ለኢትዮጲያዊነት አንድ ወጥ ትርጉም ለመስጠት መሞከር አንድም የዋህነት ከዛም በላይ አላዋቂነት ነው። ኢትዮጲያዊነት ቅኔ ነው ፤ ባለ ብዙ ሰምና ወርቅ ፤ እንደየዘመኑ የሚፈታ ፤ በደረስክበት ደረጃ ፤ በሆንክበት መጠን ተረድተህ የምትሻገረው የብዙ ውቅር ማንነቶች ውህድ ነው ።
ይህ ውህድ ማንነት ረቂቅ የትስስር ገመዳችን ደግሞም ውበታችን ነው ። በዚህ ፍጥረታዊ ውህድ ውስጥ አንድም ፤ ብዙም ነን ፤ግለሰብም ማህበረሰብ ነን። ሀገርና ህዝብ ነን ፤ በዚህ ደግሞ ዘመናትን ተሻግረናል።
ይህ ውህድ ማንነት የብዙ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶች ፤ ከዚህ የሚመነጬ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰቦች ባለቤት እንድንሆን አስችሎናል። የብዙ ሰብአዊ አሴቶች ባለሀብትም አድርጎናል።
ቀደም ባለው ዘመን እነዚህ እሴቶቻችን የትላልቅ ስልጣኔዎች ባለቤት አድርገውናል። ባህር ተሻግረን ሰንደቅ ዓላማችንን በኩራትና በልበ ሙሉነት የምናውለበልብ ህዝቦች ነበርን። ይህም የትናንት ማንነታቸን መገለጫ ነው።
ለዚህ ለሰለጠነው ዓለምና ትውልድ እንቆቅልሽ በሆነ ፤ እስካሁንም ባልተፈታ እውነታ ውስጥ ትላልቅ ቋጥኞችን ፈልፍለን ቤተ መቅደሶችን መገንባት ችለናል ፤ በዚህም ከፍያለ የይቻላል መንፈስ ባለቤት የሆኑ አባቶች ልጆች ነን።
አክሱምና ላሊበላን የመሳሰሉ ድንቅ ቅርሶችን ከአንድ ቋጥኝ ፈልፍለን ማቆም የቻልን። በዚህም የዛሬውን ማንነታችንን የበለጠ ሚስጥር ያደረግን ፣ ለራሳችን ጭምር ያልተፈታ እንቆቅልሽ የሆንን የብዙ ወቅር ማንነቶች ባለቤት ነን ።
በዘመናት መካከል ለራሳችን እንቆቅልሽ የሆነብንን የውህድ ማንነት ውቅር መረዳት የሚያስችል የፋታ ዘመን አጥተን በግጭት አዙሪት ውስጥ ስንባክን የኖርን በዚህም የጉስቁልናና የረሀብተኝነት ምሳሌ ሆነን ኖረን የነበረ ሕዝብ ነን ።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ ከፍ ያለ የተስፋ ዘር ቃል በውስጣችን ተሸክመን ፤ሸክሙ በየዘመኑ እያንገዳገደ ዋጋ የሚያስከፍለን ፤ ወደቁ አበቃላቸው ስንባል ፤ቆመን ስንራመድ የምንገኝ ፤ ተስፋ ቢስ ሆነዋል ስንባል በተስፋ ተሞልተን የምንገኝም ድንቅ ህዝቦች ነን።
በአስቸጋሪ የፈተና ወቅት እንደሚታየው ልዩነታችንን መሰረት አድርገው ከእንግዲህ ቋንቋቸው ተደበላልቋል ስንባል ፤ በአንድ ቋንቋ የምንናገር ፤ ከቋንቋም ባለፈ በስሜትና በመንፈስ አንድ የሆነ ሰራዊት ሆነን የምንተምም ነን። ይህ ሁሉ ከኢትዮጲያዊነት መገለጫ ከብዙ በጥቂቱ ነው።
በየዘመኑ ለህዝባቸው ተስፋ እራሳቸውን ሰማዕታት አድርገው ለማለፍ ከራሳቸው ጋር ሁለቴ ለመምከር የማያስቡ ጀግኖችና ያፈራችና በማፍራት ላይ ያለች ሀገር ነች። ስለ ሀገርና ህዝብ መሞት ዘላለማዊ ህያውነት ነው ብለው የሚያምኑ ፤ ለታሪክ ከፍ ያለ ከበሬታ ያላቸው አባቶችም ልጆች ነን።
ከዚህ የተነሳ የነጻነት ቀንዲል ተደርገን የምንቂጠር፤ ሥለ ነጻነት መሞት ብቻ ሳይሆን ስለ ነጻነት መሞት ክብር መሆኑን ለብዙ የአለም ህዝቦች በመሞት ማስተማር የቻልን ፤ በዚህም አለም የሚዘክረን ህዝቦች ነን።
እንግዳ እግር አጥበው ፣ አብልተው እና አጠጥተው አልጋቸውን ለቀው በክብር የሚያስተናግዱ፤ይቅር ለማለትና ለመመለስ የማያስቸግሩ፤ ለወዳጅነት የቀረቡ ለአብሮነት የተሰጡ አባቶች ልጆች ነን ።
ዛሬ ላይ ብዙዎች ለራሳቸው እጣ ፈንታ የኛን የህይወት መንገድ ዱካ የሚጠብቁ ፤ተነሱ ስንባል አብረው ልባቸው ከኛ ጋር የሚነሳ፤ ወደቁ ሲባል ልባቸው የሚወድቅ ተስፈኞችን በብዙ ከኋላችን ያሰለፍን የተስፋ ዘር ቃል ባለቤቶች ነን።
በየዘመኑ ለመነሳት በምናደርጋቸው ጥረቶች በሁሉም አቅጣጫ ጠላት ሆ ብሎ የሚተምብን ፤እውነተኛ ማንነታቸው ባጡ የገዛ ወገኖቻችን መንገዳችን በተግዳሮት የሚታጠሩብን ፤ በዚህም ዋጋ ለመክፈል የምንገደድ ሕዝቦች ነን።
የልበ ሩህሩሆች ልጆች የመሆናችንን ያህል የልበደንዳኖች ልጆችም ጭምር የሆንን ፤ልባቸው በደነደኑ የገዛ ወገኖቻችን ያልተገቡ የህይወት መንገዶችን ለመሄድ የምንገደድ ፤ ለዚህም በየዘመኑ ዋጋ እየከፈልን የተስፋ ዘመናችንን የምናርቅ ሕዝቦችም ነን ።ይህ ሁሉ ኢትዮጲያዊነት እና መገለጫው ነው።
አሁን ግን ተስፋችንን ለመጨበጥ የመጨረሻው መጀመሪያ በሚባል የታሪክ ምዕራፍ ላይ የምንገኝ ፤ከተግዳሮቶች ሁሉ በላይ በሆነ መንገድ ላይ የምንጓዝ ፤ተስፋችንን አሻግረን ከማየት ወጥተን ተስፋችንን ለመውረስ መንገድ የጀመርን ህዝቦች ነን።
የትኛውም ተግዳሮት ከጀመርነው የተስፋ መንገድ አያወጣንም ፤ የብዙ ውቅር ማንነቶች ውህድ የመሆናቸንን ሚስጥር የተስፋችን መሰረት ብቻ ሳይሆን ተስፋ ወራሽነታችን ሚስጥር ነው። ይህን እውነታ በተረዳነው መጠን ወደ ተስፋችን እንቀርባለን ተስፋችንንም እንወርሳለን። ሁሉ የሆነውን ለኢትዮጲያዊነት ትርጉምም ለአለም እንገልጻለን!
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2013