በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ ከጎዳቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ ቱሪዝም ነው። በተለይ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ በርካታ ሀገራት ድምበራቸውን በመዝጋታቸውና የእንቅስቃሴ ገደቦች በመደረጋቸው በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ከጎብኚዎች ርቀው ቆይተዋል፡፡ በዚህም በተለይ በዋናነት በዚህ ዘርፍ ላይ ኢኮኖሚያቸው የተንጠለጠለ ሀገራት ከፍተኛ ኪሳራ አጋጥሟቸዋል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መምጣትና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መልኩን እየለዋወጠ መከሰቱ አስገዳጅ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲኖሩ በማስገደዱ ከድጡ ወደማጡ እንዲሉ የቱሪዝም ዘርፉ ይበልጥ ላሽቋል፡፡ የክትባት መምጣት የሰዎችን የእንቅስቃሴ ገደብ እንደሚያላላ ተስፋ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም ስርጭቱ የታሰበውን ያህል ባለመሆኑ የቱሪዝም ዘርፉ ከመነቃቃት ይልቅ መፋዘዙ ይታያል፡፡
በዚህ ሁሉ ፈተና ታዲያ አንዳንድ ትላልቅ የቱሪስት መዳረሻ ያላቸው ሀገራት ኮቪድን ታሳቢ ያደረገ የቱሪዝም ስትራቴጂ በመቀየስና አዳዲስ መንገዶችን በመከተል ዘርፉን ለማነቃቃት ጥረት እያደረጉ ነው። በበርካታ የቱሪስት መዳረሻዎቿ የምትታወቀው ታይላንድ በወረርሽኙ ጦስ የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፏን ለማሻሻል በቅርቡ የጀመረችው አዲስ ስትራቴጂም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ሀገሪቱ ቀደም ሲል በገፍ ከሚገቡ ቱሪስቶች የምታገኘውን ገቢ በመተው በቁጥር የተገደቡ፣ ክትባት የወሰዱና ገንዘባቸውን በብዙ ለማውጣት ዝግጁ በሆኑ ቱሪስቶች ላይ አተኩራለች ፡፡ ለዚህም የተለያዩ ፓኬጆችን አዘጋጅታለች፡፡
ኢትዮጵያም ከሌሎች ዘርፎች ባልተናነሰ መልኩ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ ቱሪዝም ቢሆንም ልክ እንደሌላው ዓለም ሁሉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የቱሪስት ፍሰቱን ገቶታል፤ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም ቀንሷል፡፡ ከዚህ ባልተናነሰም በሰሜኑ ክፍል የተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻም ቱሪዝሙን አስተጓጉሏል፡፡ የአሁኑ የህልውና ዘመቻ ደግሞ ዘርፉን ይበልጥ አዳክሞታል።
የህግ ማስከበር ዘመቻው እንደተጀመረ አሸባሪው ህወሓት በመከላከያ ሰራዊት ሲመታ መሸሸጊያውን በገዳማት፣ በታሪካዊ መስጂዶችና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በማድረጉ በእነዚህ ቅርሶች ላይ ጉዳት ደርሷል። አንዳዶቹም ወድመዋል፡፡ ይህም በቀጣይ የቱሪዝም ዘርፉ እየተነቃቃ ሲመጣ ከዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ሀገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ እንዳያሳጣ ከወዲሁ ስጋትን ጭሯል፡፡
መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም አድርጎ ከመቀሌ ከወጣም በኋላ ቡድኑ በአፋርና በአማራ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ላይ ዘልቆ በመግባትና ትንኮሳ በመፈፀም መጠነ ሰፊ ጉዳት ። በተለይ ደግሞ ቡድኑ ወደ አማራ ክልል ዘልቆ በገባበት በላሊበላ የሚገኘውንና በዩኔስኮ መዝገብ ውስጥ የሰፈረውን የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ገዳም አደጋ ውስጥ ከቷል፡፡ የጨጨሆ መድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን ላይም ከባድ መሳሪያ በመተኮስ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
በነዚህ ፈተናዎች ሁሉ አልፎ እዚህ የደረሰው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ የ2013 በጀት ዓመት የሴክተር ዕቅድ አፈፃፀም ጉባኤውን ከሰሞኑ አካሂዷል። በጉባኤው መክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ባለፈው አንድ ዓመት የቱሪዝም ዘርፉ አንድም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁለትም በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ባንዳዎች ከውጭ ጠላቶች ጋር አብረው ጦርነት በመክፈታቸው ተቀዛቅዞ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና በዚህ በጀት ዓመት በፈተና ውስጥም ሆኖ ታላላቅ ስራዎች የተከናወኑበት እንደነበርም ጠቅሰዋል። የበጀት ዓመቱ የአስር ዓመት የልማት እቅድ መነሻ ዓመት እንደመሆኑ ለቀጣይ አፈፃፀም ማነቆ እንዳይሆኑ በማሰብ በርካታ የህግ ማእቀፎች እንዲዘጋጁ፣ፖሊሲዎች እንዲከለሱና አሰራሮች እንዲዘረጉ መደረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በተለይ የአድዋ 125ኛ ዓመት ክብረ በአልና የኢትዮጵያ ሳምንትን የመሳሰሉ ታላላቅ ሁነቶች እንደሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር የተቻለባቸው እንደነበሩም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
የ2014 በጀት ዓመት እቅድም በልዩ ልዩ ምክንያት በ2013 በጀት ዘመን ያልተከናወኑ ተግባራትን በማካተት፤ በአስር ዓመት አቅዱ በ2014 እንዲከናወኑ የተያዙ ተግባራትን እንዲሁም ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታንና መጪውን ጊዜ ታሳቢ ያደረጉ አንኳርና ወቅታዊ ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ የታቀዱ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
እቅዱ አሁንም በኮቪድ-19 ተፅእኖ ስር ሆኖና ከባንዳዎች ጋር በመፋለም የሚከናወን በመሆኑ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ለመተገበር የሁሉንም ዝግጅት የሚጠይቅ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ክልልሎችና የፌዴራል ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እጅ ለእጅ በመያያዝ ተናበው መስራት ከቻሉ በዘርፉ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዘገብ እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ስፖርት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲያትር፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተመፃህፍት ኤጀንሲ፣ የሆቴልና ቱሪስት አገልግሎት ስልጣና ተቋምና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ናቸው። የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ተቋምና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ደግሞ በስራ አማካኝነት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ይገናኛሉ፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የ2013 በጀት ዓመት የቱሪዝም ዘርፍ እቅድ አፈፃፀም በአንድም ሆነ በሌላም እነዚህን ተቋማት ማእከል ያደረገ ነው፡፡ የእቅድ አፈፃፀሙ የሁሉም ክልሎች የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፍ አጠቃላይ ቢሮዎችን እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ ጽህፈት ቤቶችንም ይመለከታል፡፡
ከ2013 እስከ 2022 ድረስ የሚቆይ የአስር ዓመት መሪ እቅድም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያዘጋጀ ሲሆን ከዚሁ መሪ እቅድ የተቀዳና ከ2013 እስከ 2017 ድረስ የሚቆይ የአምስት ዓመት እቅድም አዘጋጅቷል፡፡በዚሁ መሰረትም በ2013 በጀት ዓመት በተለይ ከንቅናቄ አንፃር በሀገር አቀፍ ደረጃ 125ኛው የአድዋ በአልን በሚመለከት በክልል፣ በፌዴራልና በሀገር አቀፍ እንዲሁም በእያንዳንዱ ወረዳ ደረጃ ብሎም በውጭ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በተለየ ሁኔታ በድምቀት እንዲከበር ተደርጓል፡፡ ይህም ከዚህ በፊት ከአንድነት ይልቅ ወደብሄርተኝነት ያተኮረውን የበዓል አከባበር እንዲቀየር አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በንቅናቄ በኩል የተሰራው ትልቁ ስራ የኢትዮጵያ ሳምንት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ የወዳጅነት አደባባይ ሁሉም ክልሎች ያላቸውን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ፀጋቸውን ብሎም የኢንቨስትመንት አማራጫቸውን አሳይተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር የተዋወቁበትና ሁነቱ ለስምንት ቀናት ያህል ቆይቶ ከሰላሳ ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ጎብኝተውታል፡፡
በዚህ ሁነትም የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ቀርበዋል፡፡ በአንድ ቦታና በአንድ ማእቀፍ የባህል ገጽታዎችና የቱሪዝም መዳረሻዎችም ለመታየት ችለዋል። ይህም ስራ የተከናወነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ከሴቶችና ህፃናት ሚኒስቴር እንዲሁም ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ነው፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በበጀት ዓመቱ ከቅርስ ጥገና አንፃርም የተጀመሩ በርካታ ሥራዎች ነበሩ፡፡ በተለይ ደግሞ የጥያ ትክል ድንጋይ ቱሪስት መዳረሻ በራስ ባለሙያ ጥገና ተደርጎለት ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ተደርጓል። በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ የጥገና ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ኮቪድን ታሳቢ ያደረጉና በቀጣይ ማነቆዎች እንዳያስቸግሩ የህግ ማእቀፎች እንዲዘጋጁ፣ ፖሊሲዎች እንዲከለሱና አሰራሮችም እንዲዘረጉ ተደርገዋል፡፡
ከቋንቋም አኳያም ቀደም ብሎ በ2012 የጸደቀውን የቋንቋ ፖሊሲ ወደመሬት ለማውረድ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከስፖርትም አንፃር ተመሳሳይ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ግንባታን በሚመለከት የካፒታል ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ የሚገኙ ሲሆን የብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት ኤጀንሲ ባለአስራ ሶስት ወለል ህንፃ ግንባታ የማጠናቀቂያ ስራ ላይ ይገኛል፡፡
ቦሌ ገርጂ አካባቢ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው የአደይ አበባ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታም በሁለተኛ የግንባታ ምእራፍ ላይ ይገኛል፡፡ በክልሎችም የተጀመሩ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታም እየተከናወነ ነው፡፡ በስፖርት ግብይት ላይ የግል ተቋማት እንዲሳተፉና ስፖርት እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግልም ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ኮቪድ-19 የሀገር ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም በከፍተኛ ደረጃ ዘርፉን አደብዝዞታል። በርካታ ሀገራትም ቱሪስቶች እንዳይገቡባቸው በራቸውን ዘግተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የእንቅስቃሴ ገደብም በራሱ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል፡፡ በሰሜኑ ክፍል እየተደረገ ያለውም የህልውና ዘመቻም በተመሳሳይ ቱሪዝሙ እንዲቀዛቀዝ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
ይሁንና ፎርብስ መፅሄት ባወጣው መረጃ መሰረት ከኮቪድ-19 በኋላ ኢትዮጵያ ተጎብኚ ሊሆኑ ከሚችሉ ሀገራት መካከል አንዷ እንደምትሆን አስቀምጧል። ነገር ግን ወቅቱ የኮቪድ ወረርሽኝ ሶስተኛ ማእበል ያለበት በመሆኑ በቅድሚያ ከዚህ ወረርሽኝ መውጣትን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንፃር የቱሪዝም ሴክተሩ ምን ያህል ተዳክሟል የሚለውን ሙሉ በሙሉ ለመወሰን ቀጣዩ ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ምን ሊሆን እንደሚችል ማጤን ይገባል፡፡
በቀጣይም ከቱሪዝም አንፃር በርካታ ተጨማሪ የመዳረሻ ቦታዎችን የማየትና የማስፋፋት ስራዎችም ይከናወናሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ የቱሪዝም ዘርፉ መቀዛቀዝ ብቻ ሳይሆን የኮቪድን ችግር እንደ በጎ አጋጣሚ የመጠቀም ሁኔታም እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ የሆስፒታሊቲ እና የመስተንግዶው ኢንዱስትሪ አካባቢ ያለው የስራ መቀዛቀዝም ወደ ተለየ አማራጭ አምጥቶታል፡፡ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ያለውን አማራጭ እንዴት እንጠቀምና በዚህ ሁኔታ የሰው ሃይሉን እንዴት ማሰማራት ይቻላል በሚል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስቀድሞ የኮቪድ መስተንግዶ መመሪያ አውጥቷል። ከባህል ዘርፍም የወጣ መመሪያ አለ፡፡ ይህንንም ባገናዘበ መልኩ መመሪያዎችን በማስረፅ፤ እንዲህ አይነት ቀውሶችና ወረርሽኞች ሲያጋጥሙ እንደ መልካም ተሞክሮ በመቁጠር በርካታ ስልጠናዎችም ተሰጥተዋል፡፡
ስልጠና ብቻ ሳይሆን በየሆቴሎችም ጭምር በመዞር በተሰጠው መመሪያና በፀደቀው ደምብ መሰረት በምን ያህል ደረጃ የኮቪድን ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ የመስተንግዶ ሁኔታ እየተካሄደ እንደነበርም በባለሙያዎች ክትትል ለማድረግም ጥረት ተደርጓል።ለዚህም በተለይ ይህንኑ መመሪያና ደምብ በተከተለ መልኩ ለፈፀሙ ሆቴሎች የማበረታቻ ሰርተፍኬት እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡
ወደፊትም የቱሪስት መዳረሻ ሀገራት የኮቪድ- 19 ፕሮቶኮልን የተከተሉ ናቸው የሚል ጥያቄ የሚቀርብላቸው በመሆኑና ለዚህም ማረጋገጫም ጭምር የሚሰጥ ስለሆነ በመስተንግዶው ዘርፍ በሚኒስቴሩ በኩል የተጀመረው ስራ የሚመጣውን ጥያቄ ከወዲሁ ለመመለስ ይረዳል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም