የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በታላላቅ የእግር ኳስ መድረኮች ለመጀመሪያ ጊዜ የነጥብ ጨዋታ ማድረግ የጀመረው ጥር 20 ቀን 1948 እንደሆነ የስፖርት ማህደሮች ያመላክታሉ። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የነጥብ ጨዋታ ለዝግጅቱ ተጫዋቾቹ ካምፕ ተቀምጠው ውጤቱንም ጥሩ ለማድረግ የውጭ አገር አሰልጣኝ ተቀጥሮ ነበር ወደ ውድድር የገባችው። ጨዋታውን ያደረገችውም ከግብጽ ጋር ነው። በተደራጀ መልኩ ብሄራዊ ቡድኑ ተሰርቶ ለውድድር የቀረበውም ያን ጊዜ ነው። ዘመናዊ ስልጠና የሚሰጥ ሰው ተፈልጎ ተገኘ። ይህ ሰው ጆርጅ ብራውን ነው። በኦሰትሪያ ለውንደር ቲም የተጫወተ ነው። በወቅቱ ኦስትሪያ በአውሮፓ ጠንካራ ቡድን የነበራት ነች። ፈዴሬሽኑም ለመጀመሪያ ጊዜ በክፍያ ያመጣው ይህንን አሰልጣኝ ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከብራውን ጀምሮ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ አሰልጣኞችን አፈራርቆ በዓለም ዋንጫ መድረክ ቀርቶ በአፍሪካ ዋንጫ እንኳን እንዳሻው ለመሳተፍ ዳገት ሲሆንበት ተደጋግሞ ታይቷል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ መስራችና ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳች አገር እንደመሆኗ በመሰረተችው የአፍሪካ ዋንጫ ደጋግማ መታየት አለመቻሏ ሁሌም ያስገርማል። እኤአ 2013 ላይ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከሰላሳ አንድ ዓመት በኋላ ዋልያዎቹን በአፍሪካ ዋንጫ እንዲታዩ አድርገዋል። በዚያው ዘመን ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አስደናቂ ጉዞ አድርገው ከአፍሪካ ምርጥ አስር ቡድኖች መካከል ቢመደቡም ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ ስምንት ዓመታትን ወስዶባቸዋል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከስምንት ዓመት በኋላ ዋልያዎቹን ለ2021 የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ባበቁ ማግስት ከትናንት በስቲያ ምሽት ለ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ የሚያደርጉትንም ጉዞ ከትናንት በስቲያ ምሽት ጀምረዋል። በዚህ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ጋር የተደለደሉት ዋልያዎቹ የመጀመሪያውን ማጣሪያ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ከጋና (ጥቁር ከዋክብት) ጋር አድርገዋል። በእግር ኳስ ደረጃዋ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነችው ጋናና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲነሱ ምን ጊዜም የማይዘነጋ አንድ ታሪክ በብዙዎች ዘንድ ይታወሳል። በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም ይህን ከዋልያዎቹና ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር በተያዘ የማይረሳውን አስደናቂ ታሪክ ‹‹ፍትሀዊ የጠጅ ክፍፍል›› ከተሰኘው የጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ መፅሀፍ ቀንጭበን አቅርበነዋል።
ድርጊቱ የተከሠተው በጋና አክራ በተዘጋጀው በአራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ነው። 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ከጋና ጋር እየተጫወተች ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ወደ ጋና ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ በደሎች ሲደርስባቸው ስለነበር በመጥፎ ስሜት ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። በጨዋታው ላይ በጉዳት ምክንያት ያልተሳተፈው ‹‹ኢታሎ ቫሳሎ›› ክራንቹን እንደያዘ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጧል። ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያ ባንዲራ ሆን ተብሎ ተዘቅዝቆ እንዲሰቀል በመደረጉ አምባጓሮ ፈጥሮ እንዲስተካከል ያስደረገው ኢታሎ ነበር።
ኢታሎ የአስመራ ተወላጅ ሲሆን በወቅቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይጫወት ነበር። ጨዋታው ቀጥሏል። በዳኛው አድሏዊነት ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ አንድ ጎል ተቆጠረ። የኢታሎ ንዴት ይበልጥ ናረ! ጎሉ ሲቆጠር በጨዋታው ላይ የክብር እንግዳ የነበሩት የጋናው መከላከያ ሚኒስትር ጄነራል በደስታ ስሜት ተውጠው ከመቀመጫቸው ተነስተው ወደ ሜዳው ሲንደረደሩ መጡ። ኢታሎ ግራ ገብቶት በአይኑ ይከታተላቸው ጀመር። ጄነራሉ ጎሉ አካባቢ ደርሰው የተሰቀለውን የኢትዮጵያ ባንዲራን ያወርዱት ጀመር። ኢታሎ አይኑን ማመን አቃተው። ሲንደረደር ተነስቶ በክራንቹ እየተጎተተ ደረሰባቸውና ጄነራሉን በክራንቹ ጀርባቸውን ብሎ አጋደማቸው። ይህን ያዩ የጋና ፖሊሶችም ኢታሎን ለመያዝ ሲሮጡ መጡ። ከነርሱም ውስጥ ሁለቱን በክራንቹ ብሎ ጣላቸው። ፖሊሶቹ በብዛት ሆነው ከበውት ይደበድቡት ጀመር። ይህን ያዩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችም ሜዳውን ለቀው በመውጣት ከፖሊሶቹ ጋር መደባደብ ጀመሩ!! በቴስታ፣ በእርግጫ ፣ በቡጢ…! ባገኙት ነገር ሁሉ በመደባደብ ቦታውን የጦር አውድማ አስመሰሉት። ባንዲራችን ነዋ የተነካው! በባንዲራቸው እንዴት ይደራደሩ!!… ከብዙ ጥረት በኋላ ግርግሩ ተረጋግቶ ጨዋታውን ሊቀጥሉ ወደ ሜዳ ገቡ። ሜዳ ሲገቡ ግን እነርሱ ድብድቡ ላይ እያሉ የጋና ተጫዋቾች ባዶ ሜዳ ላይ ጎል አስቆጥረው ስለነበር ዳኛው ሁለተኛ ጎል አድርጎ አፀደቀላቸው። በዚህ የተናደደው ኢታሎም በክራንቹ እየተጎተተ ወደ ዳኛው አመራ። አንደኛው ፖሊስ ሊያስቆመው ሲይዘው በክራንቹ ዘረረው። ፖሊሶች ሲከቡት አሁንም የአገራችን ተጫዋቾች ሜዳውን ጥለው ወጥተው ከፖሊሶቹ ጋር 2ኛ ዙር ድብድብ ጀመሩ። በካልቾ… በቴስታ…!! ሜዳው ዳግም ወደ ጦር አውድማነት ተቀየረ። ኢትዮጵያን በዚህ ጨዋታ ላይ በአድልዎ 2 ለ 0 ተሸንፈው ቢወጡም ፣ ጨዋታው ግን ለባንዲራ ክብር ሲባል ጦርነት ቀረሽ ድብድብን በማስተናገዱ ታሪክ ሁሌም ያስታውሰዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም