ይበጃልና እስካሁን የሆነውን እንተወው በሚል ገዢ የነበረውን አካል ለምነናል። ሆኖም እልህና ከእኔ በላይ ለአሳር በሚል ምልከታ ብቻውን ተሸሽጎ ማንም አይንካኝ ብሏል። ይህ ደግሞ ከስልጣን ዞር ሲባል እስከመጨረሻው ለመገዳደል መሞከር መልካምነት ከማጥፋት አይተናነስም። ምንጩም ያላደገ አስተሳሰብ ነው ብዬ አምናለሁ።
በውስጡ ለአገር መልካሙን ብቻ የሚያስብ መንግሽት ሰላምን እንጂ ጠብን አይመኝም። በተለይም ራሱ መርጦ የሾመውን ለመውጋት አይሞክርም። ዶክተር አብይ አሕመድን ህዝብ አልመረጣቸውም። ራሱ የኢህአዴግ መንግሥትን የሚመራው ህወሓት ነው መንግሥት ሆነህ ምራ ያለው። ህዝብ የተቀበለው በፓርላማ ኢትዮጵያዊነትን ሲያነሳ ነው። የእናቶችንና ሴቶችን ክብር ከፍ ሲያደርግ ነው። ከዚያ በፊት ግን አያውቀውም። እንደውም እስከዛሬ በሰራነው ስራ ተጸጽተናል ሲል ሳይቀር የኢትዮጵያ ህዝብን ይቅርታ ሲጠይቅ ነበርም። ታዲያ ዛሬ ምን መጥቶ የኢትዮጵያ ጠላት፤. ተዋጊና ጥላቻ ሰባኪ ሆነ ስንል ሲኖርበት የቆየው የፖለቲካ አስተዳደር የተበላሸ መሆኑን በግልጽ እንድንገነዘብ ያደርገናል።
ጦርነት የሚያመጣው ነገር ቀድሞ ማወቅ የነበረበት እርሱ ነበር። ምክንያቱም በብዙ ትግል ደርግን ተሻግረናል። ሆኖም ያንን ወደጎን በመተው አርቆ አሳቢና ለትውልድ የሚያስቡ ሽማግሌዎች እግሩ ስር ተደፍተው ሲለምኑት አሳፍሮ መልሷቸዋል። ስለዚህም ሲራመድ የቆየው መልካምነትን የማይወድ ፖለቲካ ስለነበር መልካምነት ተመናምኖ እንድናየው ሆነናል። የፖለቲካ ስሪቱ ከማይመስሉ ጋር ተባብሮ የሚሰራበት በመሆኑም እንዲሁ ከሁለቱም ወገን ያሉ ዜጎቻችን እንዲፈጁና ጥላቻ እንዲነግስም አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- መልካምነታችንን ለማጠናከር ምን ማድረግ አለብን?
ወይዘሮ ማርያ፡- መጀመሪያ ሰዎች የሚገኘውን ውጤት ከሚደርሰው ፈተና ጋር ማወዳደር አለባቸው። ምክንያቱም ጊዜያዊ መሰናክሎች ጊዜው ሲደርስ ይፈታሉና። አሁን ያለው ችግርም ጊዜ ይፈልጋል እንጂ ይታለፋል። እናም መልካም በማድረግ ውስጥ ብዙ በሮች ዝግ ሊሆኑ ቢችሉም ፤ እንቢ ባይ ቢበራከትም መውጫ ቀዳዳ እንደማይጠፋ ማመንም ይገባል። ስለዚህም በሩ እንቢ ቢል በመስኮት ለመውጣት የሚያስችል የመልካምነት መንገዶችን መጥረግ የመጀመሪያ ሥራችን መሆን አለበት። መልካም አሳቢ ሰው ሌላ ሰው እያሰበ ስለሚንቀሳቀስ በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጥበት መንገድ የለም። ስለሆነም ተስፋን ማጠንከር ዋነኛ ምግባራችን መሆን ይኖርበታልም።
የእኛ ጉድ በጦርነቱ ድል ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ምክንያቱም ከውጤቱ በኋላ የሚሰራው ሥራ ከባድ እርብርብን የሚጠይቅ ነው። ብዙዎች ተፈናቅለዋል፤ ብዙዎች ቤተሰባቸውን ተነጥቀዋል፤ የጤና ችግር የገጠማቸውም ብዙ ናቸው። የተደፈሩና ብዙ ማገገም የሚፈልጉ ሴቶችም እንዲሁ ቀላል አይደሉም። በሀብት ንብረት ጉዳይም እንዲሁ ተቋማት ላይ የደረሰው ችግርም ተመልሶ አገልግሎት መስጠት አለበትና እነርሱ ላይም መስራት ይገባል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉ የድርሻውን መወጣት አለበት። እስካሁን ላይ ላዩን እንጂ ውስጥ አልዘለቀምና መልካምነታችን የሚፈተነው ከድሉ በኋላ በመሆኑ ለዚህ ዝግጁ መሆን ያስፈልገናል። ልጆቻችን የሚያዩትንና የሚሰሙትን መምረጥም ሌላው ተግባራችን መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ መልካም ሰው በመሆንዎ ምን ተጠቅሜያለሁ ይላሉ ?
ወይዘሮ ማርያ፡- መልካም ነገር አድርጌያለሁ ብዬ ማለት አልችልም። ምክንያቱም ለኪው ሌላ ሰው ነው። ነገር ግን በጎ አስቤ የማደርገው ነገር ብዙ ነገር እንዳላበሰኝና እንደጠቀመኝ አምናለሁ። የመጀመሪያው የአዕምሮ እረፍት እንዳገኝ አግዞኛል። ውስጤ ሰላም እንዲያገኝም አድርጎኛል። መልካም እንቅልፍ ለመተኛቴም መሰረቱ እርሱ ነው። ከዚህ በተጓዳኝ ቤተሰቤ በሌሎች ምርቃት እንዲባረክልኝ ሆኛለሁ። ሁልጊዜ ደስተኛ የምሆንበትን መንገድም ከፍቶልኛል። ከዚህ በላይ ጥቅምም እርካታም አለ ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡- መልካም በማድረግና በአለማድረግ ያለውን ልዩነት ከእርሶ በላይ በቀላሉ የሚረዳ የለምና ለሰዎች ምን ይመክራሉ ?
ወይዘሮ ማርያ፡– መልካም ባለማድረግ ውስጥ ጥቅም ሳይሆን ጉዳት ብቻ ነው ያለው። ጊዜያዊ ደስታ እንኳን ቢሰጥ በምንም መልኩ የአዕምሮ እረፍትን ሊሰጥ አይችልም። በተለይም ደግሞ ቤተሰቡ ሰላም ያጣ ይሆናል። ምክንያቱም በባህሪ ጭምር የአባትና እናት ወራሽ ልጆች ይሆናሉና ሁልጊዜ ቤተሰቡ ከረብሻና ጸብ ሊወጣ አይችልም። መጥፎ ነገር ሁሌ ተቅበዝባዥ ያደርጋልም። የውስጥ ሰላምን ሳይቀር የሚነጥቅ ነው። ስለዚህም መልካም አለመስራት ቤተሰብን፣ የራስን ጤና ይገላል። የሰዎችንም ሰላም ያሳጣል።
ህይወት አጭር ናት፤ መቼ እንደምንሄድ አናውቅም። በተለይ በአሁኑ ወቅት ጦርነትና በሽታ በበዛበት ጊዜ በመጥፎ ተግባራችን መሞት አገርን ጭምር ማሰደብ ነው። ስለዚህም በእያንዳንዱ ቀናችን ስማችንን ከመቃብር በላይ የሚያውል መልካም ስራ ካልሰራን በምድሩም ሆነ በሰማይ የሚኖረን ነገር ጭለማን የተላበሰ ነው። እናም በመልካምነትና በመጥፎነት ሰፊ ልዩነት አላቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ በአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ አገራችን መልካም ነገሮች ብቻ እንዲገጥማት ማን ምን ማድረግ አለበት ይላሉ ?
ወይዘሮ ማርያ፡– መጀመሪያ ትምህርትቤቶች ላይ መስራት ያስፈልጋል። በተለይም ትምህርት አሰጣጡ ላይ ጥብቅና ጥልቅ አሰራር መዘርጋት ይገባል። ለወጣቱ መልካምነትን ማሳየትና አቅጣጫውን ማስተካከልም ተገቢ ነው። የተሳሳተበትን ቦታ በመለየት ትክክለኛውን መንገድ እንዲይዝ ማድረግም አንዱ ሥራችን መሆን አለበት። በተለይም በመንግሥት በኩልና በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ስራ ሊሰራ ይገባል።
በይቅርታ የሆነብንን ብዙ ነገር ማለፍ እንደምንችል ማስተማርም ለነገ መባል የለበትም። ብዙ የተሰራብንን በደል ለቀጣይ መልካም ጉዟችን ስንል ትተነዋል። በበደላችን ልክ አልከፈልንም። ይህ ደግሞ ከዚህ በላይ ዋጋ እንዳንከፍል አድርጎናል። ስለሆነም ወጣቱ ቂምን የሚተውና የቀጣይ አቅጣጫውን በመልካምነት የሚገነባ ማድረግ ላይ ሁሉም ተረባርቦ መስራት ይኖርበታል። በተጨማሪም ከመንግሥት ውጪ ያሉ ማህበራት ታችኛው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ በቀላሉ የመድረስ አቅም ስላላቸው ፕሮግራማቸው ላይ ጭምር ስነምግባርን እያካተቱ መስራት ይኖርባቸዋል።
ጭለማ ውስጥ ያለን የመሰለን ጥቂት መጥፎ ሰዎች ስለጎሉ እንጂ መልካም ሰዎች ስለሌሉ አይደለም። ስለሆነም የማህበራዊ መስተጋብርን የሚያጠነክሩ እንደ እድርና እቁቦችን ጭምር በመጠቀም የስነምግባር ትምህርትን ማስተማር፤ መልካምነትን መስበክ ያስፈልጋል። ሁልጊዜ መመኘት ያለብንም መልካም መልካሙን ብቻ መሆን አለበት። ይህም ያልፋል፤ የተስፋ ስንቅና ብርታት ይሰጣልና ሁሉም ይህንን እያለ፤ እየታገለና እየሰራ ወደፊት መገስገስ ይጠበቅበታል። አዲሱ ዓመት አዲስና ብሩህ ነገር የምናይበት እንዲሆን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
ወይዘሮ ማርያ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2013