ሀገር ትቀየር ዘንድ ዕድገትና ለውጥ የምናስብ ከሆነ ድልና ስንፍና ተጋብተው አብረው መኖር አይችሉም። ስንፍና ባለበት ድል የለም፣ ስንፍና ባለበት ብልፅግና የለም፣ ስንፍና ባለበት መሻሻል የለም። ማደግ መበልፀግ የሚሹ ዜጎች ከስንፍና ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና መፍጠር አይገባቸውም።
ዜጎች ትንሽ ጉልበት፣ ጥቂት ጊዜ፣ ትልቅ የአገልጋይነት መንፈስ ካላቸው ሃገር ይገነባል። በእርግጥ በአሁን ወቅት ሀገራችን በፈጣን የለውጥ ሂደት ውስጥ ናት። ባለፉት ሶስት ዓመታት ሀገራችን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለውጦችን እያስመዘገበች ትገኛለች። እነዚህ እየተመዘገቡ ያሉት ዘርፈ ብዙ ለውጦች ቀጣይነት የሚኖራቸው ዜጎች ተገቢውን አገልግሎት ያለምንም አድልዎ ሲያገኙና መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ሲቻል ነው።
መልካም አስተዳደርን ማስፈን የአንድ ጀንበር ስራ ካለመሆኑም ባሻገር የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚጠይቅ ተግባር ነው። በእርግጥ ማህበረሰብን በማገልገል ውስጥ የሚነሱ ጥንካሬዎች እንዳሉ ድክመቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ስለሆነም በድክመት የሚታሰቡ ጉዳዮችን ዳግም እንዳይፈፀሙ እያስተካከሉ መሄድ ተገቢ ነው። የመንግሥት መዋቅሩ ማለትም ከፌዴራል እስከ ወረዳ ያለው ከፍተኛ አመራሩ፣ መካከለኛ አመራሩ፣ የቡድን መሪው እና የመላው ሲቪል ሰርቫንትን ድርሻ ወሳኝነት በውል መረዳትም አስፈላጊ ነው።
አገልግሎት ሰጪውም ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት እንዲሁም በመልካም ሥነ-ምግባር የማገልገል ዓላማውን እንዲወጣ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥረት መደረግ ይኖርበታል። ይህም ሲባል የአገልጋይነት ስሜት እንዲጎለብት ሁሉም በተሰማራበት ሙያ በብቃት፣ በተመደበለት ጊዜ የበኩሉን መወጣት እንዲችል ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር ይኖርባቸዋል።
የአገልጋይነት ስሜት መጎልበት ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት የጀርባ አጥነት በመሆኑ ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና ይጫወታል። በዚህ ትልቅ አቅም ባለው የሰው ኃይል ላይ የአገልጋይነት መንፈስን ማስፈን የሚቻለው ሁሉም በተሰማራበት መስክ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መንፈስ ህዝብን ማገልገል ክብር እንደሆነ ተገንዝቦ ተግባራዊ ሲያደርግ ነው። የመንግስት ተቋማት ሀገርንና ህዝብን በቅንነት የማገልገል ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር የተቀበሉ አካላት ናቸው። በመሆኑም መንግስት ለህዝብ የሚያቀርበውን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ የሰው ሃይል ማጎልበት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ይሆናል።
ለዚህም አገልግሎት ሰጪው መንግስት የቀረጻቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አምኖ የመቀበል እንዲሁም በቅንነትና በታማኝነት ህዝብን የማገልገል ኃላፊነት መውሰድ አለበት። ምክንያቱም መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግሉ በርካታ ሲቪል ሰርቫንት እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው አንዳንዶች ደግሞ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ተጠቅመው የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ እንዳሉ እሙን ነውና።
የአገልጋይነትን መንፈስ የበለጠ ለማሳደግ ግለሰቦች ለሰሩት ጥፋት ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ከማስቀመጥ ጎን ለጎን የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በአዳዲስ አሰራሮች ማዘመን መቻል የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። መንግስት በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እንዳሉ ቢታመንም በየደረጃው ያለው እያንዳንዱ ሲቪል ሰርቫንት ህዝብን ማገልገል ድርብ ክብር መሆኑን ከመረዳት ባሻገር የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት መወጣት ይኖርበታል።
የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ያለው፤ ህዝብ ሲጠቀም፣ እጠቀማለሁ፤ ሀገር ስታድግ አብሬ አድጋለሁ፤ የሚል አገልጋይ ሀገራዊ ራዕይ ያለው ነው። በመሆኑም በማህበረሰቡ ውስጥ ተሰግስገው ለግል ጥቅማቸው የሚጥሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ለህግ አሳልፎ የመስጠት ባህላችን ሊዳብር ይገባል። እንደነዚህ ያሉ ኃላፊነት የማይሰማቸውን ስግብግቦች ከአገልግሎት ሰጪው የተደበቁ አይደሉምና ለህግ አሳልፎ መስጠት ተገቢ ነው።
በሌላ መልኩም መንግስትም የአገልግሎት ሰጪውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል አቅም በፈቀደ ሁሉ እያደረገ ያለውን ጥረትም ማጠናከር ይኖርበታል። ለዚህም ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ስግብግብ ነጋዴዎችን ማገድ፣ ህዝብን ባሳተፈ መልኩ ስርቆትና ወንጀልን መከላከል፣ የህብረተሰብን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ዓይነተኛ ማሳያዎች ናቸው። አገልግሎት ሰጪው መንግስት የነደፋቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በሚገባ ተረድቶ ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ሲጀምር ሀገር ታድጋለች፤ ትበለፅጋለች።
በአጠቃላይ ሀገራችን የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ እንድትደርስ ያላትን የሰው ሀብት በተለይም የተማረን የሰው ኃይል በተደራጀ መልኩ በአስተዳደር እርከን ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረጉ ጅማሮ ሊጠናከር የሚገባው ነው። ምክንያቱም በአገልግሎት መስጫ ተቋማት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ተጠያቂነት ያለው ስርዓት በየደረጃው ተግባራዊ ሲሆን ሀገርን ወደ ተሻለ ደረጃ የማሳደግ ዕድል ይከፍታልና ነው።
በመሆኑም ህዝብን ማገልገል ድርብ ክብር ነውና ሁሉም ሲቪል ሰርቫንት ህብረተሰቡን በንፁህ የአገልጋይነት ስሜት ሊያገለግልና ከህብረተሰቡ ጋር አብሬ እጠቀማለሁ የሚል አስተሳሰብን በማጎልበት ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና በብቃት መስራት ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013