ኳታር በ2022 በምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በምድብ ሰባት የአፍሪካ አገራት ማጣሪያ ጨዋታ ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጀመሪያ ፍልሚያውን ከትናት በስቲያ ምሽት 4፡00 ላይ አድርጓል። በኬት ኮስት ስቴድየም በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት ጥቁር ከዋክብቱን የጋና ብሔራዊ ቡድን የገጠሙት ዋልያዎቹ የአንድ ለዜሮ ሽንፈት አስተናግደዋል፡፡
የተጫዋቾች ማልያ በላብ ረጥቦ በሰውነታቸው እስኪጣበቅ ድረስ እጅግ ፈታኝ በሆነው ሞቃት የአየር ንብረት ውስጥ ከሜዳቸው ውጪ ፍልሚያውን ያደረጉት ዋልያዎቹ ግብ ተቆጥሮባቸው በመውጣታቸው ብቻ ሽንፈት ተብሎ ይጠራ እንጂ ገናና ስም ያላቸውን ጥቁር ከዋክብት ገጥመው በጨዋታው ያሳዩት አስደናቂ እንቅስቃሴ እንደ ድል የሚቆጠር ነው፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በሚጫወቱ ከዋክብት የተሞላው የአሰልጣኝ ቻርልስ አክኖር ስብስብ በጨዋታው ዋልያዎቹ ካላቸው የእግር ኳስ ደረጃ አንፃር በቀላሉ እንደሚያሸንፍ ግምት ተሰጥቶት ወደ ሜዳ የገባ ቢሆንም በጨዋታው የታየው ነገር ተቃራኒ ነው፡፡
የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የዋልያዎቹ ስብስብ ከጨዋታ ታክቲክ ጀምሮ በኳስ ቁጥጥርና በማራኪ ጨዋታ ጥቁር ከዋክብቱን አፍ ያስያዘ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ የዋልያዎቹ ስብስብ ቀድሞ ከሚታሙበት የአሰልጣኙን ታክቲክ በትክክል በመተግበር ረገድ ከጥቃቅን ስህተቶች በስተቀር በብዙ መልኩ መሻሻል ባሳዩበት ጨዋታ ለማሸነፍ ያደረጉት ተጋድሎና ጉጉት የተለየ ነበር፡፡ በአንፃሩ ጥቁር ከዋክብቱ በሜዳና በደጋፊያቸው ፊት እንዳላቸው ስምና ዝና እንዲሁም የቡድን ጥራት ረገድ ፈሪ ሆነው ታይተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይሁን እንጂ ያገኙትን የዋልያዎቹን አንድ የአጋጣሚ ስህተት ተጠቅመው ከጨዋታው የሚፈልጉትን ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ችለዋል፡፡
በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ዋልያዎቹ መከላከልንና ኳስን መሰረት ያደረገ ጨዋታ ላይ ትኩረት በማድረግ የጥቁር ከዋክብቱን በር በተደጋጋሚ ለማንኳኳት አልደፈሩም ነበር፡፡ ይህም ከሜዳቸው ውጪ ጥንቃቄ በተሞላው ጨዋታ ቢያንስ ነጥብ ተጋርተው ለመመለስ አስበው አሰልጣኝ ውበቱ የተከተሉት የጨዋታ ስልት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ያም ሆኖ እስከ ሰላሳ አምስተኛው ደቂቃ ድረስ ዋልያዎቹ በጨዋታው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እየተወጡና የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ በነበረበት ሰዓት ግብ ጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆ የሰራው ስህተት ዋጋ እስከፍሏቸዋል፡፡ ተክለማርያም በእሱ ደረጃ ባሉ ግብ ጠባቂዎች የማይሰራ ተራ ስህተት በመስራቱ ከርቀት ተመታበት ኳስ ከመረብ ማረፉ ለዋልያዎቹ አስደንጋጭና የግብ ጠባቂዎቻችንም የቴክኒክ ጥራት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር፡፡ ቀድሞውንም ባላሰቡት መንገድ ያነሰ ስምና የቡድን ጥራት በያዙት በዋልያዎቹ ያልጠበቁት የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው ጥቁር ከዋክብቱ በተክለማርያም ስህተት በለስ የቀናቸውን ግብ ይዘው ለረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ ዋልያዎቹ እንደ ከዚህ ቀደሙ በጥቃቅን ስህተት ጥሩ ተጫውተው ግብ ሲቆተርባቸው ተስፋ የመቁረጥና ተጨማሪ ግብ የማስተናገድ መደነባበር ውስጥ ይገባሉ የሚል ስጋት በበርካቶች ዘንድ ያደረ ቢሆንም አሰልጣኝ ውበቱ ብልሃት የታየበት የተጫዋች ቅያሬ በማድረግ ሁለተኛውን አርባ አምስት ጀምረዋል፡፡ ይህም ስህተቱን የፈጠረው ግብ ጠባቂ ተክለማርያም ስሜታዊ ሆኖ በጨዋታው እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት እንዳያጣና ተጨማሪ ስህተቶችን እንዳይሰራ በወጣቱ የባህርዳር ከነማ ግብ ጠባቂ ፋሲል ገብረሚካኤል ቀይረውታል፡፡ ከዚህም በኋላ ዋልያዎቹ ከመጀመሪያው ጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተሻለ በበላይነት ጨዋታውን ከመቆጣጠር በዘለለ የጥቁር ከዋክብቱን በር በተደጋጋሚ ማንኳኳት ችለዋል፡፡ ያም ሆኖ የጨዋታ ብልጫቸው ኳስን ከመረብ ማገናኘት የሚችል ጥራት ያለው የግብ ሙከራና ውጤት ሊያመጣላቸው አልቻለም፡፡
የዋልያዎቹ ግብ የማስቆጠር ጉጉት እየናረ በሄደ ቁጥር ጥቁር ከዋክብቱ በሜዳቸው የሚጫወቱ አይመስሉም ነበር። ይህም ትልቅ ጫና ውስጥ ስለከተታቸው ተጫዋቾቻቸው በሆነው ባልሆነው ሜዳ ላይ በመውደቅ ሰዓት ለመግደል በተደጋጋሚ እንዲሞክሩ አስገድዷቸዋል፡፡ በሽግግር ላይ እንደሚገኝ የሚነገርለት የጥቁር ከዋክብቱ ስብስብ በዚህ ደረጃ በሜዳና በደጋፊው ፊት ሲርበተበትና አንሶ ሲታይ ከዚህ ቀደም አልተለመደም፡፡
ጨዋታውን የተመለከተ ሁሉ ቆሞ የሚያጨበጭብ እንቅስቃሴ ያደረጉት ዋልያዎቹ በተጫዋቾቹ በኩል በታታሪነትና የጀግንነት ተጋድሎ አድርጎ ጨዋታውን ለማሸነፍ ሁሉንም ነገር አድርገዋል፡፡ አንድ የግብ ጠባቂ ስህተት ብቻ የሚያስቆጭ ነጥብ ነጥቃቸዋለች፡፡ ያም ሆኖ ዋልያዎቹ ከጨዋታው ብዙ ነገር የሚማሩበትና ስብስቡም በቀጣይ ጊዜ እየጠነከረ ሲሄድ በመጪው ጥር በሚካሄደው የካሜሩኑ አፍሪካ ዋንጫ ላይ ከተሳትፎ የዘለለ ቆይታ ሊኖረው እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነው፡፡ ዋልያዎቹ ከሚቆጨው ሽንፈት በኋላ በትናንትናው እለት ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታቸውንም በመጪው ማክሰኞ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስቴድየም ዚምቡዋቤን የሚያስተናግዱ ይሆናል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም