ሰሞኑን በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር የተጀመረበትን 100ኛ አመት በማስመልከት ለአምስት ቀን የሚቆይ የቴአትር ፌስቲቫል ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በ5ቱ ቀን 447 ከያኒያን የተሳተፉባቸው 46 አንጋፋ ቴአትሮች የቀረቡ ሲሆን ለቴአትር አፍቃሪያን የአይን አዋጅ የሆነ ቡፌ ነበር፡፡ ሰሞኑን ድግሱ እንዲህ ደምቆ ይክረም እንጂ ከዚያ በፊት በነበረው ጊዜ ግን የቴአትር ጀምበር እየጠለቀች መሆኑን አመላካች ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ቢችልም ዋነኞቹ ግን ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው የፊልም እና የቴሌቪዥን ድራማዎች መስፋፋት ነው፡፡ የእነዚህ መፈጠር ሰዎች የቴአትር አምሮታቸውን ያለ ብዙ ድካም በቀላሉ እንዲወጡ ያደረጋቸው ሲሆን የቴአትር አዳራሾች እንዲቀዛቀዙ ያደረገ ምክንያት ነው፡፡
የኢትዮጵያን ቴአትር መከራ ያከበደው ግን የፊልም እና ቴሌቪዥን ድራማ መስፋፋት ብቻ አልነበረም። በማዳከሙ የመንግስትም ድርሻ ከፍ ያለ ነበር። የኪነ ጥበብ ዘርፉን በመሪነት እና በተመራማሪነት የሚከታተሉት እንደ አርቲስት ሰርጸ ፍሬስብሀት ያሉ ምሁራን እንደሚሉት የኪነ ጥበብ ዘርፉ ሆን ተብሎ “ተቋማዊ ስብራት” እንዲገጥመው ተደርጎ ነበር፡፡ በእርግጥም ከለውጡ በፊት የነበረው መንግስት ኪነ ጥበብ ላይ የነበረው ኮስታራ ገጽታ እጅጉን ተጽእኖ ከፈጠረባቸው ዘርፎች መሀከል ዋነኛው ቴአትር ቤቶችን ሲሆን ይህም ቀደም ብለን ከገለጽነው ዲጂታላይዜሽን ጋር ተዳምሮ ቴአትር ቤቶችን ዘመናቸው ያለፈ የኪነ ጥበብ ሊቃውንት የጡረታ ስፍራ አስመስሏቸው ነበር፡፡
ይህ አሳዛኝ ሁኔታ የሚከነክናቸው ሰዎች የቴአትር ብሎም የኪነ ጥበብ ተቋማዊ ትንሳኤ እንዲመጣ በተለያየ መንገድ ሲደክሙ ነበር፡፡ ከነዚህም መሀከል አንደኛው ላለፉት 11 ወራት የቴአትርን መልካም ቀናት ለመመለስ ሲረባረብ የነበረው ስለ ቴአትር አንቅስቃሴ አንዱ ነው፡፡ እንቅስቃሴው የቴአትር ነገር በሚቆረቁራቸው የቴአትር ባለሙያዎች ፤ ምሁራን እና የሚዲያ አካላት የተዋቀረ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስነውን የ5 ቀን ፌስቲቫል ጭምሮ በዚህ አመት ቴአትርን በተመለከተ ያለውን እንቅስቃሴ በሙሉ ሲመራ እና ሲያስተባብር የነበረ እንቅስቃሴ ነው፡፡
ከአስተባባሪዎቹ መሀከል አንዷ የሆነችው አርቲስት መአዛ ወርቁ እንደምትለው ከሆነ እንቅስቃሴው ስኬታማ ጉዞ እያደረገ ነው፡፡ ለዚህም በማሳያነት በቴአትር ቤቶች በራፍ ላይ መታየት የጀመረው የተመልካች ቁጥር መጨመር እና በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ እየጨመረ የመጣው ቴአትርን የተመለከተ ሽፋን ነው፡፡ በቴአትር ዙሪያ ባለው ሙያ በነጻ ለማገልገል እየተንቀሳቀሰ ያለው ሀይል መበራከትም ለቴአትር መልካም ቀናት መመለስ ማሳያ ነው የሚል እምነት በአርቲስት መአዛ እና በሌሎቹም አንቀሳቃሾች ዘንድ አለ፡፡
በእርግጥም ለቴአትር ብሎም ለሌሎችም የኪነ ጥበብ ዘርፎች መልካሙ ቀን የመመለሻው ጊዜ መቃረቡን የሚያመለክቱ ሌሎችም ብዙ ምልክቶች አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከመጡ በኋላ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ወደ ስልጣኑ እየመጡ ነው፡፡ ለዚህም የረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ እና የአርቲስት ሰርጸ ፍሬስብሀት ሹመትን ልንወስድ እንችላለን፡፡ ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በቅርቡ ደግሞ የኢፌዴሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከሳምንታት በፊት ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሰጡት ሽልማትም ከብዙ ዘመን በኋላ የታየ መልካም መንግስታዊ የበጎ ዝንባሌ ምልክት ነው፡፡
የኪነ ጥበብ ተቋማትም እየተገነቡ ነው፡፡ እንጦጦ ፓርክ ውስጥ የተገነባው ግዙፍ የስእል ጋለሪ ፤ የቴአትር አዳራሾችን የያዘው የአድዋ ሙዚየም ፤ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት እድሳት ፤ ለኪነ ጥበብ ምቹ ሆነው እየተገነቡ ያሉ ፓርኮች እና ሌሎችም ግንባታዎች የቴአትር ብሎም የጠቅላላ ኪነ ጥበብ ዘመን ተመልሶ እየመጣ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ምናልባትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኪነ ጥበብ ያላቸው በጎ እይታ ለነዚህ መልካም ነገሮች መከሰት አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን ለቀጣይ አመታትም በጎ ነገር ተስፋ ለማድረግ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህን የቴአትር እና የኪነ ጥበብ ትንሳኤ የሚያዘገዩ ነገሮችም አልታጡም፡፡ ዋነኛው አደናቃፊ የሆነው ኮቪድ ነው፡፡ ወትሮውንም ተዳክሞ ለነበረው ቴአትር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነው ኮቪድ አሁንም ቢሆን የቴአትርን የሽቅብ ጉዞ መጎተቱን አልተወም፡፡ የስለ ቴአትር እንቅስቃሴ ቡድን አባላት እና የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማህበር ኮቪድ እና እሱን ተከትሎ የቴአትር ቤቶች ላይ የተጣለው እቀባ መነሳት እንዳለበት ያምናሉ፡፡
የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል የቢሮ ሀላፊ የሆነው አርቲስት ሰርጸ ፍሬ ስብሃትም ይህ ሁኔታ መስተካከል እንዳለበት ያምናል፡፡ በዚህም በኩል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመመካከር እና ወደ ቴአትር ቤት ፊቱን እያዞረ ያለው ተመልካች የኮቪድ ፕሮቶኮልን ሳይጥስ ገብቶ የሚስተናገድበት ሁኔታን ለማመቻቸት ጥረት መደረግ እንዳለበት ሁለቱም ተስማምተዋል፡፡ ምክትል የቢሮ ሀላፊው ከዚህም ባለፈ አሁን ቴአትርን ለማዳን የተሰበሰቡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በጠቅላላው በኪነ ጥበቡ ውስጥ ያሉ የፖለሲ ማነቆዎችን ለመፍታት ትግል እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ይሁንና ያለፉትን 10 ወራት ቴአትርን ከነበረበት ሰመመን ለመቀስቀስ ሲሰሩ የነበሩት የስለ ቴአትር እንቅስቃሴ እና የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማህበር አባላት በእስካሁኑ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ችግር የነበሩ እና በመጪውም እንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር ሊሆኑ የሚችሉ ሶስት ጉዳዮች እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህም አንደኛው በባለሙያዎች ውስጥ ያለ የአመለካከት ችግር ፤ ሁለተኛ በመንግስት ተቋማት ዘንድ ያለ ቢሮክራሲያዊ ማነቆ እንዲሁም ስራዎችን ለመስራት ያለ የበጀት ችግር ናቸው፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ቀላልም ከባድም ነገሮች አሉ፡፡ ችግር አፈታቱን ከባድ የሚያደርገው እነዚህ ችግሮች በሁሉም ዘርፍ ላይ የሚያጋጥሙ ሀገራዊ ችግር መሆናቸው ነው፡፡ አሁን ሀገሪቱ ያለችበት ጊዜም በራሱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ችግር አፈታቱን ቀላል የሚደርገው ነገር ደግሞ በዋነኝነት ማህበሩም ሆነ እንቅስቃሴው ላለፉት 10 ወራት ያሳዩት ስኬት ነው፡፡ ባለፉት 10 ወራት የነበረው ሂደት እነዚህን ችግሮች ብቻ ሳይሆን ሌላም ችግር መፍታት እንደሚቻል ያመላከቱ ናቸው፡፡
10 ወር ያለበጀት ፤ ከብዙ የአመለካከት እና የቢሮክራሲ ችግሮች ጋር ተናንቆ ቴአትርን ወደ ነፍሱ መመለስ የቻለ ስብስብ አሁንም ብዙ ነገር መፍጠር እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ በሌላ መልኩ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ኪነ ጥበብ ያላቸው በጎ እይታ ትክክለኛ ጠያቂ ካለ ሰሚ ጆሮ እንዳለ ተስፋ እንዲጣልም የሚያደርግ ነው፡፡ አሁን ዘርን በመምራት ላይ ያሉት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሙያቸው ከታገሉ ደግሞ ችግሮችን የማስወገዱ ሂደት የተፋጠነ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ አንጋፋው የቴአትር ጥበብ አሁን መነቃቃት እየታየበት ነውና ይህን ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን እንጠቁማለን፡፡
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም