ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ የአበረታች ንጥረነገር (ዶፒንግ) ሰለባ እየሆኑ እንደሚገኙ የሁለት ኦሊምፒኮች የአስር ሺ ሜትር አሸናፊዋ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ተናግራለች።
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት እየመራች የምትገኘው እንቁዋ ኦሊምፒያን ደራርቱ ቱሉ ከሳምንት በፊት የዓለም ከሃያ ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በናይሮቢ ሲካሄድ ከኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጋር በነበራት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአቋራጭ ገንዘብ ለማግኘት አበረታች ንጥረ ነገሮችን ተጠቅመው ብቃታቸውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለማሳደግ ጥረት ያደርጋሉ ስትል ወቀሳ ሰንዝራለች።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓለም አበረታች ንጥረ ነገር ስጋት ከሆነባቸው ሰባት አገራት አንዷ መሆኗን የዓለም አትሌቲክስ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን የፈረጃት ሲሆን፣ ደራርቱ ቱሉ ባለፈው ታህሳስ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆና መመረጧን ተከትሎ በአበረታች ንጥረ ነገር የጎደፈውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስምና ዝና ለመመለስ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ተናግራለች።
እኤአ 1992 ላይ በባርሴሎና ኦሊምፒክ በአስር ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አትሌት የሆነችው ደራርቱ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ከአበረታች ንጥረነገር የፀዳ ለማድረግ በምትመራው ፌዴሬሽን በኩል የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ አበረታች ውጤትም እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቁማለች።
አበረታች ንጥረነገሮች በአዲስ አበባ በቀላሉ እንደሚገኙና ይህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አደጋ ውስጥ መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ ማሳሰቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ የአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት የሚያስከትለውን አደጋ ለወጣት አትሌቶች ለማስተማርና ለመከላከል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ።
‹‹በእኛ ዘመን ንፁህ ሆነን ነው ስንወዳደር የነበረው፣ ያለን ተሰጥኦም ነበር ለድል ሲያበቃን የነበረው፣ ውድድሩ ሁሉ በእኛ ዘመን ጤናማ ነበር፣ አሁን ግን በአቋራጭ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል አትሌቶች የአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ›› በማለት ደራርቱ ለዴይሊ ኔሽን ተናግራለች። ይህም አንዳንድ አትሌቶችን ለአጭር ጊዜ ውጤታማ ሆነው በዚያው ሳይዘልቁ በአጭር አመት ከውድድር እንዲጠፉ ማድረጉን ደራርቱ አስረድታለች።
ደራርቱ አያይዛም አትሌቲክስ በአሁኑ ወቅት ከቀድሞው እየተለወጠ እንደመጣና ከጊዜው ጋር አብሮ መጓዝ እንደሚያስፈልግ ጠቁማለች፡፡ በርካታ አገራት በስፖርቱ ጠንክረው በመስራት ወደፊት መጥተው ጠንካራ ተፎካካሪና ውጤታማ እየሆኑ እንደሚገኙም ባለፈው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ መታዘቧን አስቀምጣለች፡፡ ፉክክሮች እየጠነከሩ መሄዳቸውን ተከትሎም አዳዲስ ባለተሰጥኦ አትሌቶችን ማፍራት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አክላለች፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ገናና ስም ባተረፈችበት የአትሌቲክስ ስፖርት አትሌቶች አውቀውም ይሁን ባለማወቅ የዚህ ችግር ሰለባ እንዳይሆኑ በብሔራዊ ደረጃ የፀረ አበረታች ቅመሞች ፅህፈት ቤት ተቋቁሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዓለምአቀፍ ደረጃ የተመሰገነ አበረታች ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ጎረቤታሞቹ የምስራቅ አፍሪካ የረጅም ርቀት ፈርጦች ኬንያና ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ያላቸውን መልካም ስም ያህል ከአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በስፖርቱ ትልቅ አደጋ እንዳንዣበበባቸው ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአትሌቲክሱ አበረታች መድሃኒት ወይም ንጥረ ነገሮች ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ሩሲያንን የመሳሰሉ ታላላቅ አገራት ከታላላቅ ውድድሮች እስከ መታገድ ደርሰዋል፡፡ እነዚህ አገራት አትሌቶቻቸው በብዛት አበረታች መድሃኒት ተጠቃሚ ሆነው ከመገኘታቸው ጋር ተያይዞ በመንግስት ጭምር ይደገፋሉ በሚል ከውድድሮች መታገዳቸው ይታወቃል፡፡ የዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች መድሃኒቶች ኤጀንሲ እነ ሩሲያን በቀጣበት ወቅት ኢትዮጵያና ኬንያ አደጋው በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሰጋቸው በማሳወቅ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምክረ ሃሳብ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡
ሁለቱ አገራት በተለይም ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታ በመስራት አበረታች ውጤት ማስመዝገቧም በኤጀንሲው ጭምር ተመስክሮላታል፡፡ ያም ሆኖ ስጋቱ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ለማለት አይቻልም፡፡ ባለፈው ዓመት የዓለም አትሌቲክስ ኢትዮጵያና ኬንያን በአበረታች መድሃኒት (ዶፒንግ) ምክንያት ስጋት ካለባቸው አገራት ቀዳሚውን ደረጃ እንደሚይዙ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ በ2020 ሁለቱ አገራት በአበረታች መድሃኒት ስጋት ቁንጮውን ደረጃ መያዛቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ ለዚህም በወቅቱ በጥቂት ወራት ብቻ አምስት የአፍሪካ አገራት አትሌቶች አበረታች መድሃኒት ተጠቃሚ ሆነው መገኘታቸው ማሳያ ተደርጓል፡፡ ቤላሩስና ዩክሬን ሁለቱን የአፍሪካ አገራት ተከትሎ ስማቸው ከቁንጮዎቹ ተርታ ተጽፏል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2013