ኢትዮጵያ እና ሱዳን ዘመናትን የተሻገረ አብሮነትና ትብብር ያላቸው አገራት፤ ህዝቦቻቸውም ሰፊና ጥልቅ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቡናዊ ትስስር ያላቸው ናቸው፡፡ ይህ አብሮነትና ትብብር መሰረት ባደረገ መልኩም ኢትዮጵያ ለሱዳንና ሱዳናውያን አንድነትና ሰላም ብዙ የሰራችና ውድ ዋጋም የከፈለች አገር ናት፡፡
ለማሳያም ያህል ሱዳናውያን የውስጥ ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ ኢትዮጵያ ወደ አካባቢው ጦሯን በመላክ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋን ተወጥታለች፤ በተለይም በአብዬ ግዛት በነበረው ቀውስ የሱዳን ህዝብ የሌላ የማንም አገር ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ለማረጋጋት እንዲገባ የጠየቀው ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ካለው ትልቅ ክብርና እምነት የተነሳ ነው። በቅርቡም ህዝባዊ ተቃውሞው አይሎ ሱዳን መረጋጋት በተሳናትና የመንግስት ግልበጣ በተካሄደበት ወቅትም ቢሆን፤ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሯ አማካኝነት ተቀናቃኝ ቡድኖችን አቀራርባ በማነጋገር በጋራ የሚሰሩበትንና ሰላም የሚሰፍንብትን ዕድል ፈጥራለች፡፡
ይሁን እንጂ የበሉበትን ወጪት የረገጡ፤ ለህዝባቸው ሳይሆን ለውጭ አካላት ፍላጎት መሳካት እንቅልፍ ያጡ አካላት በሱዳን የመንግስት አስተዳደር ውስጥ ተሰግስገው የሚገኙ የግብጽ ተላላኪዎች ኢትዮጵያን እንደ አገር፤ ኢትዮጵያውያንንም እንደ ህዝብ ለመውጋትና ለማጥፋት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ በሱዳን መንግስት ውስጥ ተሰግስገው የሶስተኛ አካል ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን እንቅልፍ ያጡ አካላት፤ ጉዳያቸው የሱዳን ህዝብ መሆኑን የዘነጉ፤ ሰላማቸው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በትብብር መራመድ መሆኑ የተጋረደባቸው ናቸው፡፡ ምክንያቱም ጉዞና እርምጃቸው ሁሉ ለውጭ ኃይሎች ፍላጎት ሲሉ ሱዳናውያንን አደጋ ላይ የሚጥል፤ አዛዦቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን መልካም አጋርነት የሚያሻክር ብቻ ሳይሆን ወደለየለት ችግር ውስጥ የሚያስገባም ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን መገንባቷ ፋይዳው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሱዳንም ከፍ ያለ ስለመሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የነበረው መንግስት የህንን በሚገባ በመገንዘብ ከኢትጵያ ጎን የመቆም አቋም የነበረው ቢሆንም፤ በመንግስት ግልበጣ በመጣው አመራር ውስጥ የተሰገሰጉ ተላላኪ ኃይሎች ግን የግብጽን ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ ግልጽ ወደሆነ ተቃውሞ ገብተዋል፡፡ ይሄ ደግሞ እነዚህ የሶስተኛ አካል አስፈጻሚ አካላት ለሱዳን ህዝብ አስበው እንደማይሰሩ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ሌላው፣ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር ተከትሎ እነዚህ ተላላኪ አካላት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት አልፈው መውረራቸው ነው፡፡ ይህ የሁለቱን አገራት የቆየ መልካም ግንኙነት የሚያሻክር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሆደ ሰፊነት ባይኖር ኖሮ ወደለየለት ጦርነት የሚያስገባ አክሳሪና ሱዳንን ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍል ተግባር ነው፡፡
በዚህ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ መፈጸማቸው ሳያንስ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ፣ ኢትዮጵያውያንን ለማሸበር እየሰራ ካለው አሸባሪ ቡድን ህወሓት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን በተግባር አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በማይካድራ ንጹሃንን ጨፍጭፈው ወደሱዳን የተሰደዱ እና በሱዳን መጠለያ ጣቢያ ያሉ አሸባሪዎች በሱዳን ሰልጥነውና ታጥቀው ወደኢትዮጵያ በመግባት ጥቃት ሊፈጽሙ ሲሉ መደምሰሳቸው ነው፡፡
እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥም ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ቡድን ጋር ለማደራደር ዝግጁ ነን የሚል ፌዝ መሰል ሃሳብ በሱዳን መንግስት ቢሰነዝርም ለዚህ የሚበቃ ታማኝነት ስለሌለው ኢትጵያ ጥያቄውን ወድቅ አድርጋዋለች። በቀጥታ ወረራ በመፈጸምና በትብብርም አሸባሪውን ቡድን በማሰልጠን ኢትዮጵያን ሉዓላዊነቷን ተዳፍረው ኢትዮጵያውያንን እየወጉ ባለበት ወቅትና የአሸባሪውን ቡድን ህልውና ለማቆየት በስውር ከሚሰሩት ሥራ አንጻር እናሸማግል የሚለውን የጣልቃ ገቦች ፍላጎትን ይዘው መንቀሳቀሳቸው በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ዘንድ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነበር፡፡
ይህ ደግሞ በሱዳን መንግስት ውስጥ ተሰግስገው ያሉት የሶስተኛ ቡድን ጉዳይ አስፈጻሚዎች ስለ ኢትዮጵያና ሱዳን እንደ ህዝብም ሆነ እንደ አገር የነበረውም ሆነ ያለው መልካም ትብብርና አብሮነት የማያስጨንቃቸው ለመሆኑ ግልጽ ማሳያ ሲሆን፤ ስራና እንቅስቃሴያቸውን ለውጭ ኃይሎች ፍላጎት ቀን ከሌት እንቅልፍ አጥቶ መስራት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ግብጽ የበዛ መሬታቸውን ይዛ እያለ በትብብር እየሰሩ፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ዘልቀው ገብተው እያለ ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላም እንፍታ እያለች እንኳን ለሰላማዊ ንግግር በራቸውን መዝጋታቸው ግልጽ ማሳያ ነው፡፡
በመሆኑም የሱዳን ህዝብ በመንግስት ውስጥ የተሰገሰጉ የሶስተኛ አካል አስፈጻሚዎችን ሴራ ማወቅና ይህ አካሄድ ለሱዳን ብሄራዊ ጥቅም አደጋ መሆነ ከግንዛቤ መግባት አለበት፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አካላት ወዳጅ አገርን ወግቶ፤ ወንድም ህዝብን አስቀይሞ የሚያደርጉት ጉዞ የሱዳንን ህዝብ ጥቅም ሳይሆን የሶስተኛ ወገን ፍላጎት እያስፈጸሙ መሆናቸውን ማረጋገጫ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በእነዚህ ኃይሎች አማካኝነት ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የያዘችው አቋም አክሳሪና ሱዳንን ዋጋ የሚያስከፍላት ነው፡፡ በመሆኑም ሱዳናውያን ወንድሞች ይሄንን አካሄድ ተገንዝበው ከወዲሁ ሂደቱን በቃ ሊሉና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን መልካም መስተጋብር ወደነበረበት መመለስ በሚቻልበት ላይ መስራት ይኖርባቸዋል! በአጠቃላይ ከሱዳን ህዝብ ፍላጎት ውጪ አንዳንድ በሱዳን መንግሰት ውስጥ የተሰገሰጉ ተላላኪዎች በኢትዮጵያ ላይ የሚየያራምዱት አቋም የተሳሳተና ውድ ዋጋ የሚያስከፍል ነውና የሱዳን መንግሰት የሱዳንን ህዝብ ፍላጎት ሊያከብር ግድ ይላል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013