ሀገራችን ተገዳ በገባችበት በአሁኑ ጦርነት መሬት ላይ ከሚካሄደው ነባራዊ ሁኔታ በብዙ መልኩ የሚለዩ የተለያዩ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ዘመቻዎች ደግሞ በአንድ በኩል እስትንፋሳቸው ካልወጣች በስተቀር “አልሞትም፣ አለን” ለማለት እዚህም እዚያም ጥቃት በሚፈጽሙት የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዦች፤ በሌላ በኩል ደግሞ እነሱን በሚደግፉ አንዳንድ የምእራብ ሃገራት እንዲሁም በነዚህ ሃገራት በሚዘወሩ ሚዲያዎቻቸውና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን በሚሉና ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች አማካኝነት የሚነዛ ነው፡፡
የአሸባሪው ህወሓትን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች ስንመለከት በአብዛኛው የራሳቸውን የወደቀ ስነልቦና ለመጠገንና የደጋፊዎቻቸውን ድጋፍ ለማግኘት የሚነዙት የድል ዜናዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አሸባሪዎቹ 80 ከመቶ የሚሆነውን የሃገሪቱን የጦር መሳሪያ ይዘው ወረራ በፈፀሙ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እግሬ አውጭኝ ብለው ከፊሎቹ በቀበሮ ጉድጓድ፤ ገሚሶቹም ከየጥሻው ተለቅመው መውጣታቸው እየታወቀ መንግስት ለአርሶ አደሩ እፎይታ ጊዜ ለመስጠትና ህብረተሰቡም የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ ትግራይን ለቆ በወጣ ማግስት አሸነፍናቸው እያሉ መፎከር ጀመሩ፡፡ ይህ ደግሞ በውሸት ራስን ለመደለል የሚደረግ ደካማ የስነልቦና ማካካሻ ነው፡፡
ከዚያ በኋላ ደግሞ መንግስት የተናጠል የቱኩስ አቁም ማድረጉን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአማራና በአፋር ክልሎች የፈፀሙት ወረራና ከዚህ ጋር ተያይዞ በንፁሃን ሲቪሎች ላይ የፈጸሙት ጥቃት የውድቀታቸው ማሳያ ነው፡፡ በነዚህ አካባቢዎች የአሸባሪው ቡድን አባላት በአንድ በኩል የጦርነት የበላይነት መያዛቸውን ለማሳየት “ይህንን ከተማ ተቆጣጠርን፤ አሁን እዚህ ደርሰናል” የሚያናፍሱት ወሬ ሌላኛው የራስን ስነልቦና የመገንቢያ የውሸት ማታለያ ነው፡፡
በዚህ ሂደት ታዲያ ሁኔታውን በአግባቡ ያልተረዱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተለያዩ ጉዳቶች ተዳርገዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በአንድ በኩል የአሸባሪው ህወሓት አባላት በደረሱበት ቦታ ሁሉ በጭካኔ ሲቪሎችን በመጨፍጨፍ ጠንካራ ለመምሰል የሄዱበት መንገድ አንዱ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የሚያይ የህብረተሰብ ክፍል አካባቢውን ጥሎ እንዲሰደድ በማድረግ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ መፍጠር ችለዋል፡፡
በዚህ ሂደት የሽብር ቡድኑ ቃልአቀባይ አሸባሪው ጌታቸው ረዳ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያገኛቸው የውጭ ሚዲያዎችና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም የሚያሰራጨው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ቡድኑ በወሬ ብቻ ያለ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ሰው እስካሁን ድረስ ደመሰስን እያለ የሚገልጻቸው ክፍለጦሮችና የሰራዊት አባላት የሃገሪቱ ህዝብ ሁሉ የጦር ሰራዊት ነው ወይ? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ነገር ግን የሚለቃቸው የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎች ራስን ከማታለል በዘለለ አንዳችም ፋይዳ ያለው አይደለም፡፡
በአንጻሩ ግን መንግስት ቀደም ሲል በሰጠው የተናጠል ተኩስ አቁም መነሻት ተገቢውን እርምጃ ሳይወስድ ለብዙ ጊዜ ቆይቷል። በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ በርካታ ጫናዎችን ሲያደርጉ የነበሩት የአሜሪካም ሆነ የአውሮፓ ህብረት አካላት ይህንን የተኩስ አቁም የአሸባሪው ህወሓት ቡድንም እንዲያከብር ከማድረግ ይልቅ ዝምታን በመምረጣቸው አሸባሪው ሃይል በትዕቢት እንዲያንጠራራና ወደ አማራና ወደ አፋር ክልሎች ገብቶ ንጹሀንን እንዲጎዳ እድል ሰጥቷል፡፡ በዚህ ሂደትም አሸባሪው በደረሰባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋት ፈጽሟል፡፡
በመጨረሻ ግን መንግስት ችግሩ እየከፋ ሲሄድ ይህንን ጥፋት ለማስቆም የመልስ ምት መስጠት በመጀመሩ አሸባሪው ህወሓት እንደለመደው ወደጫካው ለመመለስ ፍጥነቱን ጨምሯል፡፡ በዚህ ሂደትም የተማረኩ የአሸባሪው ህወሓት አባላት እንደሚናገሩትና በተጨባጭም እንደታየው ከጀርባቸው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ እንደነበረ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ መንግስት ይህንን የሽብር ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ ህብረተሰቡ ፊቱን ወደልማት እንዲያዞር ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃገር መከላከያ ሰራዊትና ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ጁንታውን በመቅጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ አሸባሪዎቹ ተቆጣጠርን ያሏቸውን ቦታዎችም መልሰው በመያዝ ህብረተሰቡ ተረጋግቶ ወደስራው እንዲመለስ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
አሁን የመንግስት ዋነኛ ትኩረት አሸባሪው ህወሓት እንደሚያደርገው”ይህንን ከተማ ያዝን፣ ይህንን አስለቀቅን” የሚል አይደለም፡፡ በተጨባጭ አሸባሪውን ለመቅጣት ከሚደረገው ጦርነት በዘለለ ኅብረተሳቡ ተረጋግቶ ወደስራና ልማት እንዲመለስ የማድረግ እና ኢትዮጵያን ወደብልጽግና የማሻገር ራዕይን ለማሳካት የመስራት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም በአሁኑ ወቅት የአሸባሪው ህወሓት በሃገሪቱ ላይ ተጨባጭ ችግር ሊያስከትል የሚችልበት አቅም እየተሟጠጠ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ይህንን ጁንታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ መላውን ኢትዮጵያ ከሽርተኞች ማጽዳትና ህብረተሰቡ በአንድ ስሜት ወደልማት ፊቱን እንዲያዞር ስራ እየተሰራ ነው፡፡
በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውንም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለሃገራቸው ነባራዊ ሁኔታና ስለተያዘው የእውነት መስመር ለዓለም ማህበረሰብ ሃቁን ለማሳወቅ ከመንግስት ጎን በመቆም መንቀሳቀስ ጊዜው የሚጠይቀው ወቅታዊ ጥያቄ ነው፡፡ እውነትን ይዘን እና ጫናውን ተቋቁመን ኢትዮጵያን ወደከፍታ ማሻገር ጊዜው የሚጠይቀው ወቅታዊ ጉዳይ ነውና!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም