በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ የስፖርት አይነቶች የተሳተፉ አትሌቶች በብሔራዊ ቤተመንግስት የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል። የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ባዘጋጀው የሽልማት ሥነስሥርዓት ላይ በኦሊምፒኩ የተሳተፉ አትሌቶች ከትናንት በስቲያ ምሽት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። በኦሊምፒኩ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በአስር ሺ ሜትር ያስመዘገበው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ከፍተኛ ሽልማት ከፕሬዘዳንቷ ተረክቧል።
ሰለሞን ባስመዘገበው ድል የሶስት ሚሊዮን ብር ቶዮታ መኪናና አርባ ግራም ወርቅ ተሸልሟል። በኦሊምፒኩ የተሳተፉ አትሌቶች እንደየውጤታቸው የሚመጥን ሽልማት በተበረከተላቸው ምሽት ብቸኛውን የብር ሜዳሊያ በሶስት ሺ ሜትር መሰናክል ያስመዘገበው አትሌት ለሜቻ ግርማ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆኗል። በአስርና አምስት ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገቡት አትሌት ለተሰንበት ግደይና ጉዳፍ ፀጋይ እያንዳዳቸው የአንድ ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆነዋል።
የወርቅ ሜዳሊያ ላስገኘው ዋና አሰልጣኝ ሁሴን ሼቦ የሶስት መቶ ሺ ብር ሽልማት ሲበረከት፣ ምክትል አሰልጣኙ ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ ሁለት መቶ ሺ ብር ሽልማት ተበርክቷል። የብር ሜዳሊያ ላስገኘው ዋና አሰልጣኝ ተሾመ ከበደ የሁለት መቶ ሺና ለምክትሉ ኢብራሂም ዳኜ የመቶ ሺ ብር ሽልማት ሲበረከት፣ የነሐስ ሜዳሊያ ላስገኙ ዋና አሰልጣኞች ህሉፍ ይህደጎና ሀይሌ እያሱ የመቶ ሺ ብር እንዲሁም ለምክትሎቻቸው ንጋቱ ወርቁና ኢሳ ሼቦ የሰባ ሺ ብር ሽልማት ለእያንዳዳቸው ተበርክቷል።
በውድድሩ በ4ኛ ደረጃ የዲፕሎማ ተሸላሚ ለነበሩ አትሌቶች እያንዳንዳቸው የ200 ሺ ብር ተሸላሚ ሲሆኑ በደረጃ እስከ 8ኛ ላጠናቀቁ ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የ150ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ለተሳታፊ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸውም የ50 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቷል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ በእግር ኳስ ዳኝነት የተሳተፈው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ልዩ ተሸላሚ በመሆን 100 ሺ ብር ተበርክቶለታል።
ባለፈው ሰኞ በሸራተን አዲስ በተመሳሳይ ለቶኪዮ ጀግኖች ሽልማት ያበረከተው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ላስመዘገቡ አትሌቶችና አሰልጣኞች የተለያየ የገንዘብ መጠንና እውቅና ቢያበረክትም ከዲፕሎማ ጀምሮ የተለያዩ ታሪካዊ ውጤቶችን ያስመዘገቡ አትሌቶችን በይፋ ሳይሸልምና እውቅና ሳይሰጥ መቅረቱ ቅሬታ ፈጥሮ ነበር። በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው አትሌት ሰለሞን ቱፋ ከተሳትፎ ባለፈ የዲፕሎማ ደረጃ ቢያስመዘግብም በኦሊምፒኩ ሽልማትና እውቅና በይፋ ሳይሰጠው በመቅረቱ በርካቶችን አስቆጥቶ ነበር።
ሰለሞን ከቀናት በፊትም በማህበራዊ ገፁ ‹‹በኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክንያት አገሬ የእንጀራ እናት ሆነችብኝ፣ የደማሁላት ዋጋ የከፈልኩላት አጥንቴን ሰብሬ ደሜን ያፈሰስኩላት በዓለም መድረክ ላይ ባንዲራዋን ካውለበለብኩላት አገሬ ጋር በኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክንያት የእንጀራ እናትና ልጅ ሆንን። ያሳዘነኝና ልቤን የሰበረው የኦሊምፒክ ኮሚቴ ባዘጋጀው የምስጋናና የሽልማት መርሃግብር ላይ ምስጋና ይቅርና ስሜን እንኳን አልጠራም፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ያደረሰብኝን በደል የኢትዮጵያ ህዝብ እና የሚመለከተው አካል ሁሉ እንድያቅልኝ እፈልጋለሁ።›› በማለት ቅሬታውን ገልጿል።
ሰለሞን በኦሊምፒክ ኮሚቴ ሽልማትና እውቅና ቢነፈገውም በብሔራዊ ቤተመንግስቱ ሽልማት 150 ሺ ብር ተሸላሚ ሆኗል። ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሽልማት መርሃግብሩ ላይ ‹‹ከቶኪዮ ኦሊምፒክ መንግስት እና ህዝብ ብዙ ጠብቆ ነበር ፣ነገር ግን እስካሁን ከተሳተፍንባቸው ኦሊምፒኮች ያነሰ ውጤት ተመዝግቧል›› ብለዋል ። በመሆኑም በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ችግሮችን በመለየት ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግና እንደ አዲስ መደራጀት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013