አርሶ አደር ቦጋለ ወልደ ሀና ይባላሉ። የወንጌል መምህር በመሆናቸውም ፓስተር ተብለውም ይጠራሉ።ትዳር ከመሠረቱ 33 ዓመታቸው ሲሆን ሁለት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል።ተወልደው ያደጉት በሲዳማ ክልል አርቤጎና ወረዳ ቶጋ ቀበሌ ውስጥ ነው።ትኩስ ወተት ጠጥተውና ከገብስ፣ከእንሰትና ከእንስሳት ተዋዕጾ የሚሰራውን ጨምሮ በአትክልትና ፍራፍሬ የበለፀጉ ምግቦች እየተመገቡ ነው ያደጉት።
ስፖርት መስራትና በእግራቸው መጓዝ የዘወትር ተግባራቸው መሆኑን ይናገራሉ። አስቸኳይ ጉዳይ ካልገጠማቸው መኪና አይጠቀሙም። አሁን ዕድሜያቸው ስልሳ ቢደፍንም የ40 ዓመት ጎልማሳ የሚመስል የፊት ገጽታ፣ጠንካራ ጉልበትና ቁመና አላቸው። ጤናማ በመሆናቸው በአካባቢያቸው ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ በእርሻ ሥራ በመትጋት ይታወቃሉ።
ለትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠታቸው ከልጆቻቸው ጀምሮ የአካባቢያቸው ነዋሪ እንዲማር የሚያደርጉት አስተዋጾ ከፍተኛ ነው። አርሶ አደሮችንና ልጆቻቸውን በተለያየ ችግር ጎዳና የወጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፣ጠዋሪ የሌላቸውን፣ አቅመ ደካማ አረጋዊያንንና አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ ይታወቃሉ። የአካባቢያቸውን አርሶ አደር ለጋራ ሥራና ለበለጠ ተጠቃሚነት ማነሳሳት እንዲሁም በተሰማሩበት አካባቢ ለሚገኙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። በአካባቢያቸው ተደማጭ ፣ተወዳጅና የሚከበሩ ሰው ናቸው።
ወላጆቻቸው ብዙም ትምህርት ያልነበራቸው አርሶ አደር ቢሆኑም እርሻውን መደገፍና ውጤታማ ማድረግ ለሚያስችል ዘመናዊ ትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጡ ነበሩ።በመሆኑም ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት በመላክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእርሻ እንዲይዙ አደረጉ።
አርሶ አደር ቦጋለ ወላጆቻቸውን በእርሻ ሥራው ማገዝ በእጅጉ ያስደስታቸው ነበርና ያላቸውን 10 ሄክታር መሬት ለማልማት ሙሉ በሙሉ ወደሚወዱት እርሻ ሥራ ገቡ።በሩሙዳሙ ወረዳ ቶጋ ቀበሌ ሰጋማ አካባቢ በስማቸው ከተመዘገበው ሰባት ሄክታር አራት ሄክታሩን በደን ማልበሱን አሀዱ አሉ። በአንዱ ሄክታር እንሰት ተከሉ ጎን ለጎንም የዓሣ እርባታውን ተያያዙት። ሩሙዳሞ ቀበሌ የሚገኘውን ሁለቱን ሄክታር ማሳ ደግሞ ሰፊ ሀብት ለማፍራት ባስቻላቸው ቡና ተከሉ ።ንብ የማነቡንና ከብት እርባታውንም ቀጠሉ ።በሦስት ሄክታር ቦጨሳ እና ጦጋ ቀበሌ የቡና ማድረቂያ፣ ማበጠሪያ መጋዘን በመገንባት ቀስ በቀስም ወደ ዘመናዊ ጥምር ግብርና ተሸጋገሩ።
‹‹ከግብርናው የማገኘውን ጥሪት ቋጥሮ ማስቀመጥ አልወድም››የሚሉት አርሶ አደር ቦጋለ ለሕብረተሰቡ ኑሮ መሻሻልና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ፋይዳ ባለው ኢንቨስትመንትና ንግድ ስራ እንደሚያውሉትም አጫውተውናል።
ማህበራዊ አገልግሎቶችን በተለያየ መልኩ እየተወጡ መሆናቸውን ይናገራሉ። የትምህርት ቤቶች ግንባታ አንዱ ነው። ብራይት ቪዥን ኮሌጅ አክሲዮን ማህበር፣ ሳንሻይን ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤትን ለማሳያ ይጠቅሳሉ ። በሐዋሳ ከተማ ፒያሳ አክሲዮን ማህበር፣በሐዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ ዱሜ ቀበሌ መምቦ ሆቴል ፣ ያዬ ኤስ ዲ ሲ መምቦ ሆቴል ቁጥር ሁለትን አፍርተዋል። በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይ ለቡና እርሻ ልማት ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ። ይህም ትልቅ ገቢና አቅም እንደፈጠረላቸው አልሸሸጉም ።
አርሶ አደሩ የልጅነት ዘመናቸውን ዘወር ብለው ሲያስታውሱ ሕይወታቸው ከታዳጊነት ጀምሮ ከእርሻ ሥራ ጋር የተቆራኘ ነው።እርሻውና አራሹም ዘመናዊ እንዲሆን ጥረት ማድረጉንም ያኔ ከወላጆቻቸው ወርሰዋልና ዛሬም ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የራሳቸውን እርሻ ባለሙበት ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በተለይ የቡና ዋጋ ከበቆሎ ዋጋ ባነሰ ለአካባቢው ገበያ ይቀርብ እንደነበር ይናገራሉ።
በዚህም አርሶ አደሩ ሰፊ ተጠቃሚ አለመሆኑ አብዝቶ ያሳስባቸው ነበር። ቡናቸውን በአካባቢውና እንደ ሀገር ላለው ገበያ ለማቅረብ የሚያስፈልግ ማጠቢያና ማበጠሪያ አለመኖሩም ሲከነክናቸው ኖሯል። ይሄንኑ አስፈላጊና አሳሳቢ ጉዳይ በአካባቢው ካሉ አምስት አርሶ አደሮች ጋር በመነጋገር አጀንዳ አደረጉ።
የችግሩ ዋነኛ ምንጭ አርሶ አደሩ የሚያመርተው በተበታተነ ሁኔታ መሆኑን አንዱ ምክንያት ነው። የቡና ማጠቢያና ማበጠሪያ ገዝቶ ወደ ውጪ ለመላክና ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉም ሌላው ምክንያት ነው። ለቡና ምርት በሀገር ደረጃ በቂ ትኩረት አለመሰጠቱ ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ለዩ።
ከዚያም ሰብሰብ ብለው በመደራጀት ቢያንስ ሁለቱን ችግሮች የሚቀርፉበትን ሀሳብ አቀረቡ።ምንጊዜም ሀሳባቸው ተቀባይነት የሚያገኝ በመሆኑ ከተመሠረተ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረውና በሲዳማ ክልል ሩሙዳሞ ቀበሌ የሚገኘውን የሩሙዳሞ እሸት ቡና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በቡና ላይ ዝንባሌ ካላቸው አምስቱ አርሶ አደሮች ጋር በመሆን መሠረቱ።ዕምነት ስለተጣለባቸውም ማህበሩን ለመምራት ተመረጡ። የራሳቸውንና የማህበሩን ሥራ በጥምረት መምራት ከፍተኛ ጫና ያለው ቢሆንም በተገቢው መንገድ እየተወጡት ይገኛሉ።
አርሶ አደር ቦጋለ እንዳጫወቱን ዕምነት የጣሉባቸውን አርሶ አደር አባላትም አላሳፈሩም። የራሳቸውን ጨምሮ የግልና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ማህበሩ ቡና ማጠብ ፈቃድ አገኘ ። ቀስ በቀስም የቡና አቅራቢና ላኪነት ፈቃድ አወጡ።
‹‹ከዚህ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን መቋቋሙና ቡናው ባለቤት ማግኘቱ በዘርፉ ለተሰማራነው አርሶ አደሮች የጋራ ተጠቃሚነት የራሴን ጥረት እንዳደርግ አግዞኛል››የሚሉት አርሶ አደር ቦጋለ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው የባለ ልዩ ጠዓም ቡና ውድድር ማህበራቸው እንዲሳተፍ ማድረጋቸውንም ይጠቅሳሉ። መሳተፍ የሚያስችለውን ቡና በማህበሩ 2 ነጥብ 5 ሄክታር ማሳ ላይ በጥራት እንዲለማ ከማድረግ ጀምሮ የነበረው ጥረታቸው ከባድ ነበር።በራሳቸው ማሳ ከሚያከናውኑት ጋር ተዳምሮ ብዙ መድከማቸውን ያስታውሳሉ።
አሁን ድረስ ከማሳው አጠገብ በሚገኝ ሰርቪስ ቤት ለመኖር ተገደዋል።24 ኬሻ የተበጠረና የተለቀመ ቡና በጥራት ማቅረብና 90 ነጥብ 89 በማምጣት ሁለተኛ ደግሞ ስምንተኛ ወጥቶ በከፍተኛ ዶላር እንዲሸጥ ላስቻለው ውድድር እንዲቀርብ ማድረግ ቀላል ኃላፊነት እንዳልነበረ ይናገራሉ። በየሰርክ ሥራቸው ከ300 የማህበሩ አርሶ አደር ደንበኞችና ከሌሎች አርሶ አደሮች ቡና መሰብሰብ ያደክማል። ጊዜንም በአግባቡ መጠቀም ይጠይቃል።
በዘንድሮው ዓመት ለነበረው ውድድር ሁለት ኮንቴይነር የታጠበ ቡና ለማህበራቸው ለማቅረብም በተመሳሳይ ደክመዋል። ይሄንኑ በተለያየ ደረጃ አሸናፊ የሆነ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የቴክኖሎጂ ውጤት በሆኑ ዘዴዎች ከ40 ሀገራት በላይ ዜግነት ካላቸው ቡና ፈላጊ ደንበኞች ጋር ግንኙነት ማድረግና በዋጋ መደራደሩም የእርሳቸውን ኃላፊነት ጠይቋል። ጥረታቸው እንደ ማህበር ለአካባቢው መካከል 80 በመቶ ወንድ ሲሆኑ 20 በመቶ ሴቶች ናቸው።
‹‹በማህበሩ የማደርገው ጥረት በግሌ ከማካሂደው የግብርና ሥራ ጋር ተዳምሮ ሀብት እንዳፈራ አስችሎኛል››ይላሉ አበርክቶውን ሲገልፁ።በግላቸው 150 ሚሊዮን ጥሬ ብር ቋጥረዋል ። ተንቀሳቃሽ ንብረት ከተባለ ደግሞ ቡና ማበጠሪያ ማሽን ጨምሮ ብዙ ሀብቶች አፍርተዋል።
ገጠር ላይ ለትምህርት ቤትና ለሌሎች ልማቶች እየተዘጋጁ ያሉ ንብረቶች አሏቸው።መምቦ የተሰኘው ሆቴላቸው በርካታ ሱቆችና ንግድ ቤቶችን ያካተተ በመሆኑ ከፍተኛ ገቢ ባለቤት አድርጓቸዋል። አሣና ከብት እርባታን ጨምሮ ከሰብል እርሻ የሚያገኟቸውንና ከቤት ቀለብ የሚተርፋቸውን ለገበያ በማቅረብም የሚያገኙት ዳጎስ ያለ ገንዘብ አለ።በቡና ዘርፍ በሚያንቀሳቅሱት ንግድ ለ50 ቋሚ ሠራተኞች ፣ 350 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
በተለይ በቡና ለቀማው የሚያሳትፏቸው በሙሉ ሴቶች ናቸው።አርቢ ጉናም ሐዋሳም ደረጃቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶች አሏቸው። በእግራቸው መጓዝና ተንቀሳቅሰው መሥራት ቢያዘወትሩም ዘመናዊ የቤትና የሥራ መኪኖች ባለቤትም ናቸው።
እንደ ማህበርም በዘላቂነት ጥቅሙን እየተጋሩት ያሉት የማይንቀሳቀስ ሀብት አፍርተዋል።በማህበሩ ስም ባለ አምስት ወለል የአክሲዮን ማህበራቸውን ጨምሮ ለ12 የሰሩት ሁለት ትላልቅ ህንፃ ባለቤት መሆናቸው ተጠቃሽ ነው።
አርሶ አደር ቦጋለ መንግሥት ወደፊት ቦታ ከሰጣቸው ወደ ውጪ በሚላኩና ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ በሚያስገኙ የቅባት እህሎች እርሻ ላይ በስፋት የመሰማራት ዕቅድ አላቸው።የሲዳማን ቡና አብቃይ አርሶ አደሮች በዓለም ደረጃ በቡና ምርት የሀገራቸውንና የራሳቸውን ስም እንዲያስጠሩ ብሎም በቡና ምርት የላቀ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ራዕያቸው ነው።
አርሶ አደሩ ለስኬቱም በአሁኑ ወቅት በልማቱ በስፋት መሰማራት የሚያስችለውን አቅም በማህበሩ አማካኝነት እንዲፈጥሩ ከማድረግ ባለፈም መንግሥት የአነስተኛ ብድር ተጠቃሚ እንዲያደርጋቸው በግልና በማሕበራቸው አማካኝነት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በተለይ በግላቸው የአርቤ ጉና ወረዳንና በሲዳማ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ድጋፍ እንደሚያደርጉም አንዳንድ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና ሠራተኞቻቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል ።
ከእነዚህ አስተያያት ሰጪዎች መካከል የሲዳማ አርቤ ጉና ወረዳ ሩሙዳሞ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሂርጶ ቦልጫ ይጠቀሳሉ። የራሴ የሚሉት የእርሻ ማሳም ሆነ ምንም ዓይነት ገቢና ትዳር የላቸውም። ልጅም አልወለዱም።የዕለት ጉርሳቸውን የሚያገኙት በአካባቢያቸው እየተዘዋወሩ ያገኙትን ሥራ በመስራት ነበር።ሆኖም ዕድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ ስራውን መሥራት ተስኗቸው ቤት ዋሉ።
ይሄን የሰሙት አርሶ አደር ቦጋለ ሙሉ በሙሉ የዕለት ጉርሳቸውን እየሸፈኑላቸው ይገኛሉ። በተለይ አውድ ዓመት ሲሆን ለበዓል የሚያስፈልጋቸውን ወጪ በሙሉ ይሸፍኑላቸዋል።
ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ወጣት ጥላሁን ቶቴ ከሐዋሳ እርሻ ኮሌጅ በእርሻ ዲፕሎማ አለው።ሆኖም በዲፕሎማው ቶሎ ሥራ ባለማግኘቱ እግሩ እስኪቀጥን ስራ ፍለጋ ተንከራትቷል። በዚህ አጋጣሚ ለእሱና ለሌሎች የአካባቢው ወጣቶች አርሶ አደር ቦጋለ በሰጡት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ቻለ። በአሁኑ ወቅት በአርሶ አደሩ እርሻ ልማት ውስጥ በሂሳብ ሹምነት ያገለግላል።
በዚህ ላይ አሁን በልምድ እየሰራበት የሚገኘውን የሂሳብ ሹምነት ለማጠናከር የሚያስችል የዲግሪ ትምህርቱን በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያስተማሩት ይገኛሉ።ትምህርቱን ለመከታተል የሚያስችለውን ግብዓት ጨምሮ ክፍያውን በሙሉ የሚሸፍኑት እርሳቸው ናቸው።በዚህ ላይ በየዓመቱ ቡና ሲሰበሰብና ዳጎስ ያለ ገቢ ሲያስገቡ እስከ 50 ሺህ ብር የዘለቀ ማበረታቻ ይሰጡታል።
ወጣቱ እንደሚለው ባለሀብቱ በተለይ ለትምህርት ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ።ለአብነትም ለ40 የአካባቢው ነዋሪ ልጆች ደብተር፣ ስኪሪብቶና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በማሟላት ወጪያቸውንና ቀለባቸውን ሸፍነው ያስተምራሉ። በተጨማሪም ሐዋሳ ሩሞዳሞ የቡና ሳይት አካባቢ የሚረድዋቸው ታዳጊ ተማሪዎች አሉ።
ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪና በአርሶ አደሩ ንብረት በገንዘብ ያዢነት እንዲሁም ገቢና ወጪውን በመቆጣጠር የምታገለግለው ወይዘሪት ታደለች ቹሌ ናት።ወይዘሪት ታደለች እንደምትናገረው፤ በሙያው ከፍተኛ ልምድና ሰርተፍኬት አላት። ለመቀጠርም የተለያዩ ተቋማት ጋር ተወዳድራለች። ስራውን በተገቢው መንገድ መስራት እንደምትችል ቢረዱም በሙያው ዲግሪ ስለሌላት ሊያሰሯት ባለመቻላቸውና ወላጆቿን መጦር የሚያስችላት ገቢ ባለማግኘቷ ስትቸገር ኖራለች።
በዚህ ትምህርት ዝግጅቷ ተከታታይ ስልጠና እንድትወስድ በማድረግ ብቃቷን አጎልብተው ሊቀጥሯት የቻሉት ግን አርሶ አደር ቦጋለ ብቻ ናቸው። አሁን ላይ በምታገኘው ገቢ ወላጆቿን ማስተዳደር ችላለች። በተለይ ዳጎስ ያለ ገቢ ሲገኝና ለአውድ ዓመት የሚሰጣት ጉርሻ አስፈላጊውን የቤት ፍጆታና ቁሳቁስ እንድታሟላ አስችሏታል። ለሕብረተሰቡ የሚያደርጉት ድጋፍም ሰፊ መሆኑን ተረድታለች።
የማህበሩ ዋና ፀሐፊ ታምሬ ቃሬ ስለ አርሶ አደሩ ቅን ሥራ ይመሰክራሉ። እሳቸውን ጨምሮ በዘርፉ ለተሰማሩና ለቡና አብቃይ አርሶ አደሮች አርአያ ናቸው።በጋራ ሥራ ያላቸው ዕምነት ትልቅ ነው። የማህበሩ አባላት ውጤታማ ሆነው ሀብት እንዲያፈሩ በማስቻል የእርሳቸው ሚና ጉልህ ነው። ካፒታልን ከማስቀመጥ ይልቅ ለሥራ እንዲውል በማድረግ ጥሩ ልምድ ማስፋት ችለዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013