ዛሬ የአዛውንቱ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የእድሜ እኩያ የሆኑ እንግዳ ይዘን ቀርበናል፡፡ እንግዳችን ብርጋዴል ጀነራል ዋስይሁን ንጋቱ ይባላሉ፡፡ ከጉርምስና እስከ ጎልማሳነት እድሜያቸው ድረስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን ለ30 ዓመታት ያህል በተለያዩ ግንባሮች ላይ ተሳትፈው አገራቸውን ከጥቃት ታድገዋል፡፡ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና በደርግ ዘመን የጦር ሰራዊት አባል፣ የጦር መሪ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን እና ታንከኛም ነበሩ፡፡ በዚህ ቆይታቸውም ከምክትል መቶ አለቅነት እስከ ጀነራል ድረስ የሚደርሱ ማዕረጎችን ተቀዳጅተዋል፡፡
በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር የቀድሞ ሰራዊት ውስጥ በተለያዩ የጦር ግንባሮችና የጦር ክፍሎች ሀገራቸውን በወታደራዊ ግዳጅ ውስጥ ተሳትፈው በብቃትና በትጋት ለመወጣት የቻሉ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን በመሆናቸው ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ላደረጉት ውለታ ከፍተኛውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የጦር ሜዳ የጀግና ሜዳይ ባለዘንባባ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ተቀብለዋል፡፡ እናም እኝህን የአገር ባለውለታ ለዛሬ በ«ህይወት ገጽታ»አምድ የህይወት ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩን እንግዳችን አድርገናቸዋልና ተጋበዙልን፡፡
አርበኛው የአርበኛው ልጅ
ነሐሴ 16 ቀን 1933 ዓ.ም ለቤተሰቡ ስድስተኛ ልጅ የሆኑት እንግዳችን የተወለዱበት እለት ነው፡፡ ቦታው በቀድሞው ወለጋ ጠቅላይ ግዛት በጉዱሩ አውራጃ በሎያ ጨመን በወሶ ሶቂ የገጠር መንደር ውስጥ ሲሆን፤ በሁለት ቤተሰብ መካከል የተወለዱ ናቸው፡፡ አባታቸው ጥሩ ሰራተኛ በመሆናቸው ሁለቱንም ቤተሰብ በእኩል ያስተዳድራሉ፡፡ ስለዚህም እንግዳችን የተወለዱበት ቤትም እንዳይጎድልና ደስታና ፈንጠዝያው እንዲበዛ ያላደረጉት ነገር የለም፡፡ እንደውም ትልቅ እስኪሆኑ ድረስ እንክብካቤያቸው ልዩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ልጆቻቸውን የሚወዱ አባት ስላሏቸውም እርሳቸውን ለመምሰል የማያደርጉት ነገር አልነበረም። ከእነዚህ መካከል አንዱ አርበኝነት ሲሆን፤ አባት በጣሊያን ጊዜ የዘመቱና ድልን ለአገር ካቀናጁት ውስጥ በመሆናቸው አርበኛ መሆን የልጅነት ህልማቸው ነበር። ለዛሬ ማንነታቸውም ያበቃቸው ይህ ፍቅራቸው እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ ከአባታቸው በተጨማሪ ወንድማቸውም የእርሳቸውን የልጅነት ፍላጎት ገንብቶት ነበር፡፡
እንግዳችን በባህሪያቸው ታዛዥና በስነምግባር ተኮትኩተው ያደጉ በመሆናቸው ትምህርትቤት ሳይቀር ከሁሉም ጋር ተዋደውና ተቧድነው ሲጫወቱ የሚውሉት። በእርግጥ ለመማር በቅርብ እርቀት አልቻሉም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከአካባቢያቸው ወጥተው እንኳን ከልጆች ጋር መጣላትን በምንም መልኩ አይሞክሩትም፤ አይወዱምም። ይህ ባህሪያቸው ደግሞ በሰፈርም ሆነ በትምህርትቤት ሁሉም ሰው እንዲወዳቸው አድርጓቸዋል፡፡ በጨዋታ ላይ እንኳን ከእኔ ጋር ይሁን የማይላቸው ልጅ እንዳልነበር ያስታውሳሉ፡፡
ሌላው መለያ ባህሪያቸው ማንበብና ታሪክ መስማት ወዳድነታቸው ነው፡፡ በተለይም የአርበኝነት ታሪክን ለመስማት ሁልጊዜ እንደቋመጡ ናቸው፡፡ ስለዚህም አባታቸውም ሆነ የአባታቸው ጓደኞች የኢትዮጵያን ታሪክ ሰሪነትና ጀብድ ሲናገሩ ፈጥነው ከእግራቸው ስር በመቀመጥ ያዳምጣሉ፡፡ ለትምህርት ወንድማቸው ጋር ሲኖሩ ደግሞ ወንድማቸው ፖሊስ ስለነበር ከእርሱም ብዙ ልምድ ቀስመዋል፡፡ ብዙ ታሪኮችንም ሰምተዋል። ዛሬ በአገር ጉዳይ ላይ ዘምተው ለመዋጋታቸውና ዳር ድንበር ለማስከበራቸውና ‹‹የአርበኛ ልጅ መቼም ቢሆን አገሩን አይጠላም፤ አርበኛ ሆኖ ለአገሩ ይዋደቃል እንጂ›› የሚል እምነት እንዲኖራቸው ያደረገው ምስጢሩ ይህ እንደሆነ አጫውተውናል፡፡
ከሻንቡ እስከ አሜሪካና ራሽያ
እንግዳችን እድሚያቸው ለትምህርት የደረሰ ቢሆንም ቶሎ ትምህርትቤት መግባት አልቻሉም ነበር፡፡ ምክንያቱም በአቅራቢያቸው ትምህርትቤት የለም፡፡ ስለዚህም አባት ልጆቻቸው እንዲማሩላቸው በመፈለጋቸው የተነሳ ራቅ ቢልም በ1940ዎቹ ከታላቅ ወንድማቸው ጋር በማድረግ 10 ኪሎሜትር ርቀው ሄደው በሚገኘው ‹‹ ገረመው ካንፕ›› በሚባል መንደር ውስጥ የቄስ ትምህርት እንዲማሩ ላኳቸው፡፡ በዚህም ባለታሪካችን ከፊደል ጋር ብቻ ሳይሆን ከዚያም አልፈው ዳዊት እስከመድገም የሚያደርስ ትምህርትን እንዲቀስሙ ሆኑ፡፡ ወንድማቸው ግን ፊደላትን ከቻለ በኋላ አካባቢውን ለቆ በይበልጥ መጻፍና ማንበብ ለመቻል ወደ አጎታቸው ዘንድ ጎጃም ሄደ፡፡ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም በነቀምት ፖሊስ ሰራዊት ውስጥ በውትድርና ተቀጠረ። ይህ ሁኔታው ደግሞ ለእንግዳችን ዘመናዊ ትምህርትን ለመማር እድልን አመቻቸላቸው፡፡
በእርግጥ እርሳቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት ወንድማቸው መጀመሪያ ሲሰራበት በነበረው ነቀምቴ ሳይሆን በሥራ ተቀይሮ ወደ ጉዱሩ አውራጃ ሻንቡ ሲገባ ነው፡፡ ስለዚህም የዘመናዊ ትምህርት የጀመሩት በሻንቡ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት የአንደኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ ደግሞ ወንድማቸው ወደ ነቀምቴ ተመልሶ እንዲሰራ በመደረጉ እርሳቸውም አብረውት ሄደው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
ወንድማቸው ሥራውን በገዛ ፈቃዱ አቁሞ ከአካባቢው ራቅ ባለ ቦታ በራሱ ጠበቃ ሆኖ መስራት ሲጀምር ግን የትምህርት ሁኔታቸው አደጋ ተጋርጦበት ነበር፡፡ ሆኖም ሳይደግስ አይጣላ እንዲሉ ደግ ሰው ጣለላቸውና ትምህርታቸውን መከታተል ቻሉ፡፡ እኒህ ሰው በጋብቻ የተዛመዷቸው አቶ ተፈራ ጉርሜሳ የሚባሉ ሲሆኑ፤ በእርሳቸው ቤት ተቀምጠው ከሦስተኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል እንዲማሩ ፈቅደውላቸዋል፡፡ እንደቤተሰብም ሆነው ነው ያስተሟሯቸው፡፡ በዚህም ለህይወቴ መቀየር መሰረት ከጣሉት ቤተሰቤ መካከል አንዱ ናቸው ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጡላቸዋል፡፡
ከስምንተኛ በኋላ ያለው የትምህርት ሁኔታቸው በውትድርናው ላይ ያሳለፉት ሲሆን፤ በአገር ውስጥና በውጪ አገር ብዙ የውትድርና ትምህርቶችን ተከታትለዋል፡፡ በአገር ውስጥ ያለውን ስንመለከት መጀመሪያ ትምህርቱን “ሀ” ብለው የጀመሩት በሆለታ ገነት የጦር ትምህርትቤት ነው፡፡ ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ ወታደር መሆን ለእርሳቸው ክብር እንደሆነ ማመናቸውና ለሌላ ስራ ማፈላለግ እንደመጡ የውትድርና የሚሆን ማስታወቂያ በመከላከያ ሚኒስቴር አማካኝነት ወጥቶ ተመለከቱ፡፡ በዚህም በማስታወቂያው የክቡር ዘበኛ፣ የፖሊስ፣ የአባዲናና የጦር ሰራዊት መኮንን ኮርስ ስልጠና እንደሚሰጥ አዩ፡፡ እናም በቀጥታ ወደ ጦር ጠቅላይ መምሪያ በመሄድ ተመዘገቡ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላም በትምህርት ሚኒስቴርና በምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ ትብብር የወጣውን ፈተና ወስደው ስለነበር ማለፋቸው ተነገራቸው፡፡ በሆለታ ገነት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጦር ትምህርትቤትም ገብተው ትምህርታቸውን ጀመሩ፡፡
‹‹ እጣ ፋንታዬን የሰራሁት ራሴው ነኝ›› የሚሉት እንግዳችን፤ ወታደራዊ ስነልቦናን ከቤተሰባቸው የወረሱት በመሆኑ ሆለታ ገነት ጦር ትምህርትቤት መግባታቸው ይበልጥ አስደስቷቸው ነበር፡፡ ስለዚህም የ21ኛ ኮርስ ዕጩ መኮንን ሆነው ትምህርቱን ሰለጠኑ፡፡ በእርግጥ ሲገቡ ብዙ ፈተና ገጥሟቸዋል። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ በፍጹም አይረሷቸውም፡፡ የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛው ጦርነት የተካሄደበት የታህሳስ ግርግር መነሳት ሲሆን፤ እነርሱን በገቡ በአምስተኛው ቀን በመከሰቱ እድለቢሶቹ ማስባሉ ነው፡፡ ሌላውና ሁለተኛው ትምህርት ሲቆም የቁርስ ዳቦ ተቋረጠ፡፡ ስለዚህም ለቀናት እንዲቸገሩ ሆኑ፡፡ ነገርግን ዓላማ ያለው ተማሪ ትምህርቱን አያቋርጥምና የመንግስት ግልበጣው እስከሚከሽፍ ድረስ ችግሮቹን ተጋፍጠው አሳልፈውታል፡፡
ከግርግሩ ክሽፈት በኋላ ትምህርቱን ሲጀምሩ ግን በእድለኝነታቸው ነው የቀደሱት፡፡ ምክንያቱም ለመኮንኖች የ50 ብር የደሞዝ ጭማሪ ተደረገ፡፡ ሁሉም ደስተኛ ሆነው መማሩ ቀጠሉ፡፡ በጥሩ መምህራንና መሳሪያዎች የወታደራዊ አመራር ሥልጠናውንም ወሰዱ። ተገቢውን ስልጠና ወስደው ካጠናቀቁ በኋላም በ1954 ዓ.ም የምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግን ከእነዲፕሎማው ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ ተቀብለው መመረቅ ቻሉ፡፡ መኮንንም ተባሉ፡፡
ማንም ሰው ቢሆን ዓላማውንና ግቡን በቅጡ ለይቶ ካወቀና ከተጋ የቱንም ያህል ፈተናና ውጣውረድ ቢገጥመው በመጨረሻ ያሰበውን ከማሳካት የሚያግደው አይኖርም ብለው የሚያምኑት ባለታሪካችን፤ በውትድርናው መስክ መማራቸውን ቀጠሉ፡፡ በናዝሪት ምድር ጦር ታንከኛ መምሪያ ውስጥ ገብተው መሰረታዊ የታንከኛን ትምህርትን ለስድስት ወር ያህል ተከታተሉ። በተለይም አራቱን የታንክ ምድቦች ማለትም የታንክ ሹፍርና፣ የታንክ አጉራሽ፣ የታንክ ተኳሽና የታንክ አዛዥ ሥልጠናዎችን አንድ ታንከኛ በሚገባ ማወቅና መውሰድ ነበረበትና እርሳቸውም እነዚህን ጠንቅቀው በማወቅ ለምረቃ በቁ፡፡ በድሬደዋ የኮማንዶና የአየር በረራ ትምህርቶችን ሲማሩም ብቃታቸው በየጊዜው የሚያስመሰግናቸው እንደነበር ያወሳሉ፡፡
ከኦጋዴን ጦርነት በኋላ ደግሞ እንዲሁ ጥሩ ሥራ የሰራ ለትምህርት ይታጭ ነበርና እርሳቸውም አንዱ ነበሩና የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆኑ፡፡ ስለዚህም ዳግም ወደ ሆለታ ገነት የጦር ትምህርትቤት ተመልሰው ትምህርት እንዲቀጥሉ ተደረጉ፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው በእስራኤሎች ቢሆንም የእንግሊዝኛ ትምህርት ችሎታቸው ላቅ ያለ በመሆኑ ምንም አልተቸገሩም። በዚህም አራት አይነት የውጊያ መረጃ ትምህርቶችን ሲማሩ ከፍተኛ ውጤትና ብቃት ያሳዩ እንደነበሩ አይረሱትም፡፡ እንደውም ይህ ውጤታቸውና በተግባር ልምምዱ ያሳዩት ብቃት ለአሜሪካ ትምህርት እስከማሳጨት አድርሷቸዋልም፡፡
በአሜሪካ ሁለት የትምህርት አይነቶችን ተምረው እንዲመጡ የተላኩት ብርጋዴል ጀነራል ዋስይሁን፤ የመጀመሪያው ፎርትኖክስ ኬታንኪ የተማሩት ከፍተኛ የታንክ ትምህርት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ኦክላሃማ ፎርት ሲል የተማሩት የመድፈኛና የታንከኛ የኅብርት ውጊያ ነው፡፡ እነዚህንም ትምህርቶች በጥሩ ብቃትና አቅም እንዳጠናቀቁ ይናገራሉ፡፡ እንደውም ትምህርት በቃኝ ሳይሉ ሦስተኛ ትምህርት ለመማርም ፈቃድ ጠይቀው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም በተማርከው አገልግል፤ ብዙ ይህንን እድል ያላገኘ አለ በመባላቸው ወደአገራቸው እንዲመለሱና ሥራ እንዲጀምሩ ሆነዋል።
በውጭ ሀገር የታንከኛ መሠረታዊ ትምህርት፣ ከፍተኛ የውጊያ መረጃ ትምህርት፣ የአውሮፕላን የአየር ቅኝት ፣ ፀረ-የአየር በረራ ጠለፋ ወዘተ ትምህርቶችን የተማሩት ባለታሪካችን፤ ከአሜሪካ በኋላም ውጪ ሄደው መማርን ያስቡ ነበር፡፡ በአገኙት አጋጣሚም ሁልጊዜ ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ትጋታቸው ደግሞ ወደ ራሺያ ሄደው የሚማሩበትን እድል ሰጣቸው፡፡ በዚህም በቬስትራል የጦር አካዳሚ የከፍተኛ ታንክ ሜካናይዝድ ትምህርት እንዲከታተሉ ሆኑ፡፡
ሥራና ውትድርና
የሥራ ጅማሯቸው በወቅቱ በወታደራዊ ሥነስርዓቱና ግርማሞገስ በሚያጎናጽፈው አለባበሱና መለዮው በሚታወቀው የክቡር ዘበኛ ክፍል ውስጥ ቢሆን ይመኙ ነበር፡፡ ሆኖም ምድባቸው ግን ፈጽሞ ባላሰቡትና ባልተመኙት ላይ ጣላቸው፡፡ ይህም ናዝሪት ታንከኛ ሆነው መስራት ነው፡፡ ሥራውን ሲጀምሩ የአፍላነት እድሜ ላይ ስለነበሩ ምቾት የማይሰጧቸው ብዙ ነገሮች ነበሩባቸውና ደስተኛ መሆን አልቻሉም። ለአብነትም የሚያነሱት የመለዮ ጉዳይ ሲሆን፤ እንደሀዘንተኛ ጥቁር መለዮ አጥልቆ መስራት ደስታቸውን ነጥቋቸው እንደነበር አይረሱትም፡፡ ሆኖም አንድ የቅርቤ የሚሉት ሰው በነገራቸው የታንከኝነት ሙያ ሀሳባቸውን መቀየር ችለዋል፡፡ ሥራውን ብቻ ሳይሆን ስልጠናውን ጭምር ወደውት መውሰድ እንደቻሉም ያስታውሳሉ፡፡
በናዝሪት በመጀመሪያ በመኮንንነት ያገለገሉ ሲሆን፤ ከዚያ የታንከኛ ጉዳይ የትምህርት ረዳት መኮንን ሆነው መስራት ችለዋል፡፡ ከዚያ የሻምበልነት ማዕረግ እንዳገኙ ወዲያውኑ የምድር ጦር ታንከኛ መምሪያ ምክትል አዛዥ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ከአሜሪካ ተመርቀው እንደመጡ ደግሞ አሁንም በናዝሪት የታንከኛ ትምህርት መምህር ሆነው ሰርተዋል፡፡ የትምህርት ክፍሉ ምክትል ሀላፊም ነበሩ፡፡ ለሦስት ዓመታትም በቦታው አገልግለዋል። ከዚያ ኦጋዴን እንዲሄዱ በመደረጉ ሁልጊዜ ዝግጁ ብርጌድ ተብሎ በሚጠራው 10ኛ መካናይዝድ ብርጌድ ሥር የጅግጅጋ የ3ኛ ታንክ ሻንበል አዛዥ ሆነው ማገልገላቸውን ቀጠሉ፡፡ ለዓመት ያህልም በቦታው ከቆዩ በኋላ ደግሞ የታንክ ሻለቃ ብርጌድ በመቋቋሙ የ1ኛ ሻንበል አዛዥ ሆነው እንዲሰሩ ተዛወሩ፡፡
ብዙም ሳይቆዩ ግን ለምን ባይ በመሆናቸው ከአለቃቸው ጋር መግባባት አልቻሉምና ጥጋበኛ ሻንበል ተብለው ወደ ኤርትራ ተላኩ፡፡ በዚያም ከደረሱ በኋላ ፎርቶ የሚባል በረሃ እንዲላኩ ተወሰነባቸው፡፡ ነገር ግን ‹‹ሳይደግስ አይጣላ›› እንዲሉ ሆነና ነገሩ ኤርትራ ያለው የታንክ ቃኚ ሻለቃ አዛዥ ገንዘብ አጉሎ ስለነበረ ያለሙያቸው እዚያ መላካቸው ትክክል እንዳልሆነ በመተማመን ሀሳቡ ተቀይሮ በዚያ እንዲቆዩና የአዛዡን ቦታ እንዲተኩ የሦስት ወር የሙከራ ጊዜ ተሰጣቸው፡፡ መሻላቸውን በተግባር አሳዩናም የቅጣት ቦታው ሳይሄዱ ቀሩ፡፡ በዚህም በዚህ ቦታ ላይ የዋለያ ሁለተኛ እግረኛ ክፍለጦር የታንከኛ ቃኚ ሻምበል አዛዥ ሆነው ለሦስት ዓመታት አገለገሉ፡፡
በኤርትራ፣ በኡጋዴንና መሰል ቦታዎች ላይ የአየር ጥበቃ ሥራንም ሰርተው ስለሚያውቁ አየር መንገድ ገብተው ለመስራት የወሰኑት ባለታሪካችን፤ ከሦስት መቶ ሰዎች ውስጥ የመጀመሪያው ሆነው ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በአየርመንገድ የበረራ ደህንነት ጥበቃ አባል በመሆን ሰርተዋልም፡፡ ከተወስነ ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ደግሞ ወደ ጣሊያን ተልከው በሮው የደህንነት ጥበቃ ሀላፊ ሆነው ያገለገሉም ናቸው፡፡
ሌላው የሰሩበት ቦታ ዳግም ተመልሰው የሰሩበት ምድር ጦር ሲሆን፤ ታንከኛ መምሪያ ውስጥ በማመራረሻ ሻለቃ አዛዥ ሆነው ለዓመት ያህል ሰሩ፡፡ ከዚያ ከሥራ ጋር የተገናኙት ከራሺያ የትምህርት ቆይታ በኋላ ነው፡፡ የሱማሌ ጦርነት በመጀመሩ በቀጥታ ወደዚያ እንዲሄዱና አገርን እንዲታደጉ ተላኩ፡፡ ስለዚህም በታንከኝነታቸው ዘመቻውን ተቀላቅለው ቆዩ፡፡ ድል አድርገውም ተመለሱ። ይሁን እንጂ በወቅቱ ተመተው ነበርና ለህክምና ወደውጪ ሄዱ፡፡ ለአራት ወር ያህል በህክምና ቆዩ፡፡
ከህክምና መልስ አገራቸውን ማገልገል ማቆም አልፈለጉምና ወደ ናዝሪት ምድር ጦር ተመልሰው መስራታቸውን ቀጠሉ፡፡ የታንከኛ መምሪያ ምክትል አዣዥም ሆኑ፡፡ ዓመት ከሰሩ በኋላም አዣዥ ተደረጉ። ሥራቸው ጥሩ ነበርና ወደአዲስ አበባ ተዛውረው በመከላከያ ሚኒስቴር የታንክ ጉዳይ ሀላፊ እንዲሆኑ እድሉ ተሰጣቸው፡፡ በቦታውም ላይ ለሁለት ዓመት ሰሩ። በዚህ ሥራ ላይ እያሉ ሁለት ኮሎኔሎች ተጣልተው ከስራ በመባረራቸው ምክንያት ከአንዱ ጋር አብረው ድሬደዋ ላይ በመታየታቸው ‹‹ያስኮበለልከው አንተ ነህ›› ተባሉ።መባል ብቻም ሳይሆን ዓመት ከሦስት ወር እንዲታሰሩ ተፈረደባቸው፡፡
ምንም አይነት ጥርጣኔ ሳይኖር በነጻ ከእስር ሲለቀቁ ወዲያው ወደስራ ለመግባት አልፈለጉም ነበር። ሆኖም በብዙ ድርድር ሥራቸውን መጀመር ችለዋል። በዚህም በጦላይ ብሔራዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ገብተው የትምህርት መኮንን በመሆን ከኩባ የመጡ መኮንኖችንና ብሔራዊ ውታደሮችን ወደማሰልጠኑ ገብተዋል፡፡ በዚህ ከዓመት በላይ ከሰሩ በኋላ ደግሞ የኩባ ጦር ወደ አገሩ እንዲመለስ ሲባል የታጠቅን ብርጌድ የሚጠብቁት እነርሱ በመሆናቸው ቦታው ባዶ እንዳይሆን ሰው መተካት ነበረባቸውና ከብዙዎች መካከል እርሳቸው ተመርጠው ከጦላይ ወደ ታጠቅ ተዛወሩ፡፡ የ6ኛ መካናይዝድ ብርጌድ አዛዥ ሆነውም መስራት ጀመሩ፡፡
ሌላው ሥራቸው ቢሌ ላይ የነበረው ሲሆን፤ መንገድ ላይ በመሆን የሚዘርፉትን ለማስቆም ተቆጣጣሪነት ሲሰሩም ነበር፡፡ ወንበዴዎችን ለመደምሰስ በተደረገው አሰሳ ላይ በወሎና ትግራይ የጦር መሪ በመሆንም ተሳትፈዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በ6ኛ መካናይዝድ ብርጌድ የ4ኛ መካናይዝድ ክፍለጦር አዛዥ ሆነውም ወደ ዱብቲና ኪሎማ በማሰልጠን ሥራ ላይ ቆዩ። ምጽዋ መያዙ ሲሰማም እርሳቸው ከባህርዳር እስከ ጎንደር ያለውን ቦታ ይዘው ውጊያ እንዲያደርጉ ታዘዙ፡፡
የ603 ኮር ምክትልና ዋና አዛዥ በመሆንም ለሁለት ዓመት በቦታው ላይ ሰሩ፡፡ በዚህ ሥራቸው ላይ ትልቅ ፈተና ገጥሟቸው እንደነበር የሚያስታውሱት ጀነራል ዋስይሁን፤ እርሳቸው የያዙት ጦር በአብዛኛው ወደ ሰሜን ሸዋና ወደ ኤርትራ በመላኩ የተነሳ እርሳቸው 4ኛ መካናይዝድ ጦርን ብቻ ይዘው መዋጋት አልቻሉም ነበር። ይህ ከመፈጠሩ በፊት ግን ደጋግመው ለበላይ አካል አሳወቁ፡፡ ምላሽ የሰጣቸው ግን አልነበረም። እንደውም ያፌዙባቸው ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ‹‹ከመሞት መሰንበት›› ብለው ሰራዊቱን ከጥቃት ለመከላከል አስበው ወደወለጋ ይዘውት ሸሹ፡፡
ወያኔም ብዙ ነገሮች ተለቀውለት ነበርና ባህርዳርን ያዘ፡፡ ይህንን የሰሙ ኮሎኔል መንግስቱም በቁጣ ተነሱ። ከእነአጃቢያቸው እነጀነራል ዋሲሁንን ለመረሸን ወለጋ ድረስ መጡ፡፡ በወቅቱ ጠርተው ሲያነጋግሯቸው የነበራቸውን የፊት ገጽታ መቼም እንደማይረሱት ያስታውሳሉ፡፡ እንደሚሞቱም አምነው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም ቁጣ በተቀላቀለ ንግግር ነበር ‹‹እስኪ አምስት ክፍለአገር ለወንበዴ አስረክባችሁ እንዴት ፈርጥጣችሁ እንደመጣችሁ ተናገሩ›› ሲሉ የጮሁባቸው። የእንግዳችን አለቃም ራሳቸው ከመናገር ተቆጥበው ‹‹የጦር አዛዡ እርሱ ስለሆነ ይናገር›› ሲሉ ጣታቸውን ጠቆሙባቸው፡፡
መሞቴ እነደሆነ አይቀርም በሚል ስሜት ዓይን ዓይናቸውን እያዩም እውነቱን ለመናገር ወስነው እጅ በመንሳት ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡ ይህ እንዳይከሰት በማሰብ ከስምንት ወር በፊት በተደጋጋሚ አሳውቀው እንደነበርም አስረዱ፡፡ አለቃው ሲጠየቁም በአወንታ ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡ በወቅቱ መንግስቱ የሚያደርጉት ነገር ግራ ገብቷቸው ነበር፡፡ ሆኖም እንግዳችን ግን ተርፈዋል። ነጻነታቸውንም አውጀዋል፡፡ እንደውም ከዚህ ልቆ ሰላሳ ሺህ ብር ታዞላቸው እራት ሁሉ ተጋብዘዋል፡፡ ብዙም በዚያ እንዲቆዩና እንዲሰሩ ያልፈለጉት መንግስቱ በእርሳቸው ቦታ ላይ ሌላ ሰው በመተካት የተወሰነ ሹም ሽረት አደረጉና ረዳት ሆነው እንዲሰሩ ወደ አዲስ አበባ ቀየሯቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ኢህአዴግ አዲስ አበባን እስኪቆጣጠር ድረስ በአዲስ አበባ ሰሩ፡፡ አዲስ አበባ ስትያዝ ደግሞ በቀጥታ የደርግ ጀነራል ተብለው ለእስር ተዳረጉ፡፡ 10 ዓመትም ያላንዳች ክስ ተሰቃዩ፡፡ የውትድርና ሥራቸው የተቋጨውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በእነዚህ ቆይታቸው ግን አብዛኛው የሰራ ህይወታቸው በታንከኛ ክፍል ውስጥ ማለፉን አይዘነጉትም፡፡
በንጉሱ ዘመን ለ13 ዓመት፣ በደርግ ደግሞ ለ17 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከዚያ ቀጣዩ እጣ ፋንታቸው አገራቸውን ማገልገል ከመከላከያው ወጣ፡፡ በጡረታ እስኪገለሉም ድረስ አገራቸውን በሰላምና ዕርቅ፣ በበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ አበርክቶ ያደርጉ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን ጡረታ ሳይገድባቸው ይህንኑ ሥራ በቻሉት ልክ ያከናውናሉ፡፡ በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች ላይ በመገኘት ስለሀገር ፍቅር፣ ስለ ነጻነት ክብርና ኩራት ወኔ ቀስቃሽ የሆኑ ንግግሮችን ያደርጋሉ። ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ አርበኞችና የጦር ጀግኖች በሕዝብ ዘንድ እንዲታወሱና በመንግሥት በኩል ቋሚ የሆነ መታሰቢያ እንዲደረግላቸው የበኩላቸውን ጥረት ከማድረግ ወደኋላ አላሉም፡፡
በስነጽሁፍ ዘርፍም በመሰማራት ለአገራቸው ባለውለታ የሆኑ ፣ ለሕዝባቸው መሥዋዕትነት የከፈሉትን እንዲታወሱና በትውልድ አዕምሮ ውስጥ እንዲቀመጡ ለማድረግ በግላቸው ‹‹ዕጣ ፈንታ እና መሥዋዕትነት›› እንዲሁም ተከታይ የሆነ ሁለተኛ መጽሐፋቸውን ‹‹ያልታደለች ሀገር፣ ሕዝብ እና ሰራዊት›› በሚል መጸሐፍ ጽፈው አበርክቷቸውን አድርገዋል፡፡
‹‹እኔ የኢትዮጵያ ጀነራል እንጂ የደርግ አይደለሁም›› የሚል አቋም ያላቸው ባለታሪካችን ፤ በውጊያ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡ የተሻለ ነገር እንዲያገኝም የሰሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ እርሳቸውንም ሆነ ማህበረሰቡን ያስደሰተው የትምህርትቤት ግንባታ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ የኮሎኔል ደጀኔ ስሜ ትምህርትቤት ሲሆን፤ ማህበረሰቡንም ሆነ ባለሀብቱን እንዲሁም ወታደሩንና ባለስልጣኑን ያነቃቁበትን ጥበብ ዛሬ ድረስ አይረሱትም።ከአሰቡት የእጥፍ እጥፍ ገንዘብ አግኝተው በአጭር ጊዜ ትምህርት ቤቱን ማስመረቃቸውም መቼም የማይረሱት እንደሆነ አጫውተውናል፡፡
ግዳጅ ለአገር ሲሆን
ገና ከናዝሪት የጦር ትምህርትቤት እንደተመረቁ የመጀመሪያ ግዳጃቸውን በኦጋዴን ጦርነት ጀምረዋል። ጥሩ ድል እንዲመጣ ካደረጉ መካከል አንዱ መሆን የቻሉም ናቸው፡፡ ምክንያቱም 17 ታንኮችን ይዘው በታንክ የመቶ መሪነት ቦታውን ተፈናጠው ወደ ኦጋዴን ዘምተው የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋልና ነው። በተለይም ጅጅጋ ታንከኞችን እያሰለጠኑ ጭምር ዘመቻውን መደገፋቸው ለድሉ ጥሩ ስንቅ መስጠት የቻሉ ነበሩ፡፡ ሌላው በቶጎጫሌ ሁለቱም ጦርነት ላይ ተሳታፊም የሆኑበት የሚያስመሰግናቸውና ለአገራቸው ግዳጃቸውን የተወጡበት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
በሱማሌ ጦርነትም ቢሆን ከራሺያ ድረስ መጥተው መሳተፋቸው ግዳጅ ለአገር ሲሆን ለየት የሚል ስሜት እንዳለው ያስመሰከሩበት ነው፡፡ ከኩባ የመጡ ታንከኞችም ስለነበሩ ከእነርሱ ጋር በመሆን ነበር ሱማሌን ድል መምታትና አገርን ነጻ ለማውጣት የቻሉት። በዚህ ዘመቻ ላይ ሄልሜት ባያደርጉ ይሞቱ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ምክንያቱም በሚታኮሱበት ጊዜ ታንክ ላይ የሚያርፈው ፍንጣሪ ሄልሜቱን ጥሶ ከዓይናቸው ከፍ ብሎ ቅንድባቸው አካባቢ ክፉኛ መቷቸዋል፡፡ በዚህም አራት ጊዜ ቀዶ ህክምና አድርገዋል፡፡ ከሌላው ሰውነታቸው ላይ ተወስዶም ስጋው እንደተሞላ ይናገራሉ፡፡ ይህም ለአገር ሲሆን ይገባል ያስብላቸዋል፡፡
በአጠቃላይ እንግዳችን በውጪም ሆነ በአገር ውስጥ ሆነው አገራቸውን በብዙ መንገድ አገልግለዋል። ለአብነትም በአገር ውስጥ ብቻ በኦጋዴን፣ ሐረር፣ በኤርትራ አስመራ፣ በትግራይ፣ በወሎ፣ በጎንደርና በባሕር ዳር ሀገራቸውን በተለያዩ ወታደራዊ ግዳጆች ላይ በመዝመት አገልግለዋል፡፡
መልዕክት
መከላከያ መቼም ቢሆን አይሞትም፡፡ ምክንያቱም ሞትን ለሀገሩ፣ ለሕዝቡ ባለው ፍቅርና በከፈለው ትልቅ መስዋዕትነት ድል ይነሰዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን የሚዘምተው ይህንን አስቦ መንቀሳቀስና አገሩን ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ወታደርም የማንም ሳይሆን የአገር ብቻ በመሆኑ የንጉሱ፣ የደርግ እንዲሁም የኢህአዴግ ሊባል አይገባውም። ምክንያቱም እርሱ እስከዛሬ የተዋደቀውና የተዋጋው በየዘመናቱ የገዙትን መንግስታት ህልውና ለማስቀጠል ሳይሆን የአገሩን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ነው። ስለዚህም አስተሳሰቡ መቀየር አለበት። ለአገር ህልውናና ለመንግስት ህልውና መታገል በፍጹም የተለየዩ መሆናቸውን ሁሉም መገንዘብ አለባቸው የመጀመሪያ መልዕክታቸው ነው፡፡
ሌላው ያነሱት ነገር በየዘመናቱ የተካሄዱ ጦርነቶችና የወታደራዊ ዘመቻ ታሪኮቻችንን ስንመለከት በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የተደረገ የእርስ በርስ ጦርነት ነው፡፡ ስለዚህም በክብርና በኩራት የምንተርከው ታሪክ ከመሆን ይልቅ በጸጸት የምናስታውሰው፣ በእፍረት የምንሸማቀቅበት ስለሆነ ከስህተታችን ተምረን በውይይትና በመተማመን ንግስናን ወይም ማስተዳደርን ለሚገባው መስጠት መቻል ላይ መድረስ ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ በተለይ እንደ ህወሓት አይነት እኔ ከሌለሁ ሰርዶ አይብቀል ባዮች ለአገራችን ውድቀት እንጂ ብልጽግና አይበጁምና አስተሳሰቡን መቀየር ላይ በስፋት ሊሰራ ይገባል ብለውናል፡፡
ሕይወት ብዙ ውጣ ውረድ አላት፡፡ ክፉም በጎም ይፈራረቁባታል፡፡ ተቃራኒ ስሜቶች ይቀራመቱናልም። አብዛኛው ደግሞ መራራ የጉዞ ሂደቶች ናቸው፡፡ እነዚህም የተፈጠሩት በራሳችን በሰዎች ችግር ምክንያት ነው፡፡ስለዚህም መፍቻ ቁልፎቹም ራሳችን መሆናችንን ማሰብ አለብን፡፡ ሰው ከእንሰሳት ሁሉ የላቀ የሆነበት ምክንያት አስቦና አስልቶ ስለሚጓዝ ነው፡፡ ስለሆነም አስቦና አስልቶ መጓዝ የዛሬው ዋነኛ ስራችን መሆን አለበት። የፍቅር ስሜታችንን አምጥቀን አለመግባባቶችን በጥበብና በትዕግሥት፣ በውይይትና ቀርቦ በመነጋገር በሰላማዊ መንገድ ፈተን መራመድ መጀመርም ከምንም በላይ ያስፈልገናል ሌላው መልዕክታቸው ነው፡፡
በመጨረሻም በተለያዩ ሰበቦች ሁከት እያነሳ የጥበብና የፍቅር ውጤቶችንና ስሜቶችን የሚያወድም ግጭት እየፈጠረ እንደተራበ ተኩላ እየተነካከሰ ራሱንና አካባቢውን በጦርነት ማውደም አውሬነት ነው። አገርንም ከመካድ አይተናነስም፡፡ እናም ሀገራችን የተፈጥሮ ሀብትና ውበት ሳታጣ ለዘመናት የጦርነትና ጉስቁልና (ድህነት) ውስጥ እንድትቆይ ማድረጋችንን ማቆም አለብን፡፡ ለምንወልዳቸው ልጆች ስንልም ሰላምን ፍቅርን ዕድገትን ለማውረስ እንሞክር ብለዋል። እኛም ይህ መልዕክታቸው በልባችን ይኑር በማለት አበቃን፡፡ ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም