የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር በግልጽ ያመላከተ ነው። በተለይም በስፖርት ማህበራትና ኮሚቴ አመራሮች ምክንያት ስፖርቱ ምን ያህል እንደሚጎዳና አገርም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንደሚያሳጣ በግልጽ አመላክቷል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተፈጠሩ ችግሮችና የተመዘገበው ውጤትም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የስፖርት አመራሩ ተዓማኒነት እንዲያጣ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል የተካረረው አለመግባባት የስፖርቱም ሆነ የስፖርት ቤተሰቡ ራስ ምታት ከሆነ ሰነባብቷል። ጎራ ለይተው በሚያደርጉት ሽኩቻም በስፖርት ባለሙያው መካከል መከፋፈል መፍጠሩም የአደባባይ ሃቅ ነው። እስካሁን ገላጋይ ያልተገኘለት ይህ እሰጣ ገባም በስፖርት አሰራር ጉድለት መኖሩን እንዲሁም ችግሮች ሲፈጠሩ ሊታረሙ የሚችሉበት አግባብ ያልተመቻቸ መሆኑን ያሳየ ነው። ሁለቱ አካላት ከዚህ ቀደም ኦሊምፒኩን አስመልክተው በሰጧቸው መግለጫዎችም ልዩነታቸው የቱን ያህል እንደሰፋ አመላካች ነበር።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኦሊምፒክ መልስ በመግለጫው ከዳሰሳቸው ነጥቦች በተጓዳኝ ለወደፊቱ መቀመጥ ያለባቸው የአሰራር ስርዓቶችና አቅጣጫዎች መካከል ይኸው የአሰራር ችግር መካተቱ የሚታወስ ነው። ከሚመለከተው የመንግስት አካል የፌዴሬሽኑንና የኦሊምፒክ ኮሚቴውን የስራ ኃላፊነትና ተግባር ለይቶ ማሳወቅ ተገቢ መሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአዳማ በተካሄደው የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የ2013 ዓም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2014 ዓም ዕቅድ መድረክ ላይ አነጋጋሪ ሆኖ የወጣው አጀንዳ ይህ የሁለቱ ተቋማት ውዝግብ ነበር።
በመድረኩ ላይ ከክልሎችና ከሌሎች የስፖርት ተቋማት በተነሳው ሃሳብ መሰረትም የተቋማቱን ችግር መፍታትና አደረጃጀታቸውን መመልከት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ከመንግስት በላይ የሆነ ኃይል ባለመኖሩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባ ተመላክቷል። ይህ ካልሆነ ግን ችግሩ ከሁለቱ ተቋማት አልፎ ወደሌሎች የስፖርት ማህበራት ሊዛመት የሚችልና ምልክቶችም እየታዩ ስለመሆኑም በመድረኩ በስፋት ተነስቷል።
የአገሪቷን ስፖርት በበላይነት የሚመራው የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን በበኩሉ በተቋማቱ አለመግባት የተቸገረ መሆኑን ጠቁሟል። ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ሁለቱንም አካላት በተናጥል እንዲሁም በጋራ ለማወያየት እንደሞከረም ኮሚሽነር ኤሊያስ ሽኩር ገልጸዋል። ውዝግብ ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ተቋማት ችግሮቻቸውን ለመፍታት ለውይይት ወንበር ስበው ቢቀመጡም አብረው ለመስራት ከተስማሙ በኋላ ሳይውል ሳያድር በድጋሚ አለመግባባት ውስጥ የሚገቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአዳማው የውይት መድረክ የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሃብታሙ ሲሳይ፤ ከኦሊምፒክ ተሳትፎና ውጤት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር የስፖርት ቤተሰቡን እና መንግስትም ያዘነበት መሆኑን ገልጸዋል። በቶኪዮ ያጋጠሙ ክፍተቶች መልካም ባይሆኑም የስፖርት ችግሮችና መንስኤዎቻቸው ውስብስብ፣ ስር የሰደዱና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ መዋቅራዊ ችግሮች መሆናቸውን እንዳሳየም ሚኒስትር ድኤታው ተናግረዋል። ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀምም ስፖርቱን ለማከም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አመላክተዋል።
‹‹ክስተቱ ከመቼውም በላይ በአገር ክብር፣ ዝና እና መልካም ገጽታ ላይ ጉዳት ያስከተለ በመሆኑ መንግስት ለአገር ክብርና ለህዝብ ጥቅም ሲል አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱ አይቀሬ ጉዳይ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል›› ያሉት ሚኒስትር ድኤታው ለችግሩ እልባት ከማቅረብ ይልቅ ከልክ በላይ የሚያራግቡ፣ ለአገር ክብርና ጥቅም ከመቆም ይልቅ ለግለሰቦች ጠበቃ የሆኑ፣ መሬት ላይ ያለውን እውነታ አፈላልጎ ሚዛናዊ ዘገባ ከማቅረብ ይልቅ የአንድ ወገን ሃሳብ የሚያራግቡ፣ በትብብር ከመስራት ይልቅ በፉክክር የስፖርት ቤተሰቡን የሚጎዱ ግለሰቦችም ለስፖርቱ ሲሉ ሙያዊ የስነምግባር መርሆዎችን እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለኦሊምፒክ ተሳታፊ አትሌቶች እውቅናና ሽልማት በሰጡበት ወቅት፤ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ መንግስት እና ህዝብ ብዙ ጠብቆ እንደነበር ገልፀው፣ ነገር ግን እስካሁን ከተሳተፍንባቸው ኦሊምፒኮች ያነሰ ውጤት መመዝገቡን ማስታወሳቸው ይታወቃል። በመሆኑም በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ችግሮችን በመለየት ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንደገና ሊደራጁ እንደሚገባ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተፈጠሩ ችግሮች አመላካች መሆናቸውንም የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን በድረገጹ አስነብቧል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013