ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ የገባው መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በአንድ ጃፓናዊ ተጠርጣሪ ነበር። እንደ ሀገር ከፍተኛ ውጥረት እና ፍርሃት የተፈጠረበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል። ኮቪድ-19 ከቻይና ተነስቶ በርካታ የዓለም ሀገራት ካዳረሰ በኋላ ነበር ወደ እኛ ሀገር የገባው። ይህ ደግሞ ቅድመ ዝግጅቶችን በተገቢው ደረጃ ለማድረግ አቅም እና እድል ፈጥሯል። በቫይረሱ አንድ የነበረው ተጠርጣሪ በየእለቱ ቁጥሩ እየጨመረ ከመሄድ ባሻገር ሞት መመዝገብ ጀመረ። የቫይረሱ ስርጭት በየጊዜው እየጨመረ እና በከፍተኛ ሁኔታ በማሻቀብ ከመጀመሪያ ማዕበልነት ወደ ሁለት ተሸጋገረ። የመዘናጋት ስሜቱም ቀጠለ። በበሽታው የሚያዙ ሆነ ህይወታቸው የሚያልፈው ሰዎች ቁጥር አብሮ ማሻቀቡን ቀጠለ። የስርጭቱ መጠን በፍጥነት በመጨመር ሦስተኛ ማዕበል በቅርቡ መከሰቱን ሰማን።
ሦስተኛ ማዕበል
በሀገራችን የሦስተኛው ማዕበል ከመጣ በኋላ በአብዛኛው ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ህሙማን በማሽን ዕርዳታ የሚተነፍሱ፤ ኦክስጂን በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈልጉ፤ በጽኑ ህመም የታመሙ ታካሚዎች በተለያዩ የህክምና ማዕከላት እየተጨናነቁ ይገኛል። በተለይም በፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ የወጣቶች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። በሽታው እንደዚህ ቀደሙ ተጓዳኝ ህመም ያላቸውን፤ ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች ብቻ የሚያጠቃ ሳይሆን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እየጎዳ መሆኑን ነው። በአጠቃላይ በሀገራችን የኮቪድ 19 ስርጭት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ህብረተሰቡ ይህንን አዲስ እውነታ በመረዳት ራሱን በአግባቡ ከወረርሽኙ መጠበቅ እንደሚኖርበት የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ። በተጨማሪ ደግሞ በተለያዩ የጤና ተቋማት በመሄድ የኮቪድ-19 ክትባትን መውሰድ እንደሚኖርበት ይመክራሉ።
የማህበረሰቡን በሽታውን የመከላከል አቅም ከፍ ማድረግ የኮቪድ-19 ስርጭት መቆጣጠር እና መከላከል የሚቻልበት አንዱ አማራጭ መሆኑንም አብረው ያነሳሉ። የመከላከል አቅምን ከፍ ለማድረግ ደግሞ ክትባት መከተብ ትልቁ አማራጭ መሆኑን ያመላክታሉ። የዓለም ሀገራት ኮቪድ-19 መድሃኒት የሌለው መሆኑን ተከትሎ በሽታውን ለመከላከል ክትባትን ዋነኛ አማራጭ አድርገው መጠቀም ከጀመሩ ውለው አድረዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ወቅታዊ ምክርም ክትባት መውሰድ መቻል ከበሽታው መዳኛ መንገድ መሆኑን ነው። ስለዚህ በእኛም ሀገር የኮቪድ-19 ክትባትን ለህብረተሰቡ በስፋት ተደራሽ ማድረግ መቻሉ በሽታውን መግታት የሚያስችል ስለመሆኑ ይታመናል።
በሀገራችን ሦስተኛው ማዕበል የደረሰውን የኮቪድ-19 ስርጭት ለመቆጣጠር ክትባቱን በሰፊው ተደራሽ ማድረግ የሚገባ መሆኑን ይጠቁመናል። የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነት በኢትዮጵያ ምን ይመስላል፤ አጠቃላይ እንቅስቃሴውስ ምን መልክ እንዳለው መመልከት ይገባል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ደግሞ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የብሔራዊ ክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ እና የእናቶች እና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ ላቀው አስተያየት ሰጥተውናል። አቶ ዮሃንስ በሀገራችን የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነትን በተመለከተ ወደ ኋላ ሁለት ዓመት ከነበረው ሁኔታ በመነሳት እንደሚከተለው ያብራራሉ።
ሁለቱ መጋቢቶች
ኮቪድ-19 መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ሀገራችን በገባ በአንድ ዓመቱ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ክትባቱ በሀገራችን መሰጠት እንደተጀመረም ይገልጻሉ። በወቅቱ ሀገሪቱ ያላትን አቅም መሰረት ባደረገ መልኩ በርካቶች ክትባቱን እንዲወስዱ መደረጉን ያስታወቁት አቶ ዮሃንስ፤ የጤና ሚኒስቴር ክትባቱ በቀዳሚነት ለጤና ባለሙያዎች፣ እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ እንዲሁም እድሜያቸው ከ50 እስከ 60 ሆኖ ተጓዳኝ ህመም ላለባቸው እንዲሰጥ መመሪያ በማውጣት ክትባቱ እንዲሰጥ ማድረጉን ይናገራሉ።
አቶ ዮሃንስ ሲያብራሩ፤ በወቅቱ ኮቫክስ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ትስስር ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ92 በማደግ ላይ ላሉ እና ለታዳጊ አገሮች ክትባቱን ያቀረበው በጣም ተጋላጭ ለሆኑ 20 በመቶ ለሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ነው። ይህ በመሆኑ ተጋላጭ የሆኑ ከአጠቃላይ ከማህበራዊ ህይወት እና ከጤና አንፃር በመመልከት ክትባቱን ቅድሚያ እንዲሰጥ ነው የተደረገው። በዚህ መልኩ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት ከመጋቢት 2013 ዓ.ም አንስቶ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ክትባቱን መውሰድ ችለዋል።
የኮሮና ቫይረስ ክትባት በኢትዮጵያ መሰጠት ሲጀምር ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የተደረጉ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ይናገራሉ። ይህም የሆነው ወደ ሀገራችን ተጨማሪ ቫክሲን ማስገባት ከመቻሉ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ያመለክታሉ። በክትባቱ ተደራሽነት መመሪያ ላይ የተደረገው ለውጥ ወይም ማሻሻያ፤ በተለይ አዲስ አበባ ላይ ማንኛውም ከ35 ዓመት በላይ የሆነ እና ከ18 ዓመት በላይ ሆኖ ተጓዳኝ ያለበት የከተማዋ ነዋሪ በአካባቢው ባለ የጤና ተቋም እንዲከተቡ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን ይገልጻሉ። በተጨማሪም በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች የሚገኙ ከእድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎች ክትባቱን መውሰድ እንዲችሉ መደረጉንም ያብራራሉ።
ዓለም አቀፍ ሽሚያ
በሀገሪቱ ክትባቱን የወሰዱት ሰዎች ቁጥር አጥጋቢ የሚባል እንዳልሆነ እና መንግስትም ሆነ ጤና ሚኒስቴር ሁሉንም ህዝብ መከተብ ቢችል ጥሩ እንደነበር ያመላከቱት አቶ ዮሃንስ፤ “በዓለም አቀፍ ደረጃ የክትባት እጥረት በመኖሩ ክትባቱ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እና በሚፈለገው ልክ ለማዳረስ ከባድ አድርጎታል። በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለ።
በእኛ በኩል ፍላጎቱን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች ለማድረግ ተሞክሮ ነበር። ነገር ግን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ግን ዋነኛ ችግር ፈጥረውብናል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የቫክሲን እጥረት አለ። ይህም ክትባቱን ለማስገባት ዓለም አቀፍ ሽሚያ መኖሩ ቫክሲኑን ገዝቶ ማስገባት ራሱ እንዳይቻል አድርጓል። ነገር ግን በኢኮኖሚው ጠንካራ የሚባሉ ሀገራት ሳይቀር ፍላጎታቸውን እያሟሉ ይገኛል። ይህን ተከትሎ አሁን የሚታየው ሽሚያ ቀዝቀዝ እያለ ሲመጣ ነገሮች ይስተካከላሉ ተብሎ ይታሰባል” ነው ያሉት።
ቀጣዩ እቅድ
በሀገሪቱ የክትባቱን ተደራሽነት በማስፋት ረገድ በተለየ መልኩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ያመላከቱት የብሔራዊ ክትባት ፕሮግራም አስተባባሪው አቶ ዮሃንስ፤ “በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ ክትባቱን ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ይገኛል።
በ2014 ዓ.ም ሚኒስቴሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ 20 ሚሊዮን ሰዎችን የኮቪድ-19 ክትባትን ለመስጠት እቅድ ተይዟል። ይህም ክትባቱን ተደራሽ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ያመላክታል”። በቀጣዩ ዓመት ክትባቱን ለመስጠት እቅድ የተያዘው እንደ ሀገር ያለውን የቫክሲን መጠንን መሠረት ያደረገ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ዮሃንስ፤ ወደ ሀገራችን ተጨማሪ ቫክሲን ማስገባት ከተቻለ ቁጥሩ ከፍ ሊል የሚችል መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በመጨረሻም አቶ ዮሃንስ፤ ክትባቱን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ በተያዘው እቅድ ላይ በተለየ መልኩ ደግሞ በሥራ ባህርያቸው ተጋላጭ ተብለው የተለዩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የኢኮኖሚ ሴክተሮች መሰረት ባደረገ መልኩ ክትባቱን በስፋት እንደሚሰጥ ያመላክታሉ።
ከእነዚህ ከተለዩት ተቋማት መካከል የትራንስፖርት ዘርፍ፣ የግልና የመንግሥት ባንኮች፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት የሚኖሩ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2013