መልካም መሆን ለራስ ነው የሚል አባባል አለ። እውነት ነው! መልካምነት መልካም ነገር ከተደረገለት ሰው በላይ የሚያስደስተውና ዋጋ የሚያሰጠው መልካም አድራጊውን ነው። መልካምነት ገንዘብ በመስጠት ብቻ የሚወሰን አይደለም። ቅን ሆኖ ነገሮችን ከማየት፣ በቅንነት ሰዎችን በማገልገል ጭምር ይገለጻል ። ሰዎች ለሰዎች መልካም ነገር የሚያደርጉት፤ የተራበን የሚመግቡት ፤ለታረዘ የሚያለብሱት፣ ላጣ ለነጣ የሚለግሱት ሀብቱ ስላላቸው ብቻ አይደለም። መልካም ስለሆኑ የመስጠት መሰጠት ስላላቸው እንጂ።
ይሄ ደግሞ በመጀመሪያ የሚፈጠረው ከራስ ነው ከውስጥ። ከአስተዳደግ፤ ከአካባቢ ነው። መልካምነት በቤተሰብ ደረጃ በታዛዥነት፣በመከባበር፣ በመረዳዳትና በመተሳሰብ ይገለጻል።
በየትኛውም የእምነት አስተምሮ ውስጥ መልካምነት ጉልህ ስፍራ አለው። ሁሉም አስተምሮ ቅንነትን፣ መረዳዳትን፣ መልካም አስተሳሰብን ይሰብካል፤ ያስተምራል። ስለዚህ መልካምነት እምነትን አይጠይቅም፤ የብሄር ልዩነት የለውም፤ ቀለምና ጾታም አይወስነውም ። ለሰዎች አገልጋይ ፣ለሀገር የሚቆም፣ ታማኝ ሰው ለመሆን ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው። መልካም ሰው ለሰዎች የቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ችግሮች ሲያጋጥሙ፣ ጸብና ግጭት ሲኖር በይቅርታ ይተላለፋል።
ቅንነትን ወደ እያንዳንዳች ወስደን እንየው ስንቶቻችን በተሰማራንበት ሙያና ሥራ ላይ በቅንነት፣ በታማኝነት፣ በመልካም አገልጋይነት እንሰራለን ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ይህን ስናደርግ በእርግጠኝነት ‹‹ እኔ›› ብለን ደፍረን በልበ ሙሉነት ስለራሳችን ለመመስከር እንቸገራለን። ምክንያቱ ደግሞ በአብዛኛው መልካም ተግባር ማድረግ በሚገባን ሙያ ላይ እንኳን ሆነን የተጣለብንን ኃላፊነት የምንወጣ ብዙ አይደለንምና። ነገሮችን በመልካም ጎኑ አይተን የተቸገሩ፣ የታመሙ፣ አገልግሎታችንን የሚፈልጉትን ለማገዝ አንሞክረም ። ይሄ ማለት ግን ሁሉም ባለሙያ ሁሉም የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ መልካም አይደለም ለማለት አይደለም።
ጥቂት የማይባሉ መልካም ሰዎች ከራሳቸው ይልቅ ለሌላው የሚኖሩ የተጎዳን የሚዳብሱ ፣ጎዳና የወደቀን የሚያነሱና የሚሰበስቡ ፤ሰዓት እና ወቅት ሳይገድባቸው ለሀገራቸው ታምነው የቆሙ ብዙ መልካም ሰዎች አሉና። እነዚህ መልካም ሰዎች በህይወት እያሉ በየአደባባዩ ይመሰገናሉ ፤ ይመረቃሉ ። በህይወት ካለፉ በኋላ ደግሞ ስማቸው በታሪክ መዛግብት ሰፍሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍና ሲወሳ ይኖራል። ስም ከመቃብር በላይ ይቀመጣልና።
በመልካምነት ከሚነሱት መካከል በበጎ ሥራቸው የሚታወቁት ወይዘሮ አበበች ጎበና አንዷ ናቸው። እሳቸው ለብዙዎች መኖር ለብዙዎች ስኬት ምክንያት ሆነዋል። ለራሴ የሚሉት ሳይኖራቸው ለሌሎች ኖረው ለወገናቸውና ለሀገራቸው መልካም ሥራ ሰርተው አልፈዋል።
ሀገራቸውን ለማሳደግ ፣በዓለም አደባባይ ሰንደቋ ከፍ እንዲል፣ ዳር ድንበሯ ተከብሮ፣ የነጻነት ተምሳሌት እንድትሆን የሰሩ የሀገር መሪዎች፤ ታዋቂ ሰዎች፣ ምሁራኖች ፣ አርበኞች፣ ወታደሮች … ሌሎችም በሰሩት መልካምነት ሁልጊዜ ይታወሳሉ።
ሰሞኑን የ2013 የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚ የነበሩት ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በህይወት ከተለዩ ከረጅም ዓመት በኋላ ዛሬ ለሽልማት የበቁት ስለሀገራቸው በዓለም አቀፍ መድረክ በሰሩት የዲፕሎማሲ ሥራ ፣በተመዘገበው መልካም ሥራቸው ነው። ሌሎችም በመልካም ሥራቸው ታሪክ የሚያስታውሳቸው ኢትዮጵያ የምታወድሳቸው ብዙዎች ናቸው።
ማንም ሰው በተሰማራበት የሥራ መስክ፣ በሚሰራበት ተቋም፣ በሚኖርበት ሰፈር፣ በሚንቀሳቀስበት አካባቢና መንገዶች ሁሉ መልካም ተግባራትን ማድረግ ይችላል። እያንዳንዱ ሂደታችን መልካምነትን የሚሻ ነው። ዛሬም ለሀገራቸው ለወገናቸው ቀን ከሌሊት ሳይታክቱ የሚለፉ ኢትዮጵያውያን እዚህም እዚያም አሉ። ኢትዮጵያ አትፈርስም ብለው ህይወታቸውን ሳይሰስቱ የሚሰጡ፣ ደጀን ሆነው ስንቅና ትጥቅ የሚያቀብሉ፣ ቆራጥ አመራር የሚሰጡ፣ በቅንነትና በሀቀኝነት ሀገራቸውን የሚያገለግሉ ብዙ መልካም ሰዎች ስማቸውን በወርቅ መዝገብ እያጻፉ ናቸው። መልካም የሆኑ ሰዎች ቢያልፉም የሰሩት መልካም ሥራ ታሪክ ሆኖ ይቀጥላል። መልካምነት ትውልድን ይቀርፃል። ሀገር ይገነባል።ወደ ብልጽናም ያሸጋግራል! ከሁሉ በላይ ደግሞ በምድርም በሰማይም ትልቅ ሽልማት ያሸልማል!
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2013 ዓ.ም