የትምህርት ተቋማት የእውቀት መሸመቻ ገበያዎች ናቸው። በዚህ የተነሳ ላለፉት እልፍ ዘመናት በባህላዊ መንገድ ፊደል መቁጠሪያ የሆኑት ትላልቅ የዛፍ መጠለያዎች ጭምር ክብራቸው ወደር የለውም። የኔታንማ በሙሉ ዓይን ቀና ብሎ ማየትም ከድፍረት ይቆጠር ነበር።
ዘመናዊ የቀለም ትምህርት መቅሰሚያ የሆነው አስኳላ ከመጣም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች እስከ አስተማሪዎቻቸው ክብራቸው የትየለሌ ነው። ተቋማቱ በልጆችና በማህበረሰቡ የእውቀት ገበያ አስተማሪዎች ደግሞ የእውቀት አባት ተደርገው ተከብረውና አድባር ሆነው ለእልፍ ዘመናት ኖረዋል። አሁን አሁን የሚሰማው ግን ለጆሮ ይከብዳል፤ ይሰቀጥጣል።
ትምህርት ቤቶች የእውቀት ምንጭነታቸው ነጠፈ፤ የዘረኝነት ምንጭነታቸው አቆጠቆጠ። ተቋማቱ የአእምሮ ማዳበሪያ፣ ማበልጸጊያ፣ የምርምርና የእውቀት መፍለቂያ፣ የሰላም፣ የእድገት መሰረት መሆን ሲገባቸው፤ እነሱ ግን ወደ ፀብ ማዕከልነት ዝቅ አሉ።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቆዩባቸው ዓመታት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ብሄርተኝነትን፣ ከአገር ይልቅ ዘርን፣ ከእውቀት ቀንድነት ክብር ይልቅ የአድርባይነት መረዳታቸውን የሚናገሩ ወጣቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም።
ዛሬ ላይ ግን ታሪኩ ተቀይሮ የተገላቢጦሽ ሆኗል። በዩኒቨርሲቲዎች የሚታየው፣ የሚሰማው የፀበኝነት መንፈስ ከመስረጹ ባሻገር፤ የሚራመዱት አስተሳሰቦች የከፍተኛ ትምህርት ተቋምን የማይመጥኑ ናቸው። ይህ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎቹን ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰቦች ከሚያራምዱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተርታ አውርዶ ወደ መንደር ከቷቸዋል።
በአሁኑ ወቅት የተቋማቱ እንቅስቃሴ ከፈተሽን ከአገራዊ እሳቤ ዝቅ ብሎ ወደ መንደር የወረደበትን ሁኔታ ያስመለክተናል። ሁኔታው ጠንከር ብሎ መውጣቱ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ልዩነቶችን በንግግር ሳይሆን በድብድብ ለመፍታት የሚሞክሩ፣ በዘር ቆጠራ ተጽዕኖ ሥር የወደቁ ተማሪዎች የሚፈሩበት፣ ተቋማቱም ዘመኑን ባልዋጁ ምክንያት አልባ ብጥብጦች የሚናጡ መሆኑ ክብር አልባ አድርጓቸዋል።
በዚህ ብቻ ሳያበቃ ከፀብ መንደርነት ተሻግረው ወደ ሞት መናኸሪያነት እስከመቀየር የደረሱ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ የማህበረሰቡን እምነት አሳጥቷቸዋል።
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማህበረሰቡ ልጆቹን ልኮ በእውቀት ከሚታነጹለት የሚቀጠቀጡበት ጊዜ በመስፋቱ ወደ ጦር ሜዳ የሚልክ እንጂ ወደ እውቀት ገበያው የሚልክ አልመስል እያለው ተላቅሶ ይሸኛል።
የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ያሰጋው ደግሞ ተማሪም ሆነ ወላጅ ከትውልድ አካባቢው ርቆ መሄድ ስላስፈራው በግል ዩኒቨርሲቲ ከፍሎ ማስተማርን መፍትሄ በማድረግ ከችግሩ ለማምለጥ ሲሞክር ታዝበናል።
ብዙዎች እንዲህ አይነቱን አማራጭ እያደረጉ ይገኛል። ይህ ለመሆኑ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ከምርምር ማዕከልነት ወደ ፀብ ማእከልነት መውረዳቸው ዋነኛው ምክንያት ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ለዚህ ሃሳብ ማጠናከሪያ እንዲሆን ሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አንድ በቅርቡ አውጥቶት የነበረን መረጃ እንመልከት።
ዘንድሮ አዲስ ከሚገቡ ተማሪዎቹ መካከል ከ23 ሺህ በላይ ተማሪዎች ቅሬታን ማስተናገዳቸውን ይፋ አድርጓል። ከምደባ ጋር ተያይዞ ከቀረቡት አጠቃላይ ቅሬታዎች ከ1 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ የምደባ ማስተካከያ ተደርጎላቸዋል የሚለውን መረጃ ይዘን ወደ ዋናው ነጥባችን እንሻገር። አዲስ ገቢ በሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከምደባ ጋር ተያይዞ ቅሬታ እንዲያነሱ ያስገደዳቸው ምክንያት ምን ይሆን? በሁላችንም አዕምሮ የሚመላለስ ጥያቄ መሆኑ አይቀሬ ነው።
በዚህ ደረጃ ቅሬታዎች የተወለዱት በዩኒቨርሲቲዎች ከሚታዩ ተደጋጋሚ ግጭቶች እንደሆኑ በተለያየ መልኩ ያገኘኋቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። ታዲያ ዩኒቨርሲቲዎቻችን በዚህ ደረጃ የጠፋውን እምነት ለመመለስ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ይጠበቃል። በተቋማቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሠላማዊ ለማድረግ በቂ ዝግጅት አድርገናል! የሚሉ የጋዜጣዊ መግለጫዎች ጋጋታዎችን ሣይሆን ተጨባጭ ስራዎችን ሰርቶ ማሳየትን እንደሚጠይቅ እሙን ነው።
̋ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ነውና ተረቱ፤ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ለመፍትሄው ትኩረት መስጠት ከቻሉ እንደ ተቋም ብቻ ሳይሆን ለሀገር የሚተርፍ ሠላም፣ ፍቅር፣ አንድነት የዋጀ እውቀትን በመስጠት ይኼንኑ የማሳየት አቅም አላቸው።
በመንግስትም በኩል በተመሳሳይ ለመፍትሄው መስራት ይኖርበታል። በዚህ ረገድ መንግስት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን የሰላም እጦት ዳግም ጉዳይ እንዳይሆን የተለያዩ ስራዎችን ከመስራት እንዳልቦዘነ በተደጋጋሚ ይናገራል። በየጊዜ መፍትሄ ያላቸውን ሃሳቦች በማመንጨት ወደ ተግባር እየለወጠ ለመፍትሄው እያባዘነ ይገኛል።
ከሰሞኑ እንደተለመደው የችግሩን ሰንኮፍ በዘላቂነት ነቅሎ ለመጣል እንደሚያግዝ ተስፋ የተደረገበትን አንድ ንድፈ ሃሳብ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ አድርጓል።
በዩኒቨርሲቲዎች የሚታየውን የሰላም ችግሮች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ መፍትሄ ለመስጠት ጥረቶች እየተደረጉ የሚገኙ መሆኑን ይገልጻል። “በመሆኑም ሚኒስቴሩ ስር የሰደደውን ችግር መፍትሄ ለማበጀት በመተለይም በቅርቡ በዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ትምህርት መስጠት የሚጀምር ይሆናል። በ2014 ዓ.ም በተመረጡ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች በሙከራ ደረጃ የሰላም ትምህርት መስጠት ይጀመራል” ሲል ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰላም ትምህርት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ጋር በመተባበር ትምህርቱን ለመስጠት መታሰቡንም ነው ያብራራው።
ሚኒስቴሩ ከዩኔስኮና ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተውጣጡ ምሁራን ጋር በጉዳዩ ላይ በቢሾፍቱ ከተማ ምክክር መደረጉን ገልጾ፤ በዚህ ምክክር ላይ በተመረጡ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች በሙከራ ደረጃ የሰላም ትምህርት ለመስጠት ከውሳኔ የተደረሰ ስለመሆኑም በመረጃው አስታውቋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው፤ የሰላም ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስጠት ያስፈለገው ነባራዊ አገራዊ ሁኔታውን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሆኑንም ይናገራሉ። በዚህም ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስተዋሉ የሰላም እጦት ችግሮችን ለመፍታት ትምህርቱ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ይገልጻሉ።
“ስለዚህ በ2014 ዓ.ም ጎንደር፣ ዋቸሞ፣ አሶሳ፣ ሰመራ፣ ቡሌ ሆራ እና ደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ትምህርት እንደ አንድ ኮርስ ለመስጠት የመጀመሪያ የሙከራ ትግበራ የሚደረግባቸው ናቸው። በ2014 ዓ.ም በሁለተኛ ሴሚስተር ላይ ትምህርቱን መስጠት የሚጀምሩ ይሆናል። ከሙከራው የሚገኙ ልምድና ተሞክሮዎችን በመቀመር በመላ አገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱን የመስጠት እቅድ አለ” ሲሉ ከሙከራ ባሻገር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱን ተደራሽ የማድረግ እቅድ መኖሩን ነው ያስታወቁት።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2013