ከልጅነት እስከ እውቀት ሀገር ለመበተን ሲያሴር የነበረን ጠላት ስትታገል የኖረች ሴት ናት። እድሜ ባፈዘዘው አይኗ፣ እንባና ሳግ ባነቀው ድምጽ ህወሓት የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው ለማለት ከደፈሩት ከቀዳሚዎቹ አንዷ ነች፤ በፊትም ዛሬም። ተወልዳ ባደገችባት መቀሌ እንደ ባእድ ስትታይ መኖሯ፤ በእርሷ የተነሳ የሌሎች ስቃይ መብዛት የሚያሳስባት ይህች ሴት ወገን፣ ዘመድ ሳትፈልግ ኢትዮጵያን ሊገነጣጥል ሊከፋፍል ያሰበ የትግራይም ሆነ የመላው ኢትዮጵያ ጠላት ነውና በቃህ ልንለው ይገባል ትለናለች።
ተጋይ መሰሉ ረዳ ትባላለች፤ ተወልዳ ያደገችው በሰሜናዊቷ ኮኮብ መቀሌ ነው። እድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰ ገረብ ፀዱ የሚባል ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን፤ ከዛ በከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ ትምህርት ቤት፤ በመቀጠል አፄ ዮሃንስ ትምህርት ቤት ቆይታ ካደረገች በኋላ የአጎቷ ብቸኛ ሴት ልጅ ስትሞትባቸው መፅናኛ ትሆናቸው ዘንድ መሰሉን ወደ አጎቷ የሸኙት ወላጆቿ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በኮረም እንድታጠናቅቅ አደረጓት።
በኮረም የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና ወስዳ ውጤት ብታመጣም በደርግ ሰርኣት “ተሳትፎ ያደረገ” በሚል ተለይቶ መሰሉ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሳትደርስ ትቀራለች። የመማር እድል ማጣት እንጂ የእውቀት ችግር የሌለባት ወይዘሮ መሰሉ በተለያዩ ተቋማት ተወዳድራ በመቀጠር መስራቷን ታስታውሳለች፤ ከሰራችባቸው ተቋማት መካከል ቀይ መስቀልና ወርልድ ቪዥን ተጠቃሽ ናቸው። ምንም እንኳን ሰርታ ማደር ብትችልም የትምህርቷ ነገር የሚያንገበግባት ወይዘሮ በማኔጅመንት ዲፕሎማ ለመያዝ ችላለች።
የደርግን ግፍ ከኢትዮጵያ ላይ ለማንሳት ከሚታገሉ ወጣቶች ጋር ኢዲዩ በሚባል ጥምረት ትግል እያደረገች የነበረችው ወጣት ህወሓት ሀገሪቱን ሲቆጣጠር፤ ከነፃነትም በኋላ ሀገር የመከፋፈል አላማ እንዳለው ስትገነዘብ እንደገና እነሱን ለመታገል ከብሄርተኝነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነት እንዲበልጥ ማንም ሰሚ በሌለበት ለብቻዋ እንደቁራ ትጮህ እንደነበር ታስታውሳለች። ትምህርቷን የማሻሻል ፍላጎት ቢኖራትም የተሻለ ትምህርት ለመማር ከህወሓት ጋር በነበራት ቅራኔ እድሉን ማግኘት አልቻለችም ነበር።
̋ከወጣትነት እስከ እርጅና ስታገል ነው የኖርኩት፤ በአዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥም ነበርኩ” የምትለው ታጋይ መሰሉ ̋በነሱ ሸፍጥ ምክንያት ወዳጅ ዘመድ አጥቼ ኑሮዬን አዲስ አበባ ባደርግም የቀበሌ መታወቂያ እንኳን ዶክተር አብይ አህመድ ከመጣ በኋላ ነው ያገኘሁት” ትላለች።
በእያንዳንዱ ወረዳ “መታወቂያ እንዳይሰጣት” በሚል ስሟ ተላልፎ እንደነበር የምትናገረው ወይዘሮ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የኮንዶሚኒየም ቤት እንኳን እንዳትመዘገብ አድርገዋት እንደነበር ትናገራለች።
ሁልጊዜ የትግራይ ተወላጅ ኢትዮዽያዊት ነኝ በሚል ንግግሯ የምትታወቀው ታጋይዋ ኢትዮዽያ የበርካታ ቋንቋዎች ባለቤት፤ የብዙ መልኮች ድብልቅ፤ የነብር ቆዳ እንደሚያምረው ልዩነታችን ተዥጎርጉሮ የሚያስከብረን፤ እኛ ከሰማንያ በላይ ብሄሮች በአንድ ላይ ተቃቅፎ ተከባበሮ የሚኖርባት ሀገር የኢትዮጵያ ልጆች ነን ትላለች።
እንዲያውም በኛ ጊዜ ኢትዮጵያ የባህር በር የነበራት ከልጅነቴ ጀምሮ አስራ አራት ከፍለ ሀገራት የሚጠቀሙበት አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ የነበራት ውብ ሀገር ልጅ ነኝ። ሰሜን የእያንዳንዱ ጦርነት መምጫ፤ ወራሪ ከውጭ ሲመጣ የሚያልፍባት መስመር በመሆኗ የሀገር በር እንደሆነች ይታሰባል። ይህችን በር እንደጋሻ መጠቀም ሲቻል፤ ሁሉም በኢትዮጵያዊ አንድነት ሲቆምና የሀገር ጥቅም ላይ ላለመደራደር ልዩነትን አጥፍ አብሮ ሲቆም ነው አንድ የሚሆነው የምትለው ተጋይ መሰሉ ህወሓት የመገንጠል ሀሳብ ይዞ ሲመጣ ከእኔ እምነት ጋር የማይስማማ በመሆኑ ሀሳቡን ተቀብሎ አብሮ መጓዝ ከብዶኝ ነበር።
በደርግ ስርአት ኢትዮጵያዊ አንድነት ቢያዝም በግልፅ ጭቆናዎች በማድረሱ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ዳር እስከዳር ታገሉት። ህወሓት ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የነበረውን የነፃነት ጥያቄ በራሱ አጀንዳ ቀይሮ ኤርትራን የማስገንጠል፣ ኢትዮዽያን እንደሚመቸው አድርጎ የመከፋፈል ስራ ሰርቷል። አንድ ሀገር ሲገነጠል እንዴት የባህር በር ሳይኖራት ሊሆን ይችላል በሚል ተቃወምኩ። እንደቀላል ነገር የሀገሪቱን ጥቅም ባላገናዘበ መልኩ አንድ ቤት እንኳን ሲካፈል መውጫ ቀርቶለት ነው፤ እነሱ ግን ድፍንፍን አድርገው ሀገሪቷን ከፍለው አስቀመጧት። ይህን ማድረጋቸው አሳዝኖኝ ከ1982 አ.ም ጀምሮ ከነሱ ወጥቼ ትግል ጀመርኩ።
ሀገር የመገንጠል ጥያቄ የህዝቡ አልነበረም፤ ህወሓት ለራሱ የሚመቸውን አጀንዳ ከፋፍለህ ግዛ ስለነበር መጀመሪያ የሀገሪቱን አንገት ቆረጠ፤ ከዛ ደግሞ ውስጡን በመከፋፈል ለራሱ እንደሚመቸው አድርጎ ህዝቡ ያለውን አንድነት አጥቶ፤ ያ ይከባበር፣ ይዋደድ፣ ይተሳሰብ የነበረው ህዝብ በጎሪጥ እንዲተያይ አደረገ። የአንድነት መንፈሱን አጥፍቶ እርስ በእርስ በአይነ ቁራኛ እንዲተያይ መደረጉ ደግሞ አሁን ላለውና ለተጋረጠብን አደጋ መነሻ ነው። ያም አልበቃ ብሎ ለዘመናት የራሱና የተወሰኑ ቡድኖችን ጥቅም ያስጠበቀ፤ ሌላውን ሲያጠፋ የኖረ ነበር። በዚህም አልበቃውም፤ አሁንም እኔ ካልገዛሁ ሀገር ትፍረስ በሚል እሳቤ የሽብር ስራዎችን እየሰራ ነው።
በ1995 አ.ም የመኢኣድ አባል በመሆን ትግሏን በሰላማዊ መንገድ የቀጠለችው ታጋይ መሰሉ ከዛ ደግሞ በ1997 አ.ም መኢኣድን በመወከል በትግራይ ላይ ተወዳድራም ነበር። በ2002 አ.ም በድጋሚ እንዳትወዳደር፣ ከአካባቢው (ትግራይ) ጥላ እንድትጠፋ፣ ሰው በማደራጀት፣ በመሳደብ፤ ከማህበረሰቡ እንድትገለል በማድረግ የተለያዩ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጥቃቶችን ሲያደርሱባት ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት ሁኔታዎች እየከበዷት ሲመጡ አዲስ አበባ መጥታ መወዳደር ጀመረች።
እነዚህ የክፋት ሀይሎች የጠሉትን ቀብረው እስኪያዩት ድረስ አርፈው የማይተኙ ናቸውና በብዙዎች የመኢኣድ ፓርቲ አባላት በኩል በጥርጣሬ እንድትታይ ሁሉ አድርገዋታል። ብዘዎች ህወሓትነትና ትግሬነትን በአንድ በመመልከታቸው የተነሳ “ኢትዮጵያዊነትን መርጣ እየታገለች እንኳን አሁን በምርጫ ብታሸንፍ አሳልፋ አትሰጠንም ወይ?” በሚል የሚጠራጠሩ የፓርቲው አባላት እንደነበሩ፤ ሁሉንም አይነት ጥቃቶች ተቋቁማ ለማለፍ ግን ጫንቃዋን ያደነደነች ሴት እንደነበረች ትናገራለች። ̋እኔ ግን ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚበልጥብኝ ሰው አይደለሁም። እንደዛ አይነት አስተሳሰብ የለኝም። በምንም አልገዛም። ‘ስለሀገር አንድነት ከኔ በላይ የሚመለከተው የለም’ በሚል ህሊናዬን አሳምኜ እየኖኩ ነው።” ትላለች።
በጣም የሚያሳዝነው የክፋት ዘራቸው በቅሎና አፍርቶ አሁን ላይ ኢትዮጵያዊ ከሚለው ስም በፊት እኔ ትግሬ ነኝ፤ አማራ ነኝ፤ ኦሮሞ ነኝ የሚለው ስም ይቀድማል። የዘሩት የክፋት ዘር ሀገራችንን እየከፋፈለ ይገኛል። የትግራይ ህዝብ የነበረውን ፈርሀ እግዚአብሔር፤ ቅንነቱን ሊያሳጡት አዲሱ ትውልድ ላይ ክፉ መንፈስን፣ አረመኔነትን የሚዘሩ፤ ጓደኞቻቸውን በመግደል ደም የለመዱ፤ በደም የሰከሩ፤ ሀገርን በእጃቸው የሰሩት ይመስል ሊከፍሉ፣ ሊያፈርሱ መነሳታቸው እነሱ ካልጠፉ በቀር ሰላም የማይሰጡ መሆኑን ያሳያል።
እነሱ እኮ የአከባቢያቸው ተወላጅ ለሆኑት እንኳን ያላዘኑ ሰው ናቸው። ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን የተማረውን የትግራይ ህዝብ አይፈለጉትም። አንድ እንሁን ያሉትን ቤት ውስጥ ቆልፈው ህድሞው እንዲናድበት ያደረጉ፤ ከነሱ ጎን ያልቆመውን ቆራርጠው የሚገሉ፤ ድክመታቸውን የማይቀበሉ፤ የሌሎችን ሀሳብ የሚያጣጥሉ፤ በወረቀት የሚያወሩትን የማያደርጉ፤ ህዝብን እያሳዘኑ፣ እያስለቀሱ የሚኖሩበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው የምትለው ታጋይ መሰሉ ይህንን ክፋት ደግሞ መላው ኢትዮጵያዊ በቃ ሊለው እንደሚገባ ትናገራለች።
ከሁሉም የማስታውሰው የ2002ቱን ምርጫ ለመወዳደር ምቹ እንዲሆን በሚል የመኢኣድን ቢሮ ትግራይ ላይ መክፈት ግድ ሆነና ለመክፈት ሲታሰብ የህወሓት ፅህፈት ቤት ከሚገኝበት ሰማእታት ሀውልት ፊትለፊት (መቀሌ ማለት ነው)፤ ደብረዳሞ ሆቴል አጠገብ ባለ አንድ ህንፃ ውስጥ ቢሮ በመክፈት እነሱን ለመቃወም በቅርበት መቆም የሚቻል መሆኑን ለማሳየት ሙከራ አድርጋ እንደነበረ የምትናገረው ታጋይ መሰሉ በወቅቱ ግን በር ላይ ጫማ የሚያስጠርጉ መስለው በመኢኣድ ቢሮ መጥተው አባል የሆኑትን እያሳደዱ ያጠቁ ነበር። ከውስጥ ደግሞ ሰላዮችን በማሰማራት በትግራይ ምድር ከህወሓት ሌላ ማንም መወዳደር እንደማይችል ለማሳየት ይሞክሩ እንደነበርም ትናገራለች።
ህብረተሰቡ ለውጥ ቢፈልግም ማስፈራሪያው ጭቆናው ስለበዛ ሲቀር ይታያል። በጣም የሚገርመው በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አባላቱ በጥርጣሬ እንዲመለከቱ የማድረግ ስራ ይሰራል። ሰውን ከጠሉት እስከመቀበሪያ የመከተል ተስፋ የማስቆረጥ ድጋፍ የማሰጣት ስራ ይሰራሉ። ደርግ ቢወድቅም የትግራይ ህዝብ ዘመኑን ሙሉ ከጭቆና አልተላቀቀም ነበር።
ቤተሰቦቻችን መሬታቸው እየተወሰደባቸው፤ እነሱን የማይደግፈው እየተገደለ እየተሳደደ ነው የኖረው። ሰው ድጋፍ ቢያደርግም በነገታው እነሱ በሚሰሩት የክፋት ስራ ምክንያት ድጋፉን ለእኛ ይሰጠን ነበር። የሚገርመው ማዳበሪያ ባለመስጠት፤ ስራ እንዳያገኝ በማድረግ፣ የህክምና ድጋፍ ሳይቀር ይከለክሉ ነበር።
ህውሓቶች እንደሚሉት ፓርቲያቸው የትግራይን ህዝብ እንደሚወክል ነው። አንድ ሰው ግን የአንድ ፓርቲ አባል ነው ለማለት መመዝግብ አለበት። ህዘቡ አባል ነኝ ሳይል ትግራይ በሙሉ ህውሓት ነው ማለት ጭፍለቃ ነው። የትግራይ ህዝብን በስነልነቦና አፍነውት መግቢያ መውጫ አሳጥተው ለነሱ ምቹ መደላደል አድርገው ሰርተውት ውስጡ ተሸጉጠው እየፈጁት ነው።
የትግራይ ህዝብ ሀገሬ ብሎ በመላው ኢትዮጵያ የሚኖር ህዝብ ነው። በኤርትራውያን የደረሰ በትግራይ ህዝብ እንዲደርስ ነው የሚፈልጉት። ይህን በደም የተሳሰረ ህዝብ ለመበተን ቤት ለማፍረስ አብሮ እንዳይኖር ለማድረግ ነው ያሰቡት፤ እነሱ ስልጣን ከተመቻቸው ማንም ሰው ቢሞት ግድ የላቸውም ትላለች።
በጊዜያዊ አስተዳደር ጊዜም ወጣቱን በሙሉ በፕሮፖጋንዳ አሳብደው ልጆቹ በተመዘገቡበት ቀን በዛው እየወሰዷቸው ነበር። እናት በልጇ የማታዝበት ጊዜ ላይ ደርሳለች። ልጆቹንም በጭፍን ጥላቻ ሞልተዋቸው ወላጆቻቸውን የማይታዘዙ ሆነዋል። በተረፈ በእርዳታ እህልና በሌሎች ማስፈራሪያዎች እናት አርግዛ፣ አምጣ፣ ወልዳ በመከራ ያሳደገችውን ልጇን ከጉያዋ እየነጠቁ ለእሳት ማግደዋል። ይህን እኩይ ፍጥረት ለማስወገድ ደግሞ የሁሉም የጋራ ህብረት ይጠይቃል ትላለች።
በጥባጭ ካለ ማንም ንፁህ ውሀ አይጠጣምና በጥባጩን አስወግደን በሰላም የምንኖርበት ቀን ያምጣልን እያልን የዛሬውን በዚሁ አበቃን።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም