ሦስት የጥበብ ዘለላ፣ ከሁለት ስፍራዎች ተምሰው በአንድ ስብጥር ከቻልን ሀምራዊ ስናደርጋቸው፣ ሳቢሳ ጥበባቱን ከዚህም ከዚያም አምጥተን ብናዳብላቸው “ጠቦናል ልቀቁን!”፣ አንዱም በሌላው ተነስቶ “ከግዛቴ አስወጡልኝ!” እንደማይባባሉ ተስፋ እናድርግ።
ሀሳብ በሀሳብ፣ ቃላት በቃላት፣ ፊደላቱም በፊደላት ላይ አመጽ እንደማይቀሰቅሱ እርግጠኞች ከመሆን ሌላ አማራጭ የለንም። ምክንያቱም ሳቢሳ ነው። ከወዲህና ወዲያ የተከናወኑ ጉዳዮች ከዚህች አንዲት ገጽ ሞልተው የሚፈሱ ቢሆንም እንደምንም እያሸጋሸግን ከአንዲት መደብ ላይ ማስተኛቱ ግድ ነው።
ከአንድ መሶብ፣ ከጉርሻ ማዕድ ፊት እናስቀምጣቸው። “ፍቅር ካለ ለሁሉም ይበቃል” ይለዋልና ጠጋ በፍቅር ያቆነጃል። የዛሬውን የጥበብ ጎተራ ሊሞሉልን የተዘጋጁ በርከት ያሉ ጉዳዮች ከየፌርማታው ላይ ቆመው እኛኑ ይጠባበቃሉ።
ጥበብ በየፈርጁ ከግራና ቀኝ ከነፈሰው ጋር ነፍሰን፣ ከሚወርደውም ብናፍስ በረከት ነው። ያሳለፍነው ሳምንት በጥበብ ቤት በሽ በሽ ነበር። ከሀሳቦቻችን አንደኛው ሀሳብ መቅረዝ ያቆማቸው ወጣቶችና ተውኔት ያጌጠው መጽሐፍ ነው። ሁለቱም ከአንድ ገበታ ላይ የተገኙ ማዕድ ናቸው።
ወጣቶቹ ጥበብን እያጠገቡን፣ መጽሐፉ ደግሞ “የወንዜ ሳቢሳ” ይለናል። በሦስተኛውና የመጨረሻው ነገር ማስረጊያችን ደግሞ የጥበብ ልጆች ደማምቀው ያመሹበትን የጉማ ሽልማት ስነ ስርዓት በቀጭን ቀጭኑ እንቋጨዋለን፡፡
አስቦና አቅዶም ይሁን ድንገት የጥበብ እግር ጥሎት ወር በገባ በመጀመሪያዋ ቅዱስ ሐሙስ፣ በሐሙሲቷም የጀንበር ማዘቅዘቂያ ላይ ከኢትዮጵያ ቤተ መጽሐፍትና ቤተ መዛግብት(ወመዘክር) አዳራሽ የተገኘ ሰው ከትኩስ የጥበብ አቦል ላይ ይደርሳል። በኪነ ጥበብና ስነ ጽሁፍ ምሽቶች አድገን አሁን መቀንጨር መጀመራችን እሙን ነው።
የሀገራችንን ጥበብ እቅፍ ድግፍ አድርገው የኖሩ ምሽቶች በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደጎን እየተጋደሙ ሲወድቁ ተመናምነው እንጥፍጣፊው እንኳን ናፍቆናል። ታዲያ በአሁኑ ጊዜ በከተማችን አዲስ አበባ ውስጥ ከዓመት እስከ ዓመት፣ ወር እየጠበቁ፣ ወር በገባ በመጀመሪያቱ ሐሙስ ለጥበብ አፍቃሪው አንጀት አርስ ለመሆን የበቁ ወጣቶች ስብስብ አለ። “መቅረዝ” ይሰኛል መጠሪያቸው፡፡
የወሯን የመጀመሪያ ሐሙስ እየጠበቁ የጥበብ ስጦታዎቻቸውን ከመቅረዟ ላይ ያኖራሉ። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተወዳጅነታቸው ከፍ እያለ ዝናቸው መናር ጀምሯል። ገብቶ ለመታደም የቻለ ሁሉ እያመሰገናቸው ይወጣል። እኛም እናመሰግናቸው ዘንድ ከሐሙሶች ሁሉ አንዲቷ ሐሙስ ምክንያታዊ ወኔ ሞልታናለችና ከእርሷ ጋር ጥቂት ሽርሽር እናድርግ፡፡
በጥቅምት አደይ አበባ ታጅባ ሰለል! እያለች የምትመጣው የወርሃ ጥቅምት፣ የመጀመሪያቱ ሐሙስ ባሳለፍነው ሳምንት ጥቅምት 7 ቀን ደርሳ፤ ከሩቅ ቆመው በጉጉት ሲጠባበቋት የነበሩት የመቅረዝ ልጆች ተቀብለዋታል። ታዳሚ አጃቢዎቿን ጋብዘው በወመዘክር አዳራሽ ውስጥ ደግሰው አብልተውላታል። አጠጥተው ሸኝተውላታል። ከበሉትና ከጠጡት፣ እንዲሁም ከተሸኙት መካከል ነንና በልተን ዝም፣ ጠጥተን ጭጭ ብንል ጥበብን “ትዝብት ነው ትርፉ” እናስብላታለን።
ወትሮም አንድ ነገር ብቻ ይዘን ከማንወጣበት የመቅረዞች የኪነ ጥበብ ምሽት በጥቅምት ሰባቷ ሐሙስም ከዝግጅቶቻቸው ጋር የተዋቀረ ሌላ አንድ ዝግጅትም ነበር። ከመቅረዟ ያለፌርማታው መውረድ አይሁንብንና ለሁለተኛው የያዝናትን ጨርሰን ቀጥሎ እንመጣበታለን።
የዕለቱ አመሻሽ ግን ለታደመው የጥበብ አፍቃሪ የሚጣል የሌለው፣ የሚመጠጥ ከረሜላ ነበር። በየመሃል መሃሉ ብቅ እያሉ ከሚቀርቡት ሙዚቃዎች ጋር የታዳሚው ስሜት ሲኮበልል በግልጽ ይታይ ነበር። ልክ እንደ ሁሌም የወሩን በዕለቱ፣ የአንድን ታላቅ የጥበብ ሰው ታሪክና ሥራ እያወሱ ሲተርኩ እንደመስማት ደስ የሚል ነገር አልነበረውም። የዚያን ዕለት ባለተራ ደግሞ ኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎ ነበሩ፡፡
በመቅረዝ የጥበብ ጀመአ ውስጥ መሬት ቆመው ሰማይ የሚቧጥጡ ወጣት ገጣሚያን አሉ። ብዕሮቻቸው በሳልሳና ቡጊቡጊ እየነጠሩ የሚፈሱ ጸሀፊያን በሽ ናቸው። በጥበባዊ ውበት ወግ ወጉን ይዘው በወግና መነባንቦች ፍስሀን የሚያፈልቁ ወጣቶች የመቅረዝን ቤት ሞልተዋታል። ለመጥፋት የሚቃጣቸውን ሽለላና ፉከራ፣ ቀረርቶና መሰሎቻቸው ሁሉ ከመቅረዙ እንዳይወርዱ ወጣቶቹ “መገን!” ይሏቸዋል።
ድምጸ መረዋ፣ ድምጸ ስርቅርቅ የሙዚቃ ባለተሰጥኦ ልጆች ማይኩን ጨብጠው ከመድረኩ ላይ ሲቆሙ አለማድነቅ ያስረግማል። የጥንቱን የኪነት ቡድኖችን ትርኢት ያስታውሱናልና ለአንዳንዶቻችን ከመድረኩ ላይ የቆሙ የኋልዮሽ መስታወቶቻችንም ጭምር ናቸው። ከሁሉም ዓይነት የኪነ ጥበብ ማሠሮዎች ውስጥ እየጨለፉ ታዳሚውን ያጠግቡታልና ቁጥሩ እየጨመረ መሄዱ አልቀረም። ወጣቶቹ ትንታግ ሳተናዎች ናቸው። ክረምት ከበጋው የጥበብን ዘር የሚዘሩ ብርቱ ገበሬዎች መስለው ታዩኝ። ከመድረክ በስተጀርባ ያለውን ጀመአ የጥበብ ህብረታቸውን ስንመለከት ደግሞ ይበልጥ እንወዳቸዋለን። “ሂስ ሳይሆን መዘላዘል ነው ያለው” አለኝ አንደኛው የቡድኑ አባል ሥራዎቻቸው መድረክ ላይ ከመቅረባቸው አስቀድሞ ስለሚዘጋጁበት መንገድ ሲያወጋኝ።
እንደ ጦር እየተወረወሩ የሚሰበቁ የሂስ ቀስቶችን አልፈው እንደሚመጡ ከአቀራረብ ጀምሮ መድረክ ላይ ሲታዩ ያስታውቃሉ። ከስነ ጽሁፍ እስከ ሙዚቃና ተውኔት፤ በግልም ይሁን ጣምራ ክሽን ያለ ሥራና አቀራረብ አላቸው። በመቅረዞች ህብረት ውስጥ ሂስ ያለው ቦታ የተለየ ነው።
ራሳቸውም ይሁኑ ሥራዎቻቸው በዚህ ታሽተው የሚወጡ በመሆናቸው ለጥበብ ውበትን በማልበስ ተወዳሾች ናቸው። መቅረዞች ገና ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ማዕድ አላቸው። ቀኗም የቀን ቅዱስ አትረሳምና ከጥበብ ምንጭ ለመቅዳት ወደ መቅረዝ ወንዝ ወረድ ማለት ብቻ ነው፡፡
በዚያው መድረክ ደግሞ ሌላ በረከት…ጠበቃና የቲያትር ባለሙያው ሳምሶን ብሬ የተመሰጠበትንና ተተርጉመው ቢቀርቡ ለኛም የተሻሉ ነገሮችን ሊከስቱ ይችላሉ ያላቸውን የአንቷን ቼኮቭን አራት የትርጉም ተውኔቶች የያዘውን “የወንዜ ሳቢሳ” የተሰኘ መጽሐፍ አስመርቅቦታል። ወደ መጽሐፉ ከመግባታችን አስቀድመን ቼኮቭ ማነው? ለሚለው ጥቂት ምላሽ ብንፈልግ መልካም ነው።
ቼኮቭ ሩሲያዊ ከያኒ ነው። በአጫጭር ልቦለዶቹና በተውኔት ጽሁፎቹ ዓለም ከምታሞግሳቸውም አንዱ ነው። በኋላኛው የህይወት ዘመኑ እነርሱ ከፊት፣ እርሱ ከኋላቸው ሆኖ ዳናቸውን፣ ኮቴያቸውን እግር በእግር ሲከተላቸውና ሲያስከትሉት፣ ሲመለከታቸውና ሲመለከቱት የነበሩ ታላላቅ የተውኔትና ስነ ጽሁፍ ጠቢባን ከፊቱ ነበሩ።
ሊዮ ቶልስቶይ፣ ቲዮዶር ዴስኮቭስኪ፣ አሌክሳንደር ፑሽኪን፣ ሄነሪ ኤፕሰንና በሌሎችም የዘመኑ ፈርጦች ዓይኑን ተክሎ ልቡን ሰቅሎባቸዋል። ሰተት ብሎ ከመሃከላቸው ወጥቶ ከመንበራቸው ቆመ። ቼኮቭ ከእነርሱ እግር ስር ብቅ ብሎ እንደመታየቱ ሥራዎቹም የማይተናነሳቸው ሆነው ተገኝተዋል። እንዲያውም በአጫጭር ልቦለዶቹ ሳያስንቃቸው ሁሉ አልቀረም ነበር፡፡
“ልቦለዶቹንማ እርሱ ይጻፋቸው። በአጫጭር ልቦለድ ማን እንደቼኮቭ!” ተብሎለታል። በሙያው ሀኪም ቢሆንም የራሱን ህይወትና ስሜቱን ሲያክም የኖረው ግን በስነ ጽሁፉ ነው። “ህክምና ህጋዊ ሚስቴ ስትሆን፣ ስነ ጽሁፍ ደግሞ ውሽማዬ ናት” የሚላት ፌዝ መሳይ የእውነታ ህይወት አለችው፡፡
ከቼኮቭ የተውኔት ሥራዎች መካከል ሳምሶን ብሬ “የወንዜ ሳቢሳ” በሚለው የትርጉም መጽሐፉ ካካተታቸው መካከል አንደኛው “የትንባሆ ጉዳት” የሚለው ነው። ይህ ተውኔት በ1986ዓ.ም ለመታተም በቅቶ ነበር። ደራሲው ግን ከስድስት ዓመታት በኋላ በ1992 ዓ.ም ህይወቱ አልፏል። ከሞቱ ሁለት ዓመታትን ቀደም ብሎ ደግሞ በ1990ዓ.ም በራሱ በቼኮቭ ተሻሽሎ በድጋሚ የታተመ ተውኔት ነበር።
ቼኮቭ “ዘ ሀርምፉል ኢፌክት ኦፍ ትንባሆ” ሲል የጻፈውን ተውኔት ተርጓሚው ሳምሶን ብሬ ደግሞ “የትንባሆ ጉዳት” ሲል ተርጉሞ ከሳቢሳዎቹ አንደኛው አድርጎታል። ተውኔቱ ባለ አንድ ገቢርና ገጸ ባህሪይ ቧልታይ ተውኔት ነው።
በጥቅምት ሰባቱ የመቅረዝ መድረክ ላይ ምሽቱን ካደማመቁ ዝግጅቶች መካከል አንደኛው ይኼው “የወንዜ ሳቢሳ” መጽሐፍ ውስጥ አንዱ የሆነው “የትንባሆ ጉዳት” ተውኔት ነበር። ተርጉሞ ለምርቃት ያበቃው ሳምሶን ብሬ ራሱ ተውኖታል፤ ከላይ እንደምንመለከተው። የተውኔቱን ርዕስ ገና ከመመልከታችን ጭብጡ ስለምንና ምን ላይ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ቀላል መስሎ ቢሰማንም የኋላ ኋላ ሀፍረት እንዳያከናንበን ጥቂት ረጋ እንበል፡፡
ለሰማይ ምድሩ ግልጽ፣ ፊት ለፊት ገጦ ጸሐይ ያሞቀው ቀትረ ቀላል ዓይነት ርዕስ ሆኖ ፊጥ ቢልም፤ ስያሜውን አንብበው ብቻ ስለ ጭብጡ ለማውራት ከቃጣን ቀጣፊ ከማስባል አይምረንም። ምክንያቱም የተውኔቱ ጭብጥ እማሬን ከፍካሬ ጋር ያንጠለጠለ በመሆኑ ነው። ከትንባሆ ጉዳት አስከፊነት ቢነሳም መድረሻው ግን ጉራጉር ውስጥ ይሆንና ብዙ ያስቧጥጠናል።
እዚህ ጋር “ኒውከን” አንድ ለተውኔቱ ገጸ ባህሪይ ነው። ኒውከን ከህይወት ብዙ የተማረ አዋቂ ነው። ኒውከን ግን ኑሮው “ገሪባ!” የሚሉት ዓይነት ነው። በዚህ ላይ ደግሞ ለ30 ዓመታት አብሯት የኖረችው ሚስቱ “የዝናብ ጠፈጠፍ” ናት። በሆነ ባልሆነው ሁሉ ቁምስቅሉን የሚያበላው ምላሷ አይጣል ነው። በኑሮና በትዳር ህይወቱ ምርር! ስልችት! ብሎታል። ሲፈራትም ድመት የተመለከተች አይጥ ያህል ነው።
ካለችው ውልፍት ያለ እንደሆን ውርድ ከራሱ! ኒውከን የረዥም ዘመናት የህይወት ጉዞውን በተውኔቱ ውስጥ እያስተከዘና ሳቅ እያስጫረ ወዲህና ወዲያ በቆሙ ስሜቶች ያስንጠናል።
ታዲያ አንድ ቀን ላይ ለተማሪዎች በበጎ አድራጎት ትምህርት እንዲሰጥ በባለቤቱ በኩል ማሳሰቢያ ይደርሰዋል። “…ትምህርት መስጠት ካለብኝ መስጠት አለብኝ። ይኼው ብቻ ነው ምርጫዬ። በእርግጥ ፕሮፌሰር አይደለሁም። የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ አለኝ ማለትም አልችልም፤ ሳልጨርስ ተባረርኳ። ግን የሆነ ሆኖ ሳይንሳዊ ችግሮች ላይ ለ30 ዓመታት ጤንነቴን ለችግር አጋልጬ ምርምር አድርጌያለሁ።
…አንድ ቀን አንድ ምስጉን መጣጥፍ ጽፌ ነበር። የመጣጥፉ ርዕስ “የሆኑ ነፍሳት ጉዳት” ይሰኛል። …ለዛሬው ትምህርት የምሰጥበት ርዕሰ ጉዳይ የትንባሆ ጉዳት የሚለውን መርጬዋለሁ። ትንባሆ በሰው ዘር ጉዳት አድርሷል፤ እኔ ራሴ ግን አጫሽ ነኝ። …የኔን ትምህርት በቁም ነገር እንድትከታተሉት እፈልጋለሁ። ትምህርቴን በቁም ነገር ካልተከታተላችሁትማ ከሚስቴ ዘንድ ከባድ መከራ ነው የሚወድቅብኝ…ትንባሆ እጽ ነው…” ብሎ ካለ በኋላ ስለ ትንባሆም ሆነ የትንባሆን ስም የጠራው ከሁለት ጊዜና ሁለት ዐረፍተ ነገር አይበልጥም፡፡
እሱም ከጅምር እስከ ማገባደጃው ለተማሪዎቹ ስለ ሚስቱና መከራው ሲያወራ ቆይቶ ድንገት የሷን መምጣት በተመለከተበት ቅጽበት ተርበድብዶ ርዕስ በመቀየር ነበር። ሆኖም ግን ያወራው ነገር ፍካሬያዊ ጭብጡ ስለ ትንባሆ ጉዳት ነበር። የቼኮቭ አራት የተውኔት ሥራዎች “የወንዜ ሳቢሳ”ን ሆነው መምጣታቸው ለስነ ጽሁፍና ቲያትር እድገታችን የሚያስቀስመው ይኖረዋል።
አሁን አሁን የትርጉም ሥራ የሆኑ ተውኔቶችን ከቲያትር መድረኮች ላይ የምናይበት አጋጣሚዎች ጥቂት ናቸው። አቅልን ስተው የሙጢኝ የሚሉበት ባይሆንም “አይመከረም!” የሚባል ደግሞ አይደለም። እንግዲህ “አሳን መብላት በብልሃት” ነው፡፡
በስተመጨረሻ አንዲት የጥበብ መረቅ ጠብ እናድርግባት። ላስታወስን ከዚህ ቀደም በጥቅምት 8 ቀጠሮ ነበረን። ቀጠሮውም የጉማ፣ ዕለቱም በአርብ ነበር። ብዙም ሳንርቅ ከዕለተ ሐሙስ አመሻሽ ወደ ቀጣይዋ ምሽት ሻገር ስንል ጉማን እናገኛለን። ሸራተን አዲስ በጥቅምት 8 የጉማ ምሽት ታላላቆችን ተቀብላ ታላቅ ሆና አምሽታለች። ከአርቲስቶቹ እስከ ጥበብ አፍቃሪያንና የክብር እንግዶች በአዳራሹ ጢም ብለው ታይተዋል።
ቀደም ሲል ያላሰፈርናቸው አንዳንድ ነገሮችን መስፈሪያው በተገኘ መጠን ብናሰፍረው መልካም ነው። በእጩነት ቀርበው ምሽቱ የለያቸውን አደይ ጉማዎችን በአጭሩ እናነሳሳቸው። ባሳለፍነው ሳምንት የአርብ ምሽት የጉማ ሽልማት ስነ ስርዓት እንደ ዝግጅት ባማረ መልኩ ተጠናቋል። የፈራነው ደርሶ፣ የጠላነው ወርሶ እንደሆን ግን ፍርዱን ለናንተው እንተወው። በቅርብ የኋልዮሽ፣ በአንደኛው አምዳችን ውስጥ የህይወት ዘመን ተሸላሚዋን ፍቅርተ ደሳለኝ፣ የሄርሜላዋን አዜብ ከበደንና የአርአያ ሰብ ከያኒውን ይገረም ደጀኔን አንስተናል።
አሁን ለትውስታ ይሁነንና በ10ኛው ጉማ ከእጩነት ወደ ሽልማት ገበታ ቀርበው የተመገቡ ቀሪዎቹ እንዲህ ተከታትለዋል…በምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ወንድ ተዋናይ ዘርፍ ጉማን ያጠለቀው አንጋፋው አርቲስት አበበ ባልቻ ሲሆን የታጨው ደግሞ “በህግ አምላክ” በተሰኘው ተከታታይ ድራማ ነበር።
በወንድ ካሉ ቀጥሎ በሴትም አለና በዚህ ደግሞ መዓዛ ታከለ ከ“አፉፋ” ድራማ ነበረች። በፊልሙ ኢንዱስትሪ፣ በድራማው ዘዋሪ ምርጥ ምርጦቹ ተብለው በምርጥ ዋና ወንድ ተዋናይ ሙላለም ታከለ ከ”ገምዛ” ፊልም፣ በምርጥ ዋና ሴት ተዋናይት ደግሞ ቃልኪዳን ጥበቡ በ”ልባም ሴት” ተመርጠዋል።
በምርጥ ረዳት ወንድና ሴት ተዋናያን ቴዎድሮስ ተሾመ ከ”ዝምታዬ” እና ድርብወርቅ ሰይፉ ከ”ዶቃ” ፊልሞች፤ ደረጃ ሁለትን በበላይነት አጠናቀዋል። ነገን ለዋናው ተስፋ ያደርጋሉ። እነርሱ እያደረጉም በአመቱ ምርጡ ተስፋ የተጣለባት ተዋናይት መቅደላዊት ግርማ ከ”ሌባ እና ሌባ” እንዲሁም በወንዶች በረከት ግዛው ከ”ጭረት” ፊልም ሆነዋል።
እነዚህን ሁሉ ከፊት ኋላ በሚገራውና የአንድ ፊልም አስኳል በሆነው ዳይሬክቲንግ፤ ቅድስት ይልማ ከ”ዶቃ” ፊልም የዓመቱ ምርጥ ዳይሬክተር ተብላ ክብረ ሽልማቷን ተቀብላለች፡፡
ከተዋንያን ወደ ትወና መንደር፣ ከባለሙያው ወደ ሙያው ስንዘልቅ አንዱ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ነው። ምርጥ ታሪክ፣ ምርጥ ጭብጥ፣ ቆንጆ ምስል፣ ከቆንጆ ድምጽና በሌላም በሌላም የዓመቱ አሸናፊ፤ በዳንኤል ግርማ እና ኑር አክመል ተዘጋጅቶ የተሠራው “እንደ አንድ” ድራማ ነበር።
ከፊልምና ድራማዎች ውስጥ የድምጽ ዉበት አንደኛው ወሳኝ አላባዊ ነውና አበበ አሰፋ እና ቢኒያም ሰለሞን ከ”ዶቃ” ፊልም ተመርጠው ተሸልመዋል። ከድምጹ ኋላና ፊት፣ ከምስሉ በስተጀርባ ምን ሊኖር ይችላል ካሉ አንድም ማጀቢያ ሙዚቃ ነው። ሙላለም ታከለ እና ዘቢባ ግርማ “ወዳጅ” በተሰኘው ፊልም ውስጥ ባስደመጡት ጥኡም ዜማ፤ በምርጥ የፊልም ሙዚቃ ዘርፍ ነግሠዋል። “በምርጥ የፊልም ጽሁፍ” የሚለው ሽልማትም ወደ ዶቃ ፊልም ሄዷል።
ቅድስት ይልማ እና ቤዛ ኃይሉ አሸናፊዎቹ ሆነዋል። በሲኒማቶግራፊው ብስራት ጌታቸው እና ሰዳኪያል አየለ ከፍ ብለዋል። ዶቃ በሜካፑም አልቀረውምና ዳግማዊ አለማየሁ ልቆበታል። በምርጥ የፊልም ስኮር ኢዩኤል መንግስቱ፣ በምርጥ የፊልም ቅንብር(ኤዲቲንግ) ነብዩ ሰኢድ እና ልዑል አባዲ አሁንም ከዶቃ ነበሩ። ዓመተ ዶቃ…በስተመጨረሻም ራሱ “ዶቃ” የአመቱ ምርጥ ፊልም ሆኖ ሮኬቱን አፈነዳው! ጉማም እንዲህ ሲለን እንዲሁ አመሸ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም